ይበልጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያተኮረ
1. መጀመሪያ ላይ መጠበቂያ ግንብ በዋነኝነት ይታተም የነበረው ለእነማን ነበር? ወርቃማው ዘመን የተባለው መጽሔትስ?
1 ወርቃማው ዘመን የተባለው መጽሔት የመጀመሪያ እትም የወጣው ጥቅምት 1, 1919 ነበር። ይህ መጽሔት ለስብከቱ ሥራ እጅግ ጠቃሚ መሣሪያ ሆኖ አገልግሏል። ለምን? ምክንያቱም ለማንኛውም ሰው እንዲሆን ታስቦ ይዘጋጅ ስለነበረ ነው። ለብዙ ዓመታት በአብዛኛው ‘ለታናሹ መንጋ’ ተብሎ የሚዘጋጅ መጽሔት እንደሆነ ተደርጎ ይታሰብ የነበረው መጠበቂያ ግንብ ግን የሚዘጋጀው በዚህ መንገድ አልነበረም። (ሉቃስ 12:32 የ1954 ትርጉም) የመንግሥቱ አስፋፊዎች የዚህን አዲስ ጽሑፍ መውጣት በደስታ ስለተቀበሉት ለብዙ ዓመታት ወርቃማው ዘመን የተባለው መጽሔት ስርጭት ከመጠበቂያ ግንብ ስርጭት በእጅጉ ሊበልጥ ችሏል።
2. ወርቃማው ዘመን የተባለው መጽሔት ዛሬ ምን ተብሎ ይጠራል? ይታተም የነበረውስ ለምን ዓላማ ነበር?
2 ወርቃማው ዘመን የተባለው መጽሔት ይታተም የነበረው ለሰው ልጅ ችግሮች ትክክለኛ መፍትሄ ሊያስገኝ የሚችለው ለሰው ዘሮች ወርቃማ የሆነ ዘመን የሚያመጣው የክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት መሆኑን ለማሳወቅ ነበር። ይሁንና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተለወጠ የሚሄደውን ፍላጎት ለማስተናገድ ሲባል በቀጣዮቹ አሥርተ ዓመታት ወርቃማው ዘመን በተባለው መጽሔት ላይ በርካታ ማስተካከያዎች ተደረጉ። በ1937 ስሙ ተለውጦ መጽናኛ ተባለ። በ1946 ደግሞ ንቁ! ተባለ፤ ዛሬ እኛም የምናውቀው በዚህ ስሙ ነው።
3. ንቁ! ለየትኛው ትንቢት ፍጻሜ ጥሩ መሣሪያ ሆኖ አገልግሏል?
3 ይህ መጽሔት ከ1919 ጀምሮ በመካሄድ ላይ ላለው ሰፊ የምሥክርነት ሥራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። (ማቴ. 24:14) ሆኖም ካለንበት ጊዜ አጣዳፊነት አንጻር ሲታይ በንቁ! መጽሔት ላይ ተጨማሪ ማስተካከያዎች ማድረግ አስፈላጊ ይመስላል።
4. (ሀ) አንድ ሰው ‘በይሖዋ ቁጣ ቀን ለመሰወር’ ምን ማድረግ ያስፈልገዋል? (ለ) በራእይ 14:6, 7 ላይ በተገለጸው መሠረት ‘በሰማይ መካከል የሚበረው መልአክ’ ሰዎች ሁሉ ምን እንዲያደርጉ ጥሪ እያቀረበ ነው?
4 ንቁ! ሃይማኖታዊ ያልሆኑ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን ማራኪ በሆነ መንገድ ስለሚያቀርብ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይህን መጽሔት ማንበብ ያስደስታቸዋል። በየዓመቱ በመታሰቢያው በዓል ላይ የሚገኙት አብዛኞቹ ሰዎች አዘውታሪ የንቁ! አንባቢዎች እንደሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁንና አንድ ሰው ‘በይሖዋ ቁጣ ቀን’ መሰወር ከፈለገ ጽሑፎቻችንን አዘውትሮ ከማንበብ የበለጠ ነገር ማድረግ እንዲችል እርዳታ ማግኘት ያስፈልገዋል።—ሶፎ. 2:3፤ ራእይ 14:6, 7
5. (ሀ) ንቁ! መጽሔት ከጥር 2006 እትሙ ጀምሮ ይበልጥ በምን ላይ ያተኮረ ይሆናል? (ለ) ብዙዎች ምን ለማድረግ ሊነሳሱ ይችላሉ? ይህስ የየትኛው ትንቢት ፍጻሜ ነው?
5 ስለሆነም ከጥር 2006 ጀምሮ ንቁ! መጽሔት ይበልጥ በአምላክ መንግሥት ላይ ያተኮረ ይሆናል። ሰዎች ለችግሮቻቸው መፍትሄ ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስን እንዲመረምሩ ይበልጥ ቀጥተኛ በሆነ መንገድ የሚያበረታታ ከመሆኑም በላይ ወቅታዊ ስለሆኑት ሁኔታዎች መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ማብራሪያ ጎላ አድርጎ የሚገልጽ ይሆናል። በዚህ መንገድ አንባቢዎቹ በጊዜያችን ስላሉት ሁኔታዎች የተሻለ ግንዛቤ የሚያገኙ ሲሆን ይህም በይበልጥ ስለ ይሖዋ ለማወቅ ሊያነሳሳቸው ይችላል።—ዘካ. 8:23
6, 7. (ሀ) ንቁ! መጽሔት ብዙዎች 1 ተሰሎንቄ 2:13ን ተግባራዊ እንዲያደርጉ በሚረዳ መልክ የሚዘጋጀው እንዴት ነው? (ለ) ንቁ! ወደፊት በየስንት ጊዜው ይታተማል? ይህስ ለውጥ ምን ያህል ቋንቋዎችን ይነካል?
6 ንቁ! የብዙዎችን ትኩረት የሚስቡ አንዳንድ ርዕሰ ጉዳዮችን መዳሰሱን ይቀጥላል። ይሁን እንጂ ይበልጥ ትኩረት የሚያደርገው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ይሆናል። (1 ተሰ. 2:13) መጠበቂያ ግንብ ጥልቀት ያላቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርቶችን ስለሚያቀርብና ንቁ! መጽሔትም ቅዱስ ጽሑፋዊ ይዘት ያላቸውን ተጨማሪ ትምህርቶች ይዞ ስለሚወጣ ንቁ! መጽሔትን በወር ሁለት ጊዜ ማተም አስፈላጊ አይመስልም። ስለዚህ ንቁ! ከጥር 2006 እትሙ ጀምሮ ወርኀዊ መጽሔት ይሆናል። ይህም ጽሑፎቻችንን በማዘጋጀት፣ በመተርጎምና በመላክ ረገድ ያለውን ሥራ በእጅጉ ያቀለዋል።
7 ይህ ለውጥ ንቁ! ከሚታተምባቸው ቋንቋዎች 40 በመቶ የሚያክሉትን ይነካል። በአብዛኞቹ ቋንቋዎች ቀድሞውንም ቢሆን የሚታተመው በወር አንዴ ወይም በሦስት ወር አንዴ ነው። በመጠበቂያ ግንብ ላይ ግን ምንም ለውጥ አይኖርም።
8. አስፋፊዎች ንቁ! መጽሔትን ከመጠበቂያ ግንብ ጋር እንዴት አድርገው ሊጠቀሙበት ይችላሉ?
8 አስፋፊዎች የእያንዳንዱን ወር ንቁ! መጽሔት በዚያ ወር ከሚታተሙት የመጠበቂያ ግንብ እትሞች ጋር ማበርከት ይችላሉ። ንቁ! የሚያበረክቱ ሁሉ በወሩ አጋማሽ ላይ መግቢያቸውን መለወጥ ሳያስፈልጋቸው ወሩን ሙሉ ያንኑ እትም ማበርከት ይችላሉ።
9. ንቁ! ምን ሚና መጫወቱን ይቀጥላል?
9 ወርቃማው ዘመን፣ መጽናኛ አሁን ደግሞ ንቁ! በመባል የሚጠራው መጽሔት የመጀመሪያ እትሙ ከወጣበት ከ1919 ጀምሮ በስብከቱ ሥራ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። አንዳንድ ማስተካከያዎች ተደርጎበት የሚወጣውን የዚህን መጽሔት ስርጭት ይሖዋ እንዲባርከውና መጽሔቱ “ከሕዝብ፣ ከነገድ፣ ከወገን፣ ከቋንቋም ሁሉ” የተውጣጡ ብዙ ተጨማሪ ሰዎች የሰው ልጆች ብቸኛ ተስፋ ወደ ሆነው ወደ አምላክ መንግሥት እንዲመጡ ይረዳቸው ዘንድ ጸሎታችን ነው።—ራእይ 7:9