ተጨማሪ ምሥክርነት እንዲያገኙ እርዷቸው
1 ምሥራቹን ለሰዎች ስንናገር ብዙውን ጊዜ ከጉባኤያችን ክልል ውጪ የሚኖሩ ወይም የምልክት ቋንቋን ጨምሮ ሌሎች ቋንቋዎችን የሚናገሩ ሰዎች ያጋጥሙናል። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እናወያያቸው የነበሩ አንዳንድ ሰዎችም ወደ ሌላ አካባቢ ተዛውረው ሊሄዱ ይችላሉ። እንደ እነዚህ ያሉ ሰዎች ተጨማሪ ምሥክርነት የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸት የምንችለው እንዴት ነው? እባካችሁ ተከታትላችሁ እርዱት (S-43) የተባለውን ቅጽ በመጠቀም ነው።
2 ብዙውን ጊዜ ሰዎች ምሥራቹ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ሲነገራቸው ይበልጥ ለማዳመጥ ይገፋፋሉ። (ሥራ 22:1, 2) በመሆኑም እኛ የማናውቀውን ቋንቋ የሚናገር ሰው ሲያጋጥመን ግለሰቡ የመንግሥቱን መልእክት ለመስማት ፍላጎት ባያሳይም እንኳን አብዛኛውን ጊዜ ከላይ የተጠቀሰውን ቅጽ መሙላት ይኖርብናል። ይሁን እንጂ በአካባቢው በርካታ የውጪ አገር ቋንቋ ተናጋሪዎች የሚኖሩ ከሆነና በቋንቋቸው በተደጋጋሚ ምሥክርነት የሚሰጣቸው ከሆነ ፍላጎት ያለው ሰው እስካላገኘን ድረስ ቅጹን መሙላት አያስፈልግም።
3 ቅጹን መሙላት:- በዘዴ የግለሰቡን ስም፣ አድራሻውንና የስልክ ቁጥሩን ለማግኘት ሞክር። ግለሰቡ ምን ያህል ፍላጎት እንዳለው፣ ምን ጊዜ ሊገኝ እንደሚችልና የተበረከተለትን ወይም የጠየቀውን ጽሑፍ እንዲሁም በደንብ የሚችለውን ቋንቋ በቅጹ ላይ መዝግብ። ቅጹን ሞልተህ ካጠናቀቅህ በኋላ ጊዜ ሳታጠፋ ለጉባኤያችሁ ጸሐፊ ስጠው። እርሱም ጉዳዩ ለሚመለከተው ጉባኤ ወይም ቡድን ያስተላልፈዋል።
4 ቅጹን ለሚመለከተው ጉባኤ መላክ:- የጉባኤው ጸሐፊ ቅጹን ለየትኛው ጉባኤ ወይም ቡድን መላክ እንዳለበት ካላወቀ ወይም ቅጹ የሚላክለት ጉባኤ ወይም ቡድን አድራሻ ከሌለው በቅርንጫፍ ቢሮው ወደሚገኘው የአገልግሎት ክፍል በመደወል የሚፈልገውን መረጃ መጠየቅ ይችላል። ይህን ጉዳይ በሚመለከት የከተማውን የበላይ ተመልካች መጠየቅ አስፈላጊ አይደለም።
5 አንድ ጉባኤ ወይም ቡድን እባካችሁ ተከታትላችሁ እርዱት የተባለው ቅጽ ተሞልቶ ሲደርሰው ዛሬ ነገ ሳይል ግለሰቡን ፈልጎ ለማግኘት ዝግጅት ማድረግ አለበት። የበኩላችንን ኃላፊነት በትጋት ከተወጣን ይሖዋ ‘ለዘላለም ሕይወት የተዘጋጁትን’ ሰዎች ልብ እንደሚከፍት እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ሥራ 13:48