ስለ እውነት የሚመሠክሩ መጽሔቶችን አበርክቱ
1. መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች የሚጫወቱት ሚና ምንድን ነው?
1 የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! የተባሉት መጽሔቶች በመንግሥቱ ስብከትና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ግንባር ቀደሙን ስፍራ እንደያዙ ናቸው። (ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20) በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች ስንካፈል እነዚህን ሁለት ወቅታዊ መጽሔቶች ዘወትር በማበርከት ደስታ እናገኛለን።
2. በመጠበቂያ ግንብ እና በንቁ! መጽሔቶች ላይ ምን ዓይነት ለውጦች ተደርገዋል? ለምንስ?
2 ባለፉት ዓመታት በመጽሔቶቹ መጠንና ይዘት እንዲሁም ለማሰራጨት በምንጠቀምባቸው ዘዴዎች ላይ ለውጦች ተደርገዋል። የእነዚህ ለውጦች ዓላማ መጽሔቶቹ ይበልጥ ማራኪና ውጤታማ እንዲሆኑ ማድረግ ሲሆን ይህም የመንግሥቱ መልእክት የሁሉንም ዓይነት ሰዎች ልብ በመንካት ‘ወደ መዳንና እውነትን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ’ ያስችላል።—1 ጢሞ. 2:4
3. መጽሔቶቹን በአገልግሎት ላይ የምንጠቀምባቸው እንዴት ነው?
3 ከጥር 2006 ጀምሮ ወርኃዊ የሆነውን የንቁ! መጽሔት አንድ እትም ለማበርከት የተለያዩ መግቢያዎችን በመጠቀም ረገድ ጥሩ ልምድ አዳብረናል። አሁን ደግሞ ከሁለቱ ወርኃዊ የመጠበቂያ ግንብ እትሞች መካከል አንዱን በመስክ አገልግሎት ላይ ለማበርከት ተመሳሳይ ዘዴ እንጠቀማለን። እያንዳንዱን መጽሔት ለማበርከት የሚያስችሉ የናሙና አቀራረቦች በመንግሥት አገልግሎታችን የመጨረሻ ገጽ ላይ ይወጣሉ። እነዚህ አቀራረቦች አብዛኛውን ጊዜ በመጽሔቱ መጀመሪያ አካባቢ ላይ ከሚገኙት ርዕሶች መካከል አንዱን ለማስተዋወቅ የሚረዱ ይሆናሉ፤ ሆኖም አልፎ አልፎ የብዙ ሰዎችን ትኩረት የሚስቡ ሌሎች ርዕሶችን የሚያስተዋውቁ የመግቢያ ሐሳቦችም ይወጣሉ። በመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የሚወጡ የመግቢያ ሐሳቦችን ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም የምንችለው የምናስተዋውቀውን ጽሑፍ በደንብ ካነበብነውና ለክልላችን እንደሚስማማ አድርገን በራሳችን አባባል ካቀረብነው ብቻ ነው።
4. በመንግሥት አገልግሎታችን ላይ አንድን እትም ለማበርከት ከሚወጡት መግቢያዎች በተጨማሪ ሌሎች አቀራረቦችን መዘጋጀት አስፈላጊ ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው?
4 ምንም እንኳ የመንግሥት አገልግሎታችን እያንዳንዱን መጽሔት ለማበርከት የሚያስችሉ ሁለት መግቢያዎችን ይዞ የሚወጣ ቢሆንም አንተ ራስህ ያዘጋጀኸውን የተለየ መግቢያ መጠቀም ትችላለህ። እንዲህ የምታደርግበት አንዱ ምክንያት በመጽሔቱ ውስጥ ካሉት ርዕሰ ጉዳዮች መካከል አንዱ በክልልህ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ሰዎችን ትኩረት ስለሚስብ ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ አንተ በጣም የወደድከውን ርዕስ ጥሩ አድርገህ ማስተዋወቅ እንደምትችል ስለተሰማህ ይሆናል።
5. ለምታበረክተው መጽሔት መግቢያ ከማዘጋጀትህ በፊት ምን ማድረግ ይኖርብሃል?
5 መግቢያ ማዘጋጀት የምትችለው እንዴት ነው? ከሁሉ በፊት፣ ለማስተዋወቅ የመረጥከውን ርዕስ በሚገባ ልታነበው ያስፈልጋል። መጽሔቱን በመስክ አገልግሎት ላይ ማበርከት ከመጀመርህ በፊት ሁልጊዜ ሁሉንም ርዕሰ ትምህርቶች አንብበህ ትጨርሳቸዋለህ ማለት አይደለም። ሆኖም የመረጥካቸውን ርዕሶች ስታስተዋውቅ በግለት እንዲሁም ከልብ በመነጨ ስሜት መናገር ይኖርብሃል። ይህን ማድረግ የምትችለው ልታስተዋውቀው ባሰብከው ርዕሰ ትምህርት ውስጥ የሰፈሩትን ሐሳቦች በደንብ ስታውቃቸው ብቻ ነው።
6. የራሳችንን መግቢያ ማዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው?
6 በሁለተኛ ደረጃ፣ መግቢያህን ስትዘጋጅ እንደ ሁኔታው ለውጥ ለማድረግ ፈቃደኛ ሁን። ከምታስተዋውቀው ርዕስ ጋር ተዛማጅነት ያለውና የሰዎችን የማወቅ ፍላጎት የሚቀሰቅስ ጥያቄ በመጠየቅ ውይይት መጀመር ትችላለህ። የሰዎችን ልብ መንካት እንድትችል የምትናገረው ሐሳብ ከፍተኛ ኃይል ባለው የአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ ይሁን። (ዕብ. 4:12) ከምታስተዋውቀው ርዕሰ ጉዳይ ጋር የሚዛመድ አንድ ተስማሚ ጥቅስ ምረጥ። ጥቅሱ ለማስተዋወቅ በመረጥከው ርዕሰ ትምህርት ውስጥ የተጠቀሰ ቢሆን ይመረጣል። ጥቅሱን ከርዕሱ ጋር እንዴት ልታዛምደው እንደምትችል አስብ።
7. በመግቢያዎቻችን ላይ ይበልጥ ማሻሻያ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
7 የተገኘውን አጋጣሚ ሁሉ ተጠቀም:- አንድ መግቢያ በእርግጥ ውጤታማ እንዲሆን ከተፈለገ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ልንጠቀምበት ያስፈልጋል። ጉባኤው ቅዳሜ ቅዳሜ በሚያደርገው የመጽሔት ዘመቻ ላይ ተካፈል። መጽሔቶቹን ቀደም ሲል ሌሎች ጽሑፎችን ወስደው ለነበሩ ሰዎች አበርክትላቸው። ምንጊዜም መጽሔቶችን ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችህና ተመላልሶ መጠየቅ ስታደርግ በዚያ ለምታገኛቸው ሌሎች ሰዎች ለማበርከት ጥረት አድርግ። ገበያ ስትወጣ፣ በጉዞ ላይ ስትሆን ወይም ሐኪም ቤት ወረፋ ስትጠብቅ ለምታገኛቸው ሰዎች መጽሔቶችን ልታበረክትላቸው ትችላለህ። መግቢያዎቹን ወሩን ሙሉ ስትጠቀምባቸው በየጊዜው ማሻሻያዎችን ልታደርግባቸው ትችላለህ።
8. መጠበቂያ ግንብን እና ንቁ! መጽሔትን በዓይነታቸው ልዩ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው?
8 መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች በዓይነታቸው ልዩ ናቸው። ይሖዋ የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ መሆኑን ያስታውቃሉ። (ሥራ 4:24) ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረውን ምሥራች ስለያዙ፣ ሰዎችን ያጽናናሉ እንዲሁም ሰዎች በኢየሱስ ላይ እምነት እንዲያሳድሩ ያበረታታሉ። (ማቴ. 24:14፤ ሥራ 10:43) በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ የሆኑትን የዓለም ሁኔታዎች ትኩረት ሰጥተው ይከታተላሉ። (ማቴ. 25:13) አመቺ በሆነው አጋጣሚ ሁሉ ለማበርከት ዝግጁ በመሆን በክልልህ ውስጥ የሚገኙት ሰዎች ከእነዚህ መጽሔቶች እንዲጠቀሙ እርዳቸው!
9. ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ የሚያስችል መሠረት መጣል የምትችለው እንዴት ነው?
9 መጽሔት በማበርከት ረገድ ተሳክቶልህ አሊያም ከአንድ ሰው ጋር መንፈሳዊ ውይይት ብቻ አድርገህ ሊሆን ይችላል። በዚህ ጊዜ ለተመላልሶ መጠየቅና ተጨማሪ መንፈሳዊ ውይይት ለማድረግ መንገድ ለመክፈት የሚያስችል አንድ ጥያቄ ወይም አእምሮን የሚያመራምር አንድ ሐሳብ ለመናገር ዝግጁ ሁን። የእውነትን ዘር በመዝራት ረገድ ቀናተኞች ከሆንን፤ ይሖዋ እሱን ከልብ ለማወቅና ለማገልገል የሚፈልጉ ሰዎችን ልብ እንደሚከፍት እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—1 ቆሮ. 3:6