ጤናማ ዓይን ይኑራችሁ
1 ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ ምሳሌያዊው ወይም መንፈሳዊው ዓይናችን በሕይወታችን ውስጥ ምን ያህል ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ገልጾ ነበር። እንዲህ ብሏል:- “ዐይንህ ጤናማ ከሆነ መላው ሰውነትህ በብርሃን የተሞላ ይሆናል። ዐይንህ ታማሚ ከሆነ ግን መላው ሰውነትህ በጨለማ የተሞላ ይሆናል።” (ማቴ. 6:22, 23) ጤናማ ዓይን በአንድ ዓላማ ላይ ማለትም የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ላይ ያተኮረ ሲሆን እንደዚህ ያለ እይታ ያለው ሰው ስለ ቁሳዊ ነገሮች ከመጠን በላይ በመጨነቅ ትኩረቱ አይሰረቅም። (ማቴ. 6:19-21, 24-33) ጤናማ ዓይን እንዲኖረን ምን ሊረዳን ይችላል?
2 ባለን መርካትን መማር፦ ሁላችንም ለቤተሰባችን የሚያስፈልጉትን ነገሮች የማሟላት ቅዱስ ጽሑፋዊ ግዴታ አለብን። (1 ጢሞ. 5:8) ይህ ሲባል ግን ምርጥና ዘመናዊ የሆኑ ነገሮችን ለማግኘት ስንል ማቆሚያ የሌለው ጥሮሽ እናደርጋለን ማለት አይደለም። (ምሳሌ 27:20፤ 30:8, 9) ከዚህ በተቃራኒ መጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ የሆኑትን ነገሮች ማለትም “ምግብና ልብስ” ካገኘን በዚያ ረክተን እንድንኖር ያሳስበናል። (1 ጢሞ. 6:8፤ ዕብ.13:5, 6) ይህንን ምክር መስማታችን ዓይናችን በተገቢው ነገር ላይ ያተኮረ እንዲሆን ይረዳናል።
3 አላስፈላጊ በሆነ ዕዳ ውስጥ በመዘፈቅ፣ ብዙ ጊዜና ትኩረት የሚሹ ንብረቶች በመሰብሰብ ወይም እንደዚህ በመሳሰሉ ሌሎች እንቅስቃሴዎች በመጠመድ በራሳችን ላይ ሸክም ላለመጫን መጠንቀቃችን ጥበብ ነው። (1 ጢሞ. 6:9, 10) ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? አንድ እርምጃ ለመውሰድ ስናስብ ስለ ጉዳዩ አጥብቀን መጸለይ እንዲሁም ከመንፈሳዊ ግቦቻችን ጋር ይጋጭ እንደሆነ ለማወቅ ሁኔታውን በሐቀኝነት መመርመር ይኖርብናል። በሕይወታችን ውስጥ ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ ለመስጠት ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።—ፊልጵ. 1:10፤ 4:6, 7
4 አኗኗራችንን ቀላል ማድረግ፦ ትኩረታችን በቁሳዊ ነገሮች እንዳይሰረቅ መከላከል የምንችልበት ሌላው መንገድ አኗኗራችንን ቀላል ማድረግ ነው። ብዙ ቁሳዊ ነገሮች ባይኖሯቸውም ቤተሰቡ ጥሩ ኑሮ መምራት እንደሚችል የተመለከተ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል:- “አሁን ወንድሞቼን ለማገልገል በጉባኤ ውስጥ ብዙ መሥራት እችላለሁ። ይሖዋ እውነተኛውን አምልኮ ከግል ፍላጎታቸው የሚያስቀድሙ አገልጋዮቹን በሙሉ እንደሚባርካቸው እምነት አድሮብኛል።” ተጨማሪ በረከቶች ለማግኘት አኗኗራችሁን ቀለል ማድረግ ትችሉ ይሆን?
5 ሰይጣን፣ በፍቅረ ነዋይ የተጠመደው ዓለምና ኃጢአተኛው ሥጋችን የሚያሳድሩብንን ተጽዕኖ ለመቋቋም የማያቋርጥ ትግል ይጠይቃል። ስለዚህ ትኩረታችን በተለያዩ ነገሮች እንዳይሰረቅ በመጠንቀቅ ዓይናችን ውድ በሆነው የዘላለም ሕይወት ተስፋችንና የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ላይ እንዲያተኩር እናድርግ።—ምሳሌ 4:25፤ 2 ቆሮ. 4:18
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
1. ጤናማ ዓይን ምን ዓይነት ነው? እይታችን ጤናማ እንዲሆን ማድረጋችን አስፈላጊ የሆነውስ ለምንድን ነው?
2. የአምላክ ቃል ለቁሳዊ ነገሮች እንዴት ያለ አመለካከት እንዲኖረን ያበረታታል?
3. በራሳችን ላይ ሸክም እንዳናበዛ ምን ሊረዳን ይችላል?
4. አኗኗራችንን ቀላል ለማድረግ የሚያስችሉ መንገዶችን መፈለግ ያለብን ለምንድን ነው?
5. ጤናማ ዓይን እንዲኖረን ማድረግ የማያቋርጥ ትግል የሚጠይቀው ለምንድን ነው?