በአገልግሎታችን የማናዳላ መሆናችንን ማሳየት
1 ጴጥሮስ ‘እግዚአብሔር ለሰው ፊት አያደላም፤ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ’ ነው ብሏል። (ሥራ 10:34, 35) ዛሬ አገልግሎታችንን የምናከናውነው በግልጽ የተቀመጠውን ይህንን እውነት ሙሉ በሙሉ በመገንዘብ ነው። ስለዚህ ለሰው ሁሉ የምሥራቹን እንዳናድርስ የሚያግደንን ማንኛውንም መሰናክል ለማስወገድ የምንችለውን ሁሉ ማድረጋችን አስፈላጊ ነው።
2 በአንዳንድ አካባቢዎች ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል ጉባኤው የሚጠቀምበትን ቋንቋ የማይረዱ ወይም የማይናገሩ ሰዎችን ማግኘታችን ያልተለመደ አይደለም። ቋንቋ የሚፈጥረው ዕንቅፋት አንዳንድ ሰዎች ከምንሰብከው የመንግሥት መልእክት ሙሉ በሙሉ እንዳይጠቀሙ ያግዳቸዋል። ከእነዚህም መካከል በምልክት ቋንቋ ብቻ የሚግባቡ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ይገኙበታል። ለእነዚህ ሰዎች ምሥራቹን ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዳናዳርስ የሚያግደንን የቋንቋ ዕንቅፋት ለማስወገድ እንዲረዳን ምን ማድረግ ይቻላል?
3 በአገልግሎት ክልልህ ውስጥ መስማት የተሳነው ወይም ጉባኤው የሚናገርበትን ቋንቋ የማይረዳ ሰው ካጋጠመህ ይህንን በማስታወሻህ ላይ ልትጽፍና በጉባኤህ ውስጥ ወይም በሌላ ጉባኤ ውስጥ ያለ ያንን ቋንቋ የሚረዳ ሰው ፈልገህ ተመላልሶ መጠየቁን ለእርሱ ልታስረክበው ትችላለህ። ለመጀመሪያ ጊዜ ተመላልሶ መጠየቅ ሲያደርግለት አብረኸው ብትሄድ ጥሩ ሊሆን ይችላል።
4 አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ማድረግ አስፈላጊ ላይሆን ይችላል። ለምሳሌ በምሥራቅ አፍሪካ ውስጥ ያሉ ጉባኤዎች አንድ የሆነ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች ካሉ እነዚያን ሰዎች ወዴት ሊወስዷቸው እንደሚችሉ ያውቃሉ። ያንን የአገልግሎት ክልል በዚያ አካባቢ በሚነገረው ቋንቋ የሚጠቀም ጉባኤ እንዲይዘው አንዳንድ ጊዜ የአገልግሎት ክልል ድንበሮችን ማስተካከል ሊያስፈልግ ይችላል።
5 በተፈለገው ቋንቋ ምስክርነቱን ለመስጠት የሚችል ጉባኤ ወይም ቡድን በዚያ አካባቢ ከሌለ ምናልባት በጉባኤ ውስጥ ያለ ያንን ቋንቋ የሚችል አንድ አስፋፊ ሊኖር ስለሚችል ሰውየውን ሊያነጋግረው ይችላል። ስለ ጉዳዩ የከተማ የበላይ ተመልካቹን ሳይቀር ብናነጋግርም ያንን ቋንቋ የሚናገር አንድም ሰው ካልተገኘ የጉባኤው ወንድሞች ለዚያ ሰው ምስክርነቱን ለመስጠት የሚችሉትን ሁሉ ሊያደርጉ ይገባል። በምድር ላይ ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለው ብሮሹር እንዲህ ላሉ ሁኔታዎች ጥሩ ጥቅም እንዳለው ተረጋግጧል።
6 እያንዳንዱ አስፋፊ አስፈላጊ በሆነበት ጊዜ ሁሉ ሰዎችን ተከታትሎ ለመርዳት የሚላኩ ቅጾችን ለመጠቀም ንቁ መሆን ይኖርበታል። ምንም ዓይነት ቋንቋ ቢኖራቸው ለሰዎች ሁሉ የምሥራቹን ለማዳረስ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ‘ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና ትክክለኛውን የእውነት እውቀት ወደ ማወቅ እንዲደርሱ የሚፈልገውን’ የአምላካችንን የይሖዋን ፍቅር እናንጸባርቃለን። — 1 ጢሞ. 2:4 አዓት