የመጽሔት ደንበኞችን ፍላጎት ለመቀስቀስ ጥረት አድርጉ
1 በአገልግሎት ላይ የምናገኛቸው ብዙ ሰዎች ተመላልሰን በመሄድ ስናነጋግራቸውም ሆነ ጽሑፎቻችንን ስናደርስላቸው ደስ ይላቸዋል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስን በቋሚነት እንዲያጠኑ የሚቀርብላቸውን ግብዣ ለመቀበል ያቅማማሉ። የእነዚህን ሰዎች ፍላጎት ማነሳሳት ከምንችልባቸው አጋጣሚዎች አንዱ የመጽሔት ደንበኝነት ነው። መጽሔቶችን ካበረከትክ በኋላ የግለሰቡን ስምና አድራሻ፣ ያነጋገርክበትን ቀን፣ የትኞቹን እትሞች እንደወሰደና የተወያያችሁበትን ጥቅስ እንዲሁም ስለ ግለሰቡ ያስተዋልካቸውን ነገሮች መዝግበህ ያዝ። አዳዲስ እትሞች ሲደርሱህ የመጽሔት ደንበኞችህን ይማርካሉ ብለህ የምታስባቸውን ሐሳቦች አስቀድመህ በመዘጋጀት ተመላልሶ መጠየቅ በምታደርግላቸው ወቅት ልታጎላቸው ትችላለህ። (1 ቆሮ. 9:19-23) ከጊዜ በኋላ በጽሑፎቻችን ላይ ያነበቡት አንድ ሐሳብ ፍላጎታቸውን ቀስቅሶ ይበልጥ ለማወቅ ሊያነሳሳቸው ይችላል።
2 ይሁን እንጂ ብዙ ሰዎች መጽሔቶችን በግላቸው በማንበብ ብቻ የይሖዋ አገልጋዮች እንደማይሆኑ እናውቃለን። ሰዎች ይሖዋን መፈለጋቸው አጣዳፊ ስለሆነ ከዚህ የበለጠ ለመርዳት ምን ማድረግ እንችላለን? (ሶፎ. 2:2, 3፤ ራእይ 14:6, 7) መጽሔቶችን ባደረስንላቸው ቁጥር አንድ የታሰበበት ጥቅስ በማንበብ ፍላጎታቸው እየጨመረ እንዲሄድ ማድረግ እንችላለን።
3 በአንድ ጥቅስ ላይ የተመሠረተ ውይይት:- ስለ መጽሔት ደንበኞችህ አስብ፤ ከዚያም የግለሰቦቹን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት በአንድ ጥቅስ ላይ ተመሥርተህ በቀጣይነት ለመወያየት ዝግጅት አድርግ። (ፊልጵ. 2:4) ለምሳሌ ያህል፣ ተመላልሶ መጠየቅ ከምታደርግላቸው ሰዎች መካከል አንዱ በቅርቡ ዘመድ ሞቶበት ከነበረ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታና ስለ ትንሣኤ ተስፋ ምን እንደሚል በየጊዜው እየሄድክ ልታወያየው ትችላለህ። ማመራመር በተባለው መጽሐፍ ውስጥ “ሞት” እና “ትንሣኤ” በሚሉት ርዕሶች ሥር የሚገኙትን ሐሳቦች ተጠቅሞ በአንድ ጥቅስ ላይ የተመሠረቱ ውይይቶችን መዘጋጀት ይቻላል። ከዚያ በመቀጠል በሽታ፣ እርጅናና ሞት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚወገዱት እንዴት ነው? እንደሚሉት ባሉ ተዛማጅነት ባላቸው ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ተጨማሪ ውይይቶች ማድረግ ትችላላችሁ። ዋናው ነገር የግለሰቡን ትኩረት የሚስበው ምን እንደሆነ ማወቅና መጽሐፍ ቅዱስ ያንን ጉዳይ በተመለከተ ምን እንደሚል ደረጃ በደረጃ ማስረዳቱ ላይ ነው።
4 ጥቅሱን ማብራራት:- አብዛኛውን ጊዜ ይህ ዓይነቱ ውይይት ቀላልና አጭር መሆኑ ጥሩ ቢሆንም ጥቅሱን ከማንበብ የበለጠ ነገር ማድረግ ይጠይቃል። ሰይጣን ምሥራቹን እንዳይቀበሉ የሰዎችን ልቡና አሳውሯል። (2 ቆሮ. 4:3, 4) መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነቡ ሰዎችም እንኳ የሚያስረዳቸው ሰው ያስፈልጋቸዋል። (ሥራ 8:30, 31) ስለሆነም በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ክፍል ስታቀርብ እንደምታደርገው ጊዜ ወስደህ ጥቅሱን እያብራራህ በምሳሌ አስረዳው። (ሥራ 17:3) ግለሰቡ የአምላክ ቃል ለሕይወቱ ጠቃሚ መሆኑን እንዲያስተውል ለመርዳት ጥረት አድርግ።
5 ግለሰቡ በሚማረው ነገር ደስተኛ ከሆነ የምትጠቀምባቸውን ጥቅሶች ከአንድ ወደ ሁለት፣ ከሁለት ወደ ሦስት በመጨመር ውይይቱን ሰፋ ማድረግ ትችላለህ። ከዚያም አጋጣሚ ፈልገህ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለውን ብሮሹር ወይም እውቀት መጽሐፍን ልታስተዋውቀው ትችላለህ። በዚህ መንገድ የመጽሔት ደንበኞች ቀስ በቀስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሊሆኑ ይችላሉ።
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
1. የመጽሔት ደንበኞቻችንን ፍላጎት መቀስቀስ የምንችለው እንዴት ነው?
2. ሰዎች ይሖዋን መፈለጋቸው አጣዳፊ የሆነው ለምንድን ነው? እነሱን ይበልጥ ለመርዳት ምን ማድረግ እንችላለን?
3. (ሀ) በአንድ ጥቅስ ላይ የተመሠረተ ቀጣይነት ያለው ውይይት ለማድረግ መዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) በክልልህ ውስጥ የሚገኙትን ሰዎች የሚያሳስቧቸው ጉዳዮች ምንድን ናቸው?
4. የምናነጋግራቸው ሰዎች ጥቅሶችን እንዲያስተውሉ መርዳታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? እንዲህ ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው?
5. አንድ የመጽሔት ደንበኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?