የሰዎችን ትኩረት የሚስቡ የተወሰኑ ርዕሶችን ምረጡ
1 ቀስታቸውን አነጣጥረው እንደሚወረውሩ ቀስተኞች ብዙዎቹ የጉባኤ አስፋፊዎችና አቅኚዎች በአገልግሎት ክልላቸው ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ፍላጎት በቀጥታ የሚመለከቱ ርዕሶችን ከመጠበቂያ ግንብ እና ከንቁ! መጽሔቶች በመምረጥና በመጠቀም አስደሳች ውጤት እያገኙ ነው። በመጽሔቶቹ ውስጥ ካሉት ርዕሶች መካከል የትኛው ርዕስ በተለይ ለየትኛው ሰው እንደሚስማማ በቅድሚያ ይወስናሉ። ይህን የሚያደርጉት እንዴት ነው?
2 በመጀመሪያ ደረጃ የሚደርሳቸውን እያንዳንዱን እትም ከዳር እስከ ዳር ያነብባሉ። ከዚያም እያንዳንዱ ርዕስ በተለይ ለማን እንደሚስማማ ራሳቸውን ይጠይቃሉ። ከዚያም ስለ ርዕሰ ጉዳዩ ማንበብ ያስደስታቸዋል ብለው የገመቷቸውን ሰዎች ለማነጋገር ጥረት ያደርጋሉ። አንድ ርዕሰ ጉዳይ በአገልግሎት ክልላቸው የሚገኙትን የብዙ ሰዎች ትኩረት እንደሚስብ ከተሰማቸው ተጨማሪ ቅጂዎችን ያዛሉ።
3 ብዙ ሰዎች መጽሔቶቻችንን ያደንቃሉ፦ በናይጄርያ ውስጥ በሚገኝ ዓለም አቀፍ ስርጭት ባለው በአንድ የመጽሔት ዝግጅት ክፍል የሚሠራና የመጽሔታችን ኮንትራት ያለው አንድ ሰው ንቁ! መጽሔትን በማስመልከት “ብዙ ርዕሰ ጉዳዮችን የሚዳስስ ተወዳዳሪ የማይገኝለት መጽሔት” ሲል አወድሶታል። መጽሔቶቻችንን በከፍተኛ ጉጉት የሚያነብ አንድ ሰው ደግሞ “በዋጋ የማይተመን ጥበብ ያዘለ ውድ ሃብት ነው! እነዚህ [መጽሔቶች] በውስጣቸው ከሚይዟቸው ርዕሰ ጉዳዮች መካከል የማይማርከኝ አንድም ርዕስ የለም ለማለት እችላለሁ” በማለት አስተያየት ሰጥቷል።
4 መጽሔቶቹ የማይዳስሱት ርዕሰ ጉዳይ የለም። ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያክል እንኳ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ስለ ዓለም ሁኔታዎች፣ ስለ ቤተሰብ ጉዳዮች፣ ስለ ማኅበረሰባዊ ችግሮች፣ ስለ ታሪክ፣ ስለ ሳይንስ፣ ስለ እንስሳትና ስለ እጸዋት ሕይወት ይዘው ይወጣሉ። አንድ ሰው ፍላጎቱን፣ ሁኔታውን ወይም ሙያውን የሚዳስስ ነገር ሲያገኝ ይበልጥ ለማንበብ እንደሚጓጓ የታወቀ ነው። እያንዳንዱን ግለሰብ በቀጥታ ፍላጎቱንና ችግሩን የሚመለከት ርዕሰ ጉዳይ መርጠን ስለምናነጋግር የምናገኛቸውን ሰዎች ፍላጎት የሚቀሰቅሱ ርዕሶችን መጠቀሙ ከፍተኛ ውጤት ያስገኛል።
5 ሁለት ምሥክሮች ለአንድ የጋዜጣ አዘጋጅ የመስከረም 8, 1996 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ባበረከቱ ጊዜ ምን እንደሆነ ልብ በሉ። እንዲህ ሲል ጻፈ:- “ፍላጎት የለኝም ብዬ ለመናገር ገና ፋታ ከማግኘቴ በፊት አንደኛው:- ‘መጽሔቱ የአሜሪካ ህንዳውያንን በተመለከተ የሚናገር ርዕስም አለው። ይህን ርዕስ በሚመለከት ብዙ እንደጻፍክ እናውቃለን’ በማለት ንግግሩን ቀጠለ።” ሰውዬው መጽሔቱን ወሰደና ቁርሱን እየበላ ስለ አሜሪካ ህንዳውያን የሚናገረውን ርዕስ አነበበ። ከጊዜ በኋላ “እጅግ በጣም ጥሩ” ደግሞም “በሃቅ ላይ የተመሠረተ ጽሑፍ ነው” በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል።
6 በአገልግሎት ክልላችሁ የሚገኙ ሰዎችን ፍላጎት የሚማርከው ምንድን ነው? በአገልግሎት ክልላችሁ ያሉትን ባለሱቆች ወይም የተለያየ ሙያ ያላቸውን ሰዎች ወይም ጎረቤቶቻችሁን፣ የሥራ ባልደረቦቻችሁንና የትምህርት ቤት ጓደኞቻችሁን ፍላጎት የሚማርክ በቅርብ ጊዜ ከወጡ መጽሔቶች ውስጥ ምን ርዕስ አግኝታችኋል? በተለይ የዳኞችን፣ የአስተማሪዎችን፣ የቤተሰብ ወይም የትምህርት ቤት አማካሪዎችን፣ የወጣት አማካሪዎችን፣ ማኅበራዊ አገልግሎት ሰጪዎችን የሕክምና ባለሙያዎችን ፍላጎት የሚስብ ምን ሊሆን ይችላል? የምትሰብኩላቸውን ሰዎች ሁኔታ በአእምሯችሁ ይዛችሁ የሚደርሳችሁን እያንዳንዱን መጽሔት መመርመራችሁ የእውነትን ቃል ለማሰራጨት የሚያስችሉ ጥሩ መንገዶች ይከፍትላችኋል።
7 አንድ ሰው የመጠበቂያ ግንብ ወይም የንቁ! መጽሔት ርዕስ ትኩረቱን ስቦት መጽሔቱን በሚወስድበት ጊዜ እንዲህ ልትል ትችላለህ:- “እርስዎ ይወዱታል ብዬ የማስበው ርዕስ ሳገኝ ይዤልዎት እመጣለሁ።” አዳዲስ መጽሔቶች በወጡ ቁጥር ይዘህ የምትሄድ ከሆነ የመጽሔት ደንበኞችህን ቁጥር ከፍ ማድረግ ትችላለህ። በመጽሔቶቻችን ላይ የሚወጡ የተወሰኑ ርዕሶችን ማንበብ ለሚፈልጉ የምንጠቀምበት ዘዴም ይኸው ነው።
8 መንፈሳዊ ነገሮች ላይ ትኩረት አድርጉ፦ ከጥቂት ዓመታት በፊት በተሰለፈበት የሙያ መስክ እድገት በማድረግ ላይ ያተኮረ አንድ ሰው ፍላጎቱን የማረከውን አንድ የንቁ! መጽሔት ይወስዳል። ይሁን እንጂ ይህ ሃይማኖታዊ ዝንባሌ ያለው ሰው ዕድሜውን በሙሉ ሲያምንበት የነበረውን የሥላሴ እምነት እንዲመረምር ያነሳሳውን ርዕስ የያዘ የመጠበቂያ ግንብ እትም ያነባል። ከስድስት ወራት በኋላ ተጠመቀ። ስለዚህ የመጽሔቶቻችንን አንባቢዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ውይይት እንዲያደርጉ ከመጋበዝ ወደኋላ አትበሉ። አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተባለውን ብሮሹር ልትሰጧቸውና አዲስ የወጣ መጽሔት ይዛችሁላቸው በምትሄዱበት በእያንዳንዱ ቀን ከብሮሹሩ አንድ ትምህርት አብራችሁ እንድትሸፍኑ ልትጋብዟቸው ትችላላችሁ።
9 ተመላልሶ መጠየቅ ከምታደርጉላቸውና በሥራ ጉዳይ ከምታገኟቸው ሰዎች መካከል በቅርብ የወጡ የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! እትሞችን ማግኘት የሚፈልጉት የትኞቹ እንደሆኑ አስቀድማችሁ ለማወቅ ጣሩ። ከዚያም እነርሱን ለማግኘት ጥረት አድርጉ። እነዚህን ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው መጽሔቶች በተቻለ መጠን ለብዙ ሰዎች አበርክቱ። መጽሔቶቻችንን እንዲያነቡ ብዙ ሰዎችን ለመርዳት ጥረት ባደረጋችሁ መጠን ‘እንጀራችሁን በውኃ ላይ እየጣላችሁ’ እንደሆነ ፈጽሞ አትዘንጉ። ውሎ አድሮ እነሱም እንደኛው ደቀ መዝሙር ሊሆኑ ስለሚችሉ ልትካሱ ትችላላችሁ።—መክ. 11:1, 6