አመስጋኝ መሆናችሁን አሳዩ
1 የምንኖረው ‘በሚያስጨንቅ ጊዜ’ ውስጥ ቢሆንም ይሖዋን እንድናመሰግን የሚገፋፉን በርካታ ምክንያቶች አሉን። (2 ጢሞ. 3:1) ለእኛ ሲል ልጁን በመስጠት ያበረከተልን ውድ ስጦታ በዋነኝነት የሚጠቀስ ነው። (ዮሐ. 3:16) ከዚህም በላይ በሐሰት ሃይማኖት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች በመንፈሳዊ እየተራቡ ባሉበት ወቅት እኛ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ አግኝተናል። (ኢሳ. 65:13) ዓለም አቀፍ የሆነ የወንድማማች ማኅበር አባላት ከመሆናችንም በላይ እውነተኛውን አምልኮ በማስፋፋቱ አስደሳች ሥራ የመካፈል መብት አግኝተናል። (ኢሳ. 2: 3, 4፤ 60:4-10, 22) ይሖዋ አትረፍርፎ ለሰጠን በረከት አመስጋኝ መሆናችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?—ቆላ. 3:15, 17
2 ከልብ ተነሳስተን በደስታ ማገልገል:- ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ቁሳዊ ልግስና ሲናገር “እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ሰው ይወዳል” ብሏል። (2 ቆሮ. 9:7) ይህ መሠረታዊ ሥርዓት ለአምላክ በምናቀርበው አገልግሎት ረገድም ይሠራል። አመስጋኝ መሆናችንን ለእውነት ባለን ፍቅር፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በምናሳየው የደስተኝነት መንፈስ፣ አገልግሎታችንን በቅንዓት በማከናወን እንዲሁም የአምላክን ፈቃድ በደስታ በመፈጸም ማሳየት እንችላለን።—መዝ. 107:21, 22፤ 119:14፤ 122:1፤ ሮሜ 12:8, 11
3 በጥንቷ እስራኤል አንዳንድ መሥዋዕቶች የሚቀርቡበት መጠን በሕጉ አልተደነገገም ነበር። እያንዳንዱ የይሖዋ አገልጋይ ‘አምላኩ እግዚአብሔር በባረከው መጠን’ በመስጠት አመስጋኝነቱን መግለጽ ይችል ነበር። (ዘዳ. 16:16, 17) ዛሬም በተመሳሳይ ልባችን በአመስጋኝነት መንፈስ ሲሞላ በመንግሥቱ ስብከትና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ሁኔታችን የሚፈቅድልንን ያህል እንድንካፈል ይገፋፋናል። አንዳንዶች የሥራ ወይም የትምህርት ቤት እረፍታቸውን በመጠቀም በመስክ አገልግሎት የሚያሳልፉትን ሰዓት ከፍ ለማድረግና አልፎ ተርፎም በረዳት አቅኚነት ለማገልገል ይጥራሉ። አንተስ አገልግሎትህን ማስፋት ትችላለህ?
4 የተትረፈረፈ ምስጋና:- አመስጋኝነታችንን ለይሖዋ መግለጽ የምንችልበት ዋነኛው መንገድ ጸሎት ነው። (1 ተሰ. 5:17, 18) የአምላክ ቃል “የተትረፈረፈ ምስጋና” እንድናቀርብ አሳስቦናል። (ቆላ. 2:7) በጣም ሥራ በሚበዛብን ወይም ውጥረት ውስጥ በምንሆንበትም ጊዜ እንኳ በየቀኑ በምናቀርበው ጸሎት ላይ ምስጋና ማካተት ይኖርብናል። (ፊልጵ. 4:6) አዎን፣ በአገልግሎታችንና በጸሎታችን “ብዙ ምስጋና ለእግዚአብሔር [እናቅርብ።]”—2 ቆሮ. 9:12