የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን እድገት እንዲያደርጉ መርዳት
ክፍል 9፦ ጥናቶቻችን መደበኛ ባልሆነ መንገድ መመሥከር እንዲችሉ ማሠልጠን
1 እንድርያስና ፊልጶስ፣ እንደሚመጣ ተስፋ የተደረገው መሲሕ ኢየሱስ መሆኑን ሲያውቁ ይህን አስደሳች ዜና ለሌሎች ከመንገር ወደኋላ አላሉም። (ዮሐ. 1:40-45) ዛሬም በተመሳሳይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን በተማሩት ነገር ላይ እምነት ማሳደር ሲጀምሩ ያወቁትን ለሌሎች ለመናገር ይገፋፋሉ። (2 ቆሮ. 4:13) መደበኛ ባልሆነ መንገድ እንዲመሠክሩ እንዴት ማበረታታት እንችላለን? በዚህ ረገድ ውጤታማ እንዲሆኑ ልናሠለጥናቸው የምንችለውስ እንዴት ነው?
2 ጥናትህ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማረውን ለሌሎች መናገር ጀምሮ እንደሆነ ልትጠይቀው ትችላለህ። ምናልባት በሚያጠናበት ወቅት ጓደኞቹንና የቤተሰቡን አባላት በጥናቱ ላይ እንዲገኙ ሊጋብዛቸው ይችላል። ከሥራ ባልደረቦቹ፣ አብረውት ከሚማሩት ልጆች ወይም ከሌሎች ወዳጆቹ መካከል ለምሥራቹ ፍላጎት ያሳዩ እንዳሉ ጠይቀው። በዚህ መንገድ መመሥከር ሊጀምር ይችላል። ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ዓላማዎቹ ለሌሎች በሚናገርበት ጊዜ አስተዋይ መሆን እንዳለበት እንዲሁም አክብሮትና ደግነት ማሳየቱ አስፈላጊ መሆኑን እንዲገነዘብ እርዳው።—ቈላ. 4:6፤ 2 ጢሞ. 2:24, 25
3 ስለ እምነታቸው ለሌሎች መናገር:- የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ስለ እምነታቸው ለሌሎች በሚናገሩበት ጊዜ በአምላክ ቃል እንዲጠቀሙ ማሠልጠኑ በጣም አስፈላጊ ነው። በጥናቱ ወቅት በአንዳንድ ነጥቦች ላይ ጥናትህን እንዲህ እያልክ ጠይቀው:- “ይህንን እውነት በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅመህ ለቤተሰቦችህ እንዴት ማስረዳት ትችላለህ?” ወይም “ስለዚህ ጉዳይ ለአንድ ጓደኛህ ለማስረዳት የትኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ትጠቀማለህ?” የሚሰጠውን መልስ ልብ ብለህ አዳምጠው፤ ከዚያም ለሚናገረው ነገር የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ እንዴት ማቅረብ እንደሚችል አሳየው። (2 ጢሞ. 2:15) እንዲህ በማድረግ ጥናትህ አሁን መደበኛ ባልሆነ መንገድ እንዲመሠክር፣ ብቃቱን ሲያሟላ ደግሞ ከጉባኤው ጋር በተደራጀ መልክ በሚከናወነው የስብከት ሥራ መሳተፍ እንዲችል ታዘጋጀዋለህ።
4 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ተቃውሞን መቋቋም እንዲችሉ አስቀድሞ ማዘጋጀት ጥበብ ነው። (ማቴ. 10:36፤ ሉቃስ 8:13፤ 2 ጢሞ. 3:12) አንዳንዶች ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ጥያቄ ሲያነሱ ወይም ሐሳብ ሲሰጡ፣ ጥናቶች ምሥክርነት ለመስጠት ጥሩ አጋጣሚ ያገኛሉ። ማመራመር በተባለው መጽሐፍ ላይ “የይሖዋ ምሥክሮች” በሚለው ርዕስ ሥር የቀረበው ሐሳብ ‘መልስ ለመስጠት ሁልጊዜ የተዘጋጁ’ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል። (1 ጴጥ. 3:15) ይህ መጽሐፍ ትክክለኛ መረጃዎችን የያዘ ስለሆነ አዲሶች በአሳቢነት ተነሳስተው ለሚቃወሟቸው ወዳጆቻቸው ወይም የቤተሰባቸው አባላት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለተመሠረተው እምነታችንና ሥራችን ለማስረዳት ሊጠቀሙበት ይችላሉ።