ይሖዋ በእርሱ የሚታመኑትን ይረዳቸዋል
1 ብዙ ሰዎች ገንዘብ፣ ሥልጣን እንዲሁም በአንድ መስክ ባለሞያ መሆን የስኬት ቁልፍ እንደሆኑ ይሰማቸዋል። (መዝ. 12:4፤ 33:16, 17፤ 49:6) ይሖዋን ለሚፈሩና በእርሱ ለሚታመኑ ሰዎች ግን መጽሐፍ ቅዱስ “ረዳታቸውና ጋሻቸው እርሱ ነው” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል። (መዝ. 115:11) በይሖዋ እንደምንታመን ልናሳይባቸው የሚገቡ ሁለት ዘርፎችን እንመልከት።
2 በክርስቲያናዊ አገልግሎታችን፦ በጉባኤ ውስጥ ክፍል ተሰጥቶን ስናቀርብም ሆነ በመስክ አገልግሎት ስናስተምር በአምላካችን ልንታመን ይገባል። የኢየሱስን ምሳሌ እንመልከት። የአምላክ ልጅ ቢሆንም እንኳ በራሱ ጥበብ ወይም ችሎታ ሳይሆን በሰማይ በሚኖረው አባቱ ሙሉ በሙሉ እንደሚታመን አሳይቷል። (ዮሐ. 12:49፤ 14:10) እርሱ እንደዚህ ካደረገ እኛማ ምን ያህል በአምላክ ልንታመን ይገባል! (ምሳሌ 3:5-7) የምናከናውነው አነስተኛ ሥራ ይሖዋን ሊያስከብርም ሆነ ሰዎችን ሊጠቅም የሚችለው የእርሱ በረከት ሲታከልበት ብቻ ነው።—መዝ. 127:1, 2
3 መመሪያ እንዲሰጠንና በመንፈስ ቅዱሱ አማካኝነት እንዲረዳን ወደ ይሖዋ በመጸለይ በእርሱ እንደምንታመን እናሳያለን። (መዝ. 105:4፤ ሉቃስ 11:13) በተጨማሪም ትምህርታችን በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን በማድረግ በእርሱ እንደምንታመን እናሳያለን። በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው መልእክት የሰዎችን ልብ ለመንካትና ሕይወታቸውን ለመለወጥ የሚያስችል ኃይል አለው። (ዕብ. 4:12) የምናገለግለው “እግዚአብሔር በሚሰጠኝ ኃይል ነው” በሚል መንፈስ ከሆነ ይሖዋ ይከበራል።—1 ጴጥ. 4:11 የ1954 ትርጉም
4 ችግሮች ሲያጋጥሙን፦ ችግሮች ሲያጋጥሙንና ተጽዕኖ ሲበረታብንም የይሖዋን እርዳታ መጠየቅ ያስፈልገናል። (መዝ. 46:1) ለአብነት ያህል፣ በአንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ ለመገኘት አሠሪያችን ፈቃድ ይከለክለን ወይም በቤተሰባችን ውስጥ አንድ አስቸጋሪ ሁኔታ ይገጥመን ይሆናል። ስለ ጉዳዩ አጥብቀን ወደ ይሖዋ በመጸለይ እንዲሁም በቃሉና በድርጅቱ አማካኝነት የሚሰጠንን መመሪያ ተግባራዊ በማድረግ በእርሱ እንደምንታመን እናሳያለን። (መዝ. 62:8፤ 119:143, 173) የይሖዋ አገልጋዮች እንደዚህ በማድረግ በሕይወታቸው ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመወጣት የእርሱን እርዳታ ያገኛሉ።—መዝ. 37:5፤ 118:13, 16
5 ይሖዋ ራሱ “በእግዚአብሔር የሚታመን፣ መታመኛውም እግዚአብሔር የሆነ ሰው ብሩክ ነው” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (ኤር. 17:7) እንግዲያው በምናከናውናቸው ነገሮች ሁሉ በእርሱ እንደምንታመን እናሳይ!—መዝ. 146:5