ሰዎች ቤታቸው ባይገኙ ምን ማድረግ እንችላለን?
1. ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል አብዛኛውን ጊዜ የሚያጋጥመን አስቸጋሪ ሁኔታ ምንድን ነው?
1 በብዙ አካባቢዎች ሰዎችን ቤታቸው ማግኘት በጣም አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል። በዚህ “የሚያስጨንቅ ጊዜ” ውስጥ ሰዎች ኑሯቸውን ለማሸነፍ ሲሉ ለረጅም ሰዓታት ለመሥራት ይገደዳሉ። (2 ጢሞ. 3:1) ሰዎች በሥራ ምክንያት ወይም አንዳንድ ነገሮችን ለመሸመት አሊያም ለመዝናናት ወደ ሌላ ቦታ ስለሚሄዱ ቤታቸው አይገኙም። ታዲያ ለእነዚህ ሰዎች ምሥራቹን ማድረስ የምንችለው እንዴት ነው?
2. ቤታቸው ያልተገኙ ሰዎችን ተከታትለን መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?
2 ጥሩ ማስታወሻ ያዝ:- ልንወስደው የሚገባው የመጀመሪያው እርምጃ ቤታቸው ያልተገኙ ሰዎችን መዝግበን መያዝ ነው። በክልልህ ውስጥ አዘውትረህ የምታገለግል ከሆነ እንዲህ ማድረግህ በጣም ጠቃሚ ነው። በማስታወሻህ ላይ የቤቱን ቁጥር፣ የአገልግሎት ክልሉን ቁጥር፣ ስምህንና ቀኑን ትጽፋለህ? አንተም ሆንክ ሌላ አስፋፊ ቤታቸው ያልተገኙ ሰዎችን ለማነጋገር ተመልሳችሁ በምትሄዱበት ጊዜ ተጨማሪ ማስታወሻ ለመጻፍ እንድትችሉ ክፍት ቦታ መተው ትችላለህ። አገልግሎትህን ስትጨርስ የያዝከውን ማስታወሻ ክልሉ ለተሰጠው ወንድም መስጠት እንደሚኖርብህ አትርሳ። ቤታቸው ያልተገኙትን እንድትከታተል ከፈቀደልህ ግን ማስታወሻውን ልትይዘው ትችላለህ። ተመላልሶ መጠየቅ የምታደርግላቸውን ሰዎች ለመመዝገብ ሌላ ወረቀት ተጠቀም።
3. ቤታቸው የማይገኙ ሰዎችን ለማግኘት የሚረዱን አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?
3 በሌላ ጊዜ ለመመለስ ሞክር:- በሥራ ቀናት ቤታቸው ያልተገኙ ሰዎች ምናልባት ምሽት ላይ ወይም ቅዳሜና እሁድ ቤታቸው ይገኙ ይሆናል። ይበልጥ አመቺ በሆነ ሰዓት ላይ ተመልሰህ ለመሄድ ፕሮግራምህን ማስተካከል ትችል ይሆን? (1 ቆሮ. 10:24) እንዲህ ማድረግ ካልቻልክ ቤታቸው ያልተገኙ ሰዎችን አድራሻ በሌላ ጊዜ መሄድ ለሚችል አንድ አስፋፊ ልትሰጠው ትችላለህ። ካልሆነም ቤታቸው ለማይገኙ ሰዎች ደብዳቤ ልትጽፍላቸው አሊያም ስልክ ልትደውልላቸው ትችላለህ። በዚህ ረገድ በጤንነት ምክንያት ከቤት ወደ ቤት ማገልገል የማይችሉ አስፋፊዎች ሊረዱህ ይችላሉ።
4. ቤታቸው የማይገኙ ሰዎችን ለማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራ ማድረጋችን አስፈላጊ እንደሆነ የሚያሳየው ምንድን ነው?
4 የሚከተለው ተሞክሮ ቤታቸው የማይገኙ ሰዎችን እንደምንም ብለን ለማግኘት ጥረት ማድረጋችን አስፈላጊ መሆኑን ያሳያል። ወንድሞች ወደ አንድ ቤት ለሦስት ዓመታት ከተመላለሱ በኋላ አንድ ቀን የቤቱን ባለቤት አገኟት። ሴትየዋ ወደዚህ ቤት ከመዛወሯ በፊት የጀመረችውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መቀጠል እንድትችል፣ ሁልጊዜ የይሖዋ ምሥክሮችን መምጣት ትጠባበቅ እንደነበር ተናግራለች።
5. አንድ ክልል ተሸፍኗል ሊባል የሚችለው መቼ ነው?
5 ክልልህን ሸፍን:- አንድ ክልል ተሸፍኗል የሚባለው መቼ ነው? በእያንዳንዱ ቤት አንድ ሰው አግኝቶ ለማነጋገር አስፈላጊው ጥረት ከተደረገ ተሸፍኗል ሊባል ይችላል። አልፎ አልፎ በሚሠራባቸው ክልሎች ውስጥ ቤታቸው ለማይገኙ ሰዎች ትራክት ወይም የቆዩ መጽሔቶችን ሌሎች በማያዩበት ቦታ ማስቀመጣችን ተገቢ ሊሆን ይችላል። ክልሉ በአራት ወር ውስጥ መሸፈን ይኖርበታል። የክልል አገልጋዩ አስፈላጊውን መረጃ መመዝገብ እንዲችል ክልሉን እንደጨረስክ ወዲያውኑ ማሳወቅ ይኖርብሃል።
6. በክልላችን ውስጥ ለሚገኝ ለእያንዳንዱ ሰው ምሥራቹን ለማድረስ ጥረት ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?
6 በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች የይሖዋን ስም በመጥራት መዳን እንዲያገኙ እንፈልጋለን። (ሮሜ 10:13, 14) ይህ ደግሞ ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል ቤታቸው የማይገኙ ሰዎችን መርዳትን ይጨምራል። እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ሁሉ አንተም ‘የአምላክን የጸጋ ወንጌል የመመስከር አገልግሎትህን’ ሙሉ በሙሉ የመፈጸም ፍላጎት ይኑርህ።—ሥራ 20:24