የናሙና አቀራረቦችን እንዴት ልንጠቀምባቸው ይገባል?
1. ለናሙናነት የሚቀርቡልንን አቀራረቦች እንዴት ልንጠቀምባቸው ይገባል?
1 መጽሔቶቻችንንና ሌሎች ጽሑፎችን ለማበርከት የሚያስችሉ የናሙና አቀራረቦች በመንግሥት አገልግሎታችን ላይ በየጊዜው ይወጣሉ። በአገልግሎት ላይ እነዚህን የናሙና አቀራረቦች ሸምድደን ይዘን ቃል በቃል መድገም አያስፈልገንም። አቀራረቦቹ የሚወጡት ምን ማለት እንደምንችል ፍንጭ ለመስጠት ነው። አብዛኛውን ጊዜ አቀራረቦቹን በራሳችን አባባል ብንናገራቸው ይበልጥ ውጤታማ እንሆናለን። ሐሳባችንን ከወትሮው ባልተለየ መልኩ የምንገልጽ ከሆነ የምናነጋግራቸው ሰዎች ዘና ብለው የሚያዳምጡን ከመሆኑም በላይ ከልባችን የምናምንበትን ነገር እንደምንናገር ያሳያል።—2 ቆሮ. 2:17፤ 1 ተሰ. 1:5
2. መግቢያዎችን ስንዘጋጅ የአካባቢውን ልማድ ግምት ውስጥ ማስገባት ያለብን ለምንድን ነው?
2 መግቢያህን እንደ ሁኔታው አስተካክል:- የአካባቢው ልማድ ምሥራቹን በምንናገርበት መንገድ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አለው። ከቤቱ ባለቤት ጋር ሰላምታ ከተለዋወጥህ በኋላ ስለተለያዩ ነገሮች በማንሳት ቀስ በቀስ የውይይታችሁን አቅጣጫ ወደ ምሥራቹ ማዞር ትችላለህ? ወይስ በአካባቢያችሁ ሰዎች የመጣህበትን ጉዳይ በቀጥታ እንድትናገር ይፈልጋሉ? ይህ ከቦታ ወደ ቦታ አንዳንድ ጊዜም ከሰው ወደ ሰው ይለያያል። ከዚህም በላይ ጥያቄዎችን ስንጠቀም ጠንቃቃ መሆን አለብን። ለአንዳንድ አካባቢዎች ተስማሚ ናቸው የሚባሉ ጥያቄዎች በሌሎች ቦታዎች ግን ሰዎችን እንዲያፍሩና እንዲሳቀቁ ሊያደርጓቸው ይችላሉ። በመሆኑም የማመዛዘን ችሎታችንን በመጠቀም አቀራረባችንን እንደ አካባቢው ሁኔታ ማስተካከል አለብን።
3. የምናነጋግራቸውን ሰዎች ሁኔታና አስተሳሰብ ከግምት ማስገባት ያለብን ለምንድን ነው?
3 በተጨማሪም ለመስክ አገልግሎት ስንዘጋጅ በክልላችን ውስጥ ያሉትን ሰዎች ሁኔታና አስተሳሰብ ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብናል። ለምሳሌ ያህል ማቴዎስ 6:9, 10ን በሚመለከት ለአንድ ቀናዒ የካቶሊክ እምነት ተከታይ የምትሰጠው ማብራሪያ “አቡነ ዘበሰማያት” ስለሚባለው ጸሎት ጨርሶ ሰምቶ ለማያውቅ ሰው ከምትሰጠው ማብራሪያ ይለያል። አስቀድመን ካሰብንበት አብዛኛውን ጊዜ መግቢያዎቻችን በአገልግሎት የምናገኛቸውን ሰዎች ትኩረት እንዲስቡ አድርገን ማቀናጀት እንችላለን።—1 ቆሮ. 9:20-23
4. ጥሩ ዝግጅት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
4 ለናሙና የሚቀርቡትን የመግቢያ ሐሳቦች ብዙም ሳንለውጣቸው በቀጥታ ወስደን ለመጠቀም ከወሰንንም አስቀድመን ጥሩ ዝግጅት ማድረጋችን አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። ልናበረክተው ካሰብነው ጽሑፍ ላይ አንድ ርዕስ ወይም ምዕራፍ በማንበብ የሰዎችን ትኩረት ሊስቡ የሚችሉ ነጥቦች መፈለግ አለብን። ከዚያም እነዚህን ነጥቦች በመግቢያችን ውስጥ እናካታቸው። ልናበረክተው ያሰብነውን ጽሑፍ በግለት ልናስተዋውቀው የምንችለው ስለ ይዘቱ በቂ ግንዛቤ ሲኖረን ብቻ ነው።
5. በመንግሥት አገልግሎታችን ላይ ከሚወጣው የተለየ አቀራረብ መዘጋጀት የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? እንዴትስ መዘጋጀት እንችላለን?
5 አማራጭ አቀራረቦች:- በአገልግሎታችን ላይ መጠቀም የሚኖርብን ለናሙና የቀረቡትን መግቢያዎች ብቻ ነው? አይደለም። በይበልጥ የሚቀላችሁ ሌላ አቀራረብ ወይም ጥቅስ ካለ በእርሱ ተጠቀሙ። በተለይ መጽሔቶችን ስናበረክት በሽፋኑ ላይ ካለው ርዕስ ውጪ ለክልላችን ተስማሚ የሆኑ ሌሎች በመጽሔቱ ውስጥ የወጡ ርዕሶችን ለመጠቀም ንቁ መሆን ይኖርብናል። በአገልግሎት ስብሰባ ላይ በመስክ አገልግሎት የምንጠቀምባቸው አቀራረቦች በሠርቶ ማሳያ በሚቀርቡበት ወቅት ለጉባኤው የአገልግሎት ክልል ተስማሚ የሆነ ማንኛውንም አቀራረብ መጠቀም ይቻላል። ይህም ሁላችንም ምሥራቹን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመናገር እንድንችል ይረዳናል።