ለሰዎች ያለብን ዕዳ
1 ሐዋርያው ጳውሎስ ለሰዎች የመስበክ ግዴታ እንዳለበት ተሰምቶታል። ይሖዋ በልጁ ክቡር ደም አማካኝነት ሰዎች ሁሉ መዳን የሚችሉበትን ዝግጅት ማድረጉን ያውቅ ነበር። (1 ጢሞ. 2:3-6) በዚህም ምክንያት “ግሪኮች ለሆኑትና ላልሆኑት፣ ለጥበበኞችና ለማያስተውሉ፣ ዕዳ አለብኝ” በማለት ተናግሯል። ጳውሎስ ለሌሎች ሰዎች ያለበትን ዕዳ ለመክፈል ሲል ምሥራቹን በጋለ ስሜትና ያለማሰለስ ሰብኳል።—ሮሜ 1:14, 15
2 በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ክርስቲያኖችም ልክ እንደ ጳውሎስ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ለሰዎች ምሥራቹን መስበክ ይፈልጋሉ። ‘ታላቁ መከራ’ በፍጥነት እየተቃረበ በመሆኑ ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች መፈለጋችን አጣዳፊ ነው። ለሰዎች ያለን ልባዊ ፍቅር ሕይወት አድን በሆነው በዚህ ሥራ ላይ በትጋት እንድንካፈል ይረዳናል።—ማቴ. 24:21፤ ሕዝ. 33:8
3 ዕዳችንን መክፈል:- ለሰዎች መስበክ የምንችልበት ዋነኛው መንገድ ከቤት ወደ ቤት ማገልገል ነው። ብዙ ሰዎች ቤታቸው በማይገኙባቸው የአገልግሎት ክልሎች ውስጥ ትክክለኛ መረጃ መያዝና በተለያየ ሰዓት መሄድ ተጨማሪ ሰዎችን እንድናገኝ ያስችለናል። (1 ቆሮ. 10:33) በተጨማሪም በንግድ አካባቢ፣ በመንገድ ላይ፣ በመናፈሻ ቦታዎች፣ በመኪና ማቆሚያ አካባቢዎች እንዲሁም በስልክ በመመሥከር ምሥራቹን ለሰዎች ማድረስ እንችላለን። ‘የሕይወትን መልእክት ለሌሎች ለማካፈል በሁሉም ዓይነት የስብከት ዘዴዎች የቻልኩትን ያህል ለመጠቀም እየጣርኩ ነው?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን።—ማቴ. 10:11
4 አንዲት አቅኚ እህት በአገልግሎት ክልሏ ለሚገኙት ሰዎች ሁሉ ምሥራቹን የማድረስ ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባት ይሰማታል። ይሁን እንጂ ወደ አንድ ቤት ደጋግማ ብትሄድም ማንንም ሰው አግኝታ አታውቅም። አንድ ቀን በሌላ ጉዳይ በዚያ አካባቢ ስታልፍ በር ላይ መኪና ቆሞ አየች። አጋጣሚው እንዳያመልጣት ስትል የቤቱን መጥሪያ ደወለች። አንድ ሰው በሩን ከፍቶላት ውይይት ያደረጉ ሲሆን ይህም እህትና ባለቤቷ ለበርካታ ጊዜያት ተመላልሶ መጠየቅ እንዲያደርጉ መሠረት ጥሏል። ከጊዜ በኋላ ሰውየው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምር የቀረበለትን ግብዣ ተቀበለ፤ አሁን የተጠመቀ ወንድም ሆኗል። ይህች እህት ለሌሎች የመስበክ ዕዳ እንዳለባት ተሰምቷት ኃላፊነቷን በመወጣቷ አመስጋኝ ነው።
5 መጨረሻው ይበልጥ እየተቃረበ በመሆኑ በስብከቱ ሥራ በትጋት እየተካፈልን ለሌሎች ሰዎች ያለብንን ዕዳ የምንከፍልበት ጊዜ አሁን ነው።—2 ቆሮ. 6:1, 2