የመታሰቢያው በዓል ሰሞን—የአገልግሎት እንቅስቃሴያችንን ከፍ የምናደርግበት ወቅት
1. በየዓመቱ ይከበሩ የነበሩ “የተመረጡ የእግዚአብሔር በዓላት” ፈሪሃ አምላክ በነበራቸው እስራኤላውያን ላይ ምን በጎ ተጽዕኖ አሳድረዋል?
1 የጥንቶቹ እስራኤላውያን በዓመቱ በተወሰኑ ጊዜያት ‘የተመረጡ የእግዚአብሔር በዓላትን’ ያከብሩ ነበር። (ዘሌ. 23:2) ስለ አምላካቸው ጥሩነት ማሰላሰል የሚችሉበት ጊዜ ማግኘታቸው ደስታቸው እንዲጨምር ከማድረጉም በላይ ለንጹሕ አምልኮ ቀናተኛ እንዲሆኑ አነሳስቷቸዋል።—2 ዜና 30:21 እስከ 31:2
2, 3. በመታሰቢያው በዓል ሰሞን መንፈሳዊ እንቅስቃሴያችንን ከፍ ማድረጋችን ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው? የመታሰቢያው በዓል የሚከበረውስ መቼ ነው?
2 በዘመናችንም በየዓመቱ በመታሰቢያው በዓል ሰሞን አስደሳች የሆነው ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴያችን ከምንጊዜውም ይበልጥ ይጧጧፋል። ይሖዋ ስለሰጠን በዋጋ ሊተመን የማይችል ስጦታ ይበልጥ የምናሰላስልበት ጊዜ ነው። ይህ ውድ ስጦታ አንድያ ልጁ ነው። (ዮሐ. 3:16፤ 1 ጴጥ. 1:18, 19) ይሖዋ አምላክና ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ስላሳዩን ፍቅር ካሰላሰልን ይሖዋን ለማመስገንና ፈቃዱንም ለማድረግ እንነሳሳለን።—2 ቆሮ. 5:14, 15
3 በዚህ ዓመት የመታሰቢያው በዓል የሚከበረው መጋቢት 24 ሐሙስ ዕለት ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ነው። ክልላችንን ለመሸፈን ልዩ ዘመቻ በምናደርግበት በመጋቢት፣ በሚያዝያና በግንቦት ወር ላይ የአገልግሎት እንቅስቃሴያችንን ከፍ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
4, 5. (ሀ) አንዳንዶች ምሥራቹን ለብዙ ሰዎች እንዲያዳርሱ የረዳቸው ምንድን ነው? (ለ) በአካባቢህ ውጤታማ ሆኖ ያገኘኸው ዘዴ የትኛው ነው?
4 ብዙ ሰዎችን ማነጋገር:- በመስክ አገልግሎት በምትሳተፍበት ጊዜ ለብዙ ሰዎች ለመስበክ የምትችለውን ሁሉ አድርግ። በዚህ የአገልግሎት ዓመት ያልተሸፈኑ ክልሎችን ለመሸፈን ፕሮግራም ማውጣት ትችላለህ። አብዛኞቹ ሰዎች ቤት ሊገኙ በሚችሉበት ጊዜ፣ ለምሳሌ ያህል ከሰዓት በኋላ ወይም ወደ አመሻሹ ላይ ከቤት ወደ ቤት ለማገልገል ዕቅድ ማውጣት ትችል ይሆን? ከመጽሐፍ ጥናት ቡድናችሁ አባላት መካከል አንዳንዶቹ ከመጽሐፍ ጥናት ስብሰባው በፊት ጥቂት ማገልገል ከፈለጉ የመጽሐፍ ጥናቱ የበላይ ተመልካች በመጽሐፍ ጥናቱ አቅራቢያ በሚገኝ የአገልግሎት ክልል መስራት እንዲችሉ አጭር የስምሪት ስብሰባ እንዲኖር ዝግጅት ማድረግ ይችል ይሆናል።
5 ብዙ ሰዎችን ማነጋገር የሚቻልበት ሌላው መንገድ ሰዎች በብዛት በሚገኙባቸው ቦታዎች መመስከር ነው። በጃፓን የምትኖር አንዲት እህት ምንም እንኳን ሙሉ ቀን ሰብዓዊ ሥራ የምትሠራ ብትሆንም ረዳት አቅኚ ሆና ማገልገል ፈለገች። በየዕለቱ ወደ ሥራ ከመሄዷ በፊት በአንድ ባቡር ጣቢያ አካባቢ እንድታገለግል አንድ ሽማግሌ አበረታታት። ዘወትር በባቡር ከሚመላለሱ ሰዎች የሚሰነዘርባትን ፌዝና የራሷን ፍርሃት ካሸነፈች በኋላ 40 የሚያክሉ የመጽሔት ደንበኞችን ያገኘች ሲሆን ከእነሱ ውስጥ ዘወትር በባቡር የሚመላለሱ፣ በባቡር ጣቢያው የሚሰሩና በአቅራቢያው የሚገኙ ባለ ሱቆች ይገኙበታል። በወር ውስጥ በአማካይ 235 መጽሔቶችን ለማበርከት ችላለች። በየቀኑ ለጥቂት ደቂቃዎች አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳቦችን ለሰዎች በመንገር ስድስት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ማግኘት ችላለች።
6. ወጣቶች መንፈሳዊ እንቅስቃሴያቸውን ከፍ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?
6 ለመመሥከር የሚያስችሉ አጋጣሚዎች:- ተማሪ የሆኑ አስፋፊዎች በዓመቱ ውስጥ ትምህርት ቤት ለዕረፍት ሲዘጋ ረዳት አቅኚ ሆነው ለማገልገል ጥሩ አጋጣሚ ይኖራቸዋል። በተጨማሪም ክርስቲያን ወጣቶች በትምህርት ቤት ውስጥ በመመሥከር የአገልግሎት እንቅስቃሴያቸውን ከፍ ማድረግ ይችላሉ። ምናልባት የክፍል ጓደኞችህ ስለ እምነትህ ለማወቅ ያላቸውን ጉጉት ስታይ ትደነቅ ይሆናል። የክፍል ውስጥ ውይይቶችን ወይም በትምህርት ቤት ጽሑፍ የማቅረብ አጋጣሚዎችን ለምን ለመመስከር አትጠቀምባቸውም? አንዳንዶች የቪዲዮ ፊልሞቻችንን ለመመሥከር ተጠቅመውባቸዋል። ሌሎች ደግሞ የክፍል ጓደኞቻቸውን መጽሐፍ ቅዱስ በማስጠናት ራሳቸውን ወስነው እንዲጠመቁ ረድተዋል። እነዚህ ‘የይሖዋን ስም ማመስገን’ የምንችልባቸው ግሩም አጋጣሚዎች ናቸው።—መዝ. 148:12, 13
7. (ሀ) አንድ ወንድም ለሌሎች ለመመሥከር አጋጣሚዎቹን የተጠቀመባቸው እንዴት ነው? (ለ) አንተስ እንዲህ ዓይነት ተሞክሮ አጋጥሞሃል?
7 በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴህ ድንቅ ስለሆነው አምላካችንና ግሩም ስለሆኑት ተስፋዎቹ ለሰዎች ለመናገር የተለያዩ መንገዶችን ፈልግ። በየቀኑ ተመሳሳይ ባቡር የሚጠቀም አንድ ወንድም አብረውት ለሚጓዙት ሰዎች የሚመች ሁኔታ ፈልጎ ይመሠክርላቸው ነበር። ለምሳሌ በአንደኛው ባቡር ጣቢያ የሚቀጥለውን ባቡር በሚጠብቅበት ጊዜ ለአንድ ወጣት በየቀኑ ለአምስት ደቂቃ ያህል ይመሠክርለት ነበር። ከዚህም የተነሳ ይህ ወጣትና የሥራ ባልደረባው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር ተስማሙ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ ይካሄድ የነበረው እዚያው ባቡሩ ላይ አብረው እየተጓዙ ነበር። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ውይይታቸውን ያዳምጡ የነበሩ አንዲት አረጋዊት ወንድምን ጠጋ ብለው መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት እንደሚፈልጉ ነገሩት። እኚህ አረጋዊትም በባቡሩ በተሳፈሩ ቁጥር ጥናታቸውን ያጠናሉ። በዚህ መንገድ ወንድም በባቡር በሚጓዝበት ጊዜ አሥር የተለያዩ ሰዎችን ለማስጠናት ችሏል።
8. በዕድሜ መግፋት ወይም በጤና እክል ምክንያት የአቅም ገደብ ያለባቸው አገልግሎታቸውን ከፍ ለማድረግ የትኛውን ዘዴ ሊጠቀሙ ይችላሉ?
8 በዕድሜ መግፋት ወይም በጤንነት እክል ምክንያት ልታደርግ የምትችላቸው ነገሮች በጣም ውስን ቢሆኑስ? አሁንም ቢሆን ለይሖዋ የምታቀርበውን ምስጋና ከፍ የምታደርግባቸው መንገዶች ሊኖሩ ይችላሉ። የስልክ ምሥክርነት ሞክረህ ታውቃለህ? ይህንን ማከናወን የሚቸግርህ ከሆነ ለመጽሐፍ ጥናት የበላይ ተመልካችህ ንገረው። ምናልባት ይህን ዘዴ ከሚጠቀሙበት ሌሎች አስፋፊዎች ጋር የምታገለግልበትን መንገድ ሊያመቻችልህ ይችላል። አንድ ላይ አብራችሁ መስራታችሁ አንዳችሁ ከሌላው የመማር አጋጣሚ የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ እርስ በርሳችሁ ለመረዳዳትና ውጤታማ ምሥክርነት ለመስጠት ያስችላችኋል። የስልክ ምሥክርነት ለመስጠት የሚያስችሉ አንዳንድ ውጤታማ ሐሳቦችን ከነሐሴ 1993 የመንግሥት አገልግሎታችን ገጽ 3 ላይ ማግኘት ይቻላል።
9. አዲሶችን ከጉባኤው ጋር ሆነው በአገልግሎት መካፈል እንዲችሉ እንዴት ልንረዳቸው እንችላለን?
9 አዲሶች በመታሰቢያው በዓል ላይ መገኘታቸው ለይሖዋ የሚያቀርቡትን ውዳሴ ከፍ ለማድረግ ያነሳሳቸው ይሆናል። መደበኛ በሆነ መንገድ የስብከቱን ሥራ ለመጀመር ያላቸውን ማንኛውንም ፍርሃት ለማሸነፍ እንዲያስችሏቸው የሚያበረታቱ ተሞክሮዎችን ልታካፍላቸው እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን እንዴት ብለው ማስረዳትና ስለ እምነታቸው ለሚጠየቁት ጥያቄ ምን ብለው መልስ መስጠት እንደሚችሉ ደረጃ በደረጃ ልታሰለጥናቸው ትችላለህ። (1 ጴጥ. 3:15) የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ አስፋፊ ለመሆን ፍላጎት እንዳለው ከነገረህ ከሰብሳቢ የበላይ ተመልካቹ ጋር ተነጋገር። ከጉባኤው ጋር ሆኖ በአገልግሎት ለመካፈል ብቁ መሆኑን ለማረጋገጥ ሽማግሌዎች እንዲያነጋግሩት ዝግጅት ያደርጋል። አዲሶች አቋም ወስደው ሉዓላዊነቱን በመደገፍ ከጎኑ በሚቆሙበት ጊዜ ይሖዋ ልቡ ምን ያህል እንደሚደሰት መገመት አያዳግትም።—ምሳሌ 27:11
10. (ሀ) ጥሩ ፕሮግራም ማውጣት ረዳት አቅኚ ሆነን ለማገልገል ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) ባለፈው ዓመት በመታሰቢያው በዓል ሰሞን ረዳት አቅኚ ሆነህ ለማገልገል ችለህ ነበር? ከሆነስ እንዴት?
10 ረዳት አቅኚ መሆን ትችላለህ? ከረዳት አቅኚ የሚፈለገው 50 ሰዓት በቁም ነገር ሊታሰብበት የሚገባ ነው። (ማቴ. 5:37) ይህ ማለት በየሳምንቱ በአማካይ 12 ሰዓት ለአገልግሎት ለማዋል ጊዜ መመደብ ይኖርብሃል። በገጽ 5 ላይ የሚገኘው የረዳት አቅኚ የናሙና ፕሮግራም ለአንተ ሁኔታ የሚስማማ ነው? ካልሆነ መጋቢትን፣ ሚያዝያን ወይም ግንቦትን ረዳት አቅኚ ሆነህ ለማገልገል የሚያስችልህን ፕሮግራም ማውጣት ትችላለህ? አገልግሎትህን ከፍ ለማድረግ የምታደርገውን ጥረት እንዲባርክልህ ይሖዋን ለምነው።—ምሳሌ 16:3
11. ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች ረዳት አቅኚ ሆነው የሚያገለግሉትን እንዴት ሊረዷቸው ይችላሉ?
11 በዚህ በመታሰቢያው በዓል ሰሞን ይሖዋን ይበልጥ ለማወደስ በምታደርገው ጥረት የጉባኤ ሽማግሌዎችና አገልጋዮች ሙሉ በሙሉ ይደግፉሃል። በተቻላቸው መጠን አብዛኞቹ ረዳት አቅኚ ይሆናሉ። ሽማግሌዎች በሥራ ቀናት ምሽት ላይ እንዲሁም ቅዳሜና እሑድ እንደ አስፈላጊነቱ ተጨማሪ የስምሪት ስብሰባዎች እንዲኖሩ ዝግጅት ያደርጋሉ። እነዚህ የስምሪት ስብሰባዎች የሚደረጉት መቼና የት እንደሆነ እንዲሁም ማን እንደሚመራቸው ለመወሰን ሽማግሌዎች አቅኚ ለመሆን እቅድ ያወጡትን ወይም ሐሳቡ ያላቸውን ማናገር ይችላሉ። አንተ ለአገልግሎት ብለህ በመደብከው ጊዜ አብረውህ የሚያገለግሉ ሌሎች አስፋፊዎችም እንዲኖሩ ሽማግሌዎች የተቀናጀ ዝግጅት ለማድረግ ጥረት ያደርጋሉ። በዚህ መንገድ አስቀድሞ እቅድ ማውጣት ከተቻለ ጥሩ ውጤት ይገኛል።—ምሳሌ 20:18
12. ይሖዋን ሁልጊዜ ለማወደስ የሚያነሳሳን ምንድን ነው?
12 የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ:- ሁኔታህ ረዳት አቅኚ ለመሆን የማይፈቅድልህ ከሆነ፣ ይሖዋ የምናደርገውን ጥረትና የምንከፍለውን መሥዋዕትነት እንደሚቀበለው እንዲሁም ይሖዋ የሚፈልግብን ‘ባለን መጠን እንጂ በሌለን መጠን እንዳልሆነ’ መዘንጋት የለብህም። (2 ቆሮ. 8:12) ይሖዋን እንድናመሰግን የሚያደርጉን ብዙ ነገሮች አሉን። ዳዊት “እግዚአብሔርን ሁልጊዜ እባርከዋለሁ፤ ምስጋናውም ዘወትር ከአፌ አይለይም” ያለው ያለ ምክንያት አይደለም። (መዝ. 34:1) በዚህ በመታሰቢያው በዓል ሰሞን የእኛም ቁርጥ ውሳኔ ይህ እንዲሆን እንመኛለን።
[ገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
አገልግሎትህን እንዴት ከፍ ማድረግ ትችላለህ?
◼ ያልተሸፈኑ ክልሎችን በመሥራት
◼ ሰዎች ቤታቸው በሚገኙበት ጊዜ በመስበክ
◼ ሰው በሚበዛባቸው አካባቢዎች በማገልገል
◼ በትምህርት ቤት ወይም በሥራ ቦታ በመስበክ
◼ በስልክ ለመመሥከር ጥረት በማድረግ
◼ ረዳት አቅኚ ሆኖ በማገልገል
[ገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በረዳት አቅኚነት ለማገልገል የሚያስችሉ የናሙና ፕሮግራሞች በእያንዳንዱ ሳምንት በመስክ አገልግሎት 12 ሰዓት ለማሳለፍ የሚያስችል ፕሮግራም
ከሰኞ እስከ ቅዳሜ—ጠዋት
ከእነዚህ ቀናት አንዱን በእሑድ መቀየር ይቻላል።
ቀን ክፍለ ጊዜ ሰዓት
ሰኞ ጠዋት 2
ማክሰኞ ጠዋት 2
ረቡዕ ጠዋት 2
ሐሙስ ጠዋት 2
ዓርብ ጠዋት 2
ቅዳሜ ጠዋት 2
ጠቅላላ ሰዓት፦ 12
ሁለት ሙሉ ቀናት
ከሳምንቱ ቀናት መካከል የትኞቹንም ሁለት ቀናት መምረጥ ይቻላል።
(በሳምንቱ ውስጥ በመረጥናቸው ቀናት መሠረት ይህ ፕሮግራም በወር ውስጥ በአጠቃላይ 48 ሰዓት ብቻ ያመጣ ይሆናል።)
ቀን ክፍለ ጊዜ ሰዓት
ረቡዕ ሙሉ ቀን 6
ቅዳሜ ሙሉ ቀን 6
ጠቅላላ ሰዓት፦ 12
ሁለት ምሽቶች እና ቅዳሜና እሑድ
ከሳምንቱ ቀናት መካከል የትኞቹንም ሁለት ምሽቶች መምረጥ ይቻላል።
ቀን ክፍለ ጊዜ ሰዓት
ሰኞ ምሽት 1 1⁄2
ረቡዕ ምሽት 1 1⁄2
ቅዳሜ ሙሉ ቀን 6
እሑድ ግማሽ ቀን 3
ጠቅላላ ሰዓት፦ 12
ሦስት ቀናት ከሰዓት በኋላ እና ቅዳሜ
እሑድን በማንኛውም ቀን መተካት ይቻላል።
ቀን ክፍለ ጊዜ ሰዓት
ሰኞ ከሰዓት በኋላ 2
ረቡዕ ከሰዓት በኋላ 2
ዓርብ ከሰዓት በኋላ 2
ቅዳሜ ሙሉ ቀን 6
ጠቅላላ ሰዓት፦ 12
የራሴ የአገልግሎት ፕሮግራም
በእያንዳንዱ ክፍለ ጊዜ ስንት ሰዓት እንደምታገለግል ወስን።
ቀን ክፍለ ጊዜ ሰዓት
ሰኞ
ማክሰኞ
ረቡዕ
ሐሙስ
ዓርብ
ቅዳሜ
እሑድ
ጠቅላላ ሰዓት፦ 12