ክፍል 2—የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን እድገት እንዲያደርጉ መርዳት
ጥናቱን ለመምራት መዘጋጀት
1 መጽሐፍ ቅዱስ በምናስጠናበት ወቅት ውጤታማ በሆነ መንገድ ማስተማር የሚጠናውን ጽሑፍ ከማብራራትና ምዕራፍና ቁጥራቸው ብቻ የተጠቀሱትን ጥቅሶች ከማንበብ የበለጠ ነገርን ይጨምራል። ትምህርቱን የተማሪውን ልብ በሚነካ መንገድ ማቅረብ ይኖርብናል። ይህ ደግሞ የተማሪውን ሁኔታ በአእምሮ ይዞ በሚገባ መዘጋጀትን ይጠይቃል።—ምሳሌ 15:28
2 መዘጋጀት ያለብህ እንዴት ነው? ስለ ተማሪውና ስለሚያስፈልጉት ነገሮች ለይሖዋ በመጸለይ ዝግጅትህን ጀምር። የተማሪውን ልብ መንካት እንድትችል የይሖዋን እርዳታ ጠይቅ። (ቆላ. 1:9, 10) የምዕራፉን ወይም የትምህርቱን ጭብጥ በሚገባ ለመረዳት እንድትችል ጊዜ ወስደህ በርዕሱ፣ በንዑስ ርዕሶቹና በሥዕሎቹ ላይ አሰላስልባቸው። ‘የምዕራፉ ፍሬ ነገር ምንድን ነው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። ይህ በጥናቱ ወቅት በዋና ዋና ነጥቦች ላይ እንድታተኩር ይረዳሃል።
3 የምታጠኑትን ጽሑፍ አንቀጽ በአንቀጽ በጥንቃቄ ተዘጋጅ። የጥያቄዎቹን መልሶች ፈልገህ ካገኘህ በኋላ ቁልፍ በሆኑት ቃላትና ሐረጎች ላይ ብቻ ምልክት አድርግ። ምዕራፍና ቁጥራቸው ብቻ የተሰጡት ጥቅሶች ከአንቀጹ ሐሳብ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ተመልከት። እንዲሁም በጥናቱ ወቅት የምታነቧቸውን ጥቅሶች ምረጥ። በጽሑፉ ኅዳግ ላይ ጥቅሶቹን በሚመለከት አጠር ያሉ ማስታወሻዎችን መጻፍ ትችላለህ። ተማሪው እየተማረ ያለው ከአምላክ ቃል መሆኑ ግልጽ ሊሆንለት ይገባል።—1 ተሰ. 2:13
4 ትምህርቱን ለተማሪህ እንደሚስማማ አድርገህ አቅርበው፦ ከዚህ በመቀጠል ተማሪህን በአእምሮህ ይዘህ ትምህርቱን በድጋሚ ከልሰው። ጥያቄ ሊያነሳባቸው የሚችላቸውን ነጥቦችና ለመረዳት ወይም ለመቀበል ሊከብዱት የሚችሉ ሐሳቦችን አስቀድመህ ለመገመት ሞክር። ‘መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ እንዲችል ሊያስተውለው የሚገባው ነጥብ ወይም ማሻሻል ያለበት ጉዳይ ምንድን ነው? ልቡን መንካት የምችለው እንዴት ነው?’ በማለት ራስህን ጠይቅ። ከዚያም በዚህ መሠረት ትምህርቱን እንደሚስማማ አድርገህ አቅርበው። አንዳንድ ጊዜ ተማሪህ አንድን ነጥብ ወይም ጥቅስ በሚገባ ለማስተዋል እንዲችል ለመርዳት ምሳሌ፣ ማብራሪያ ወይም የተለያዩ ጥያቄዎችን ማዘጋጀት ያስፈልግህ ይሆናል። (ነህ. 8:8) ይሁን እንጂ ከጭብጡ ጋር ብዙም ተዛምዶ የሌለውን ተጨማሪ ሐሳብ ከመጨመር ተቆጠብ። በጥናቱ መጨረሻ ላይ አጭር ክለሳ ማድረግ ተማሪው ዋና ዋና ነጥቦችን ለማስታወስ ይረዳዋል።
5 አዳዲሶች ይሖዋን የሚያስከብር የጽድቅ ፍሬ ሲያፈሩ ስንመለከት በእጅጉ እንደሰታለን! (ፊልጵ. 1:11) ተማሪዎችህ እዚህ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ለመርዳት ምንጊዜም ጥናት ከመምራትህ በፊት በሚገባ ተዘጋጅ።