የበኩልህን እርዳታ ማበርከት ትችላለህ
1 “እኛን ለመርዳት ለምታደርጉት ጥረት ከልብ እናመሰግናችኋለን። የእናንተ እርዳታ በእርግጥ ያስፈልገናል።” ይህ ምስጋና በመካከላችን ላሉት ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች ያለንን አድናቆት ግሩም አድርጎ ይገልጸዋል። የአምላክ ድርጅት እያደገ በሄደ መጠን በዓለም ዙሪያ ወደ 100,000 በሚጠጉት ጉባኤዎች ውስጥ የሚያገለግሉ የጎለመሱ ወንድሞች ይበልጥ ያስፈልጋሉ። አንተም የተጠመቅክ ወንድም ከሆንክ በዚህ ረገድ የበኩልህን እርዳታ ማበርከት ትችላለህ።
2 ብቃቱን ማሟላት:- ለተጨማሪ የአገልግሎት መብቶች ብቃቱን ማሟላት የምትችለው እንዴት ነው? (1 ጢሞ. 3:1) በዋነኝነት በሁሉም የሕይወት ዘርፎች ጥሩ ምሳሌ በመሆን ነው። (1 ጢሞ. 4:12፤ ቲቶ 2:6-8፤ 1 ጴጥ. 5:3) በስብከቱ ሥራ የተሟላ ተሳትፎ ይኑርህ፤ ሌሎችም እንዲህ እንዲያደርጉ እርዳ። (2 ጢሞ. 4:5) ለእምነት አጋሮችህ ደኅንነት ከልብ የምታስብ ሁን። (ሮሜ 12:13) የአምላክን ቃል በትጋት አጥና፤ እንዲሁም የማስተማር ችሎታህን አዳብር። (ቲቶ 1:9፤ 1 ጢሞ. 4:13) ሽማግሌዎች የሚሰጡህን ኃላፊነት በትጋት ተወጣ። (1 ጢሞ. 3:10) የቤተሰብ ራስ ከሆንክ ደግሞ ‘ቤተሰብህን በአግባቡ አስተዳድር።’—1 ጢሞ. 3:4, 5, 12
3 በጉባኤ ውስጥ በኃላፊነት ቦታ ላይ ማገልገል ትጉ መሆንንና የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስን ይጠይቃል። (1 ጢሞ. 5:17) ስለዚህ ይህን ግብ ስታወጣ በዋነኝነት ሌሎችን በትሕትና የማገልገል ፍላጎት ይኑርህ። (ማቴ. 20:25-28፤ ዮሐ. 13:3-5, 12-17) ጢሞቴዎስ በነበሩት ባሕርያት ላይ አሰላስል፤ እንዲሁም እርሱን ለመኮረጅ ጥረት አድርግ። (ፊልጵ. 2:20-22) አንተም እንደ እርሱ ለተጨማሪ ኃላፊነት የሚያበቃ መልካም ስም ይኑርህ። (ሥራ 16:1, 2) ተጨማሪ ኃላፊነቶችን ለመሸከም የሚያስፈልጉትን መንፈሳዊ ባሕርያት እያዳበርክ ስትሄድና ማሻሻያዎችን እንድታደርግ የሚሰጥህን ምክር በሥራ ላይ ስታውል ‘ማደግህ በሰው ሁሉ ዘንድ’ ይታያል።—1 ጢሞ. 4:15
4 ወላጆች ወጣት ልጆቻችሁን እርዳታ እንዲያበረክቱ አሠልጥኗቸው:- ልጆች ከለጋነታቸው አንስቶ እርዳታ ለማበርከት ራሳቸውን ማቅረብን መማር ይችላሉ። በስብሰባዎች ላይ በትኩረት እንዲያዳምጡ፣ በስብከቱ ሥራ እንዲካፈሉና በመንግሥት አዳራሽም ሆነ በትምህርት ቤት ምሳሌ የሚሆን ምግባር እንዲኖራቸው አሠልጥኗቸው። ሌሎችን መርዳት በሚችሉባቸው ተግባራት ማለትም የመንግሥት አዳራሹን በማጽዳት፣ አረጋውያንን በመርዳትና በመሳሰሉት ሥራዎች እንዲካፈሉ አበረታቷቸው። በመስጠት የሚገኘውን ደስታ እንዲቀምሱ አድርጉ። (ሥራ 20:35) እንዲህ ያለው ሥልጠና ወደፊት ለአቅኚነት፣ ለጉባኤ አገልጋይነትና ለሽማግሌነት ብቁ እንዲሆኑ ሊረዳቸው ይችላል።