የጉባኤያችሁ የአገልግሎት ክልል ሰፊ ነውን?
1 ኢየሱስ ከይሁዳ ከተሞች አንስቶ እስከ ገሊላ ገጠራማ ቦታዎች ድረስ ያለውን ሰፊ ክልል በሚሸፍነው የጥንቷ እስራኤል ምድር የተጣራ ምሥክርነት ሰጥቷል። (ማር. 1:38, 39፤ ሉቃስ 23:5) እኛም ብንሆን የቻልነውን ያህል ለብዙ ሰዎች ምሥራቹን ማድረስ አለብን። (ማር. 13:10) ይሁን እንጂ ይህንን ማድረግ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ለምን?
2 የብዙ ጉባኤዎች የአገልግሎት ክልል በአብዛኛው ገጠራማና በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን የሚሸፍን ነው። ሌሎች ጉባኤዎች ደግሞ ሕዝብ በበዛባቸው ትላልቅ ከተሞች ያገለግሉ ይሆናል። እንደዚህ በመሰሉ ሰፊ ክልሎች ውስጥ የሚኖሩት ሰዎች ስለ ይሖዋ፣ ስለ ኢየሱስና ስለ መንግሥቱ እንዲያውቁ ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው?
3 ጥንቃቄ የተሞላበት እቅድ አውጡ፦ የተሻለ ውጤት ማግኘት እንዲቻል የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹና የክልል አገልጋዩ ጉባኤውን ማስተባበር አለባቸው። ምናልባትም አብዛኞቹ ሙሉውን ቀን ለሥራው ማዋል እንዲችሉ ቅዳሜ ቀን ለማገልገል ፕሮግራም ማውጣት ይቻል ይሆናል። ራቅ ባሉ ክልሎች ውስጥ ስትሠሩ ከተቻለ ምሳችሁን ይዛችሁ በመሄድ በአገልግሎቱ ረዘም ያለ ሰዓት ለማሳለፍ እቅድ አውጡ። ወደ ክልሉ በጊዜ ለመድረስ እንድትችሉ ለመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ ከወትሮው ቀደም ብላችሁ መገናኘት አሊያም የስምሪት ስብሰባውን ክልሉ አካባቢ ስትደርሱ ማድረግ ትችላላችሁ። በቡድኑ ውስጥ ያሉት ሁሉ የሚያንኳኩት ቤት እንዲያገኙ በአንድ ቡድን ውስጥ ጥቂት አስፋፊዎች እንዲኖሩ አድርጉ። ገጠራማ በሆኑ ቦታዎች የአየሩ ጠባይና መንገዱ ጥሩ በሚሆንበት ወቅት ለመሥራት ዝግጅት አድርጉ።
4 በቂ ጽሑፎች ይዛችሁ መሄድ አትርሱ። ክልሉ እምብዛም ያልተሠራበት ከሆነ ሰው በሌለባቸው ቤቶች ትራክት ወይም የቆዩ መጽሔቶች መተዉ ጥሩ ነው። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የበለጠ ለማወቅ ትፈልጋለህን? የተሰኘው ትራክት በቋንቋችሁ የሚገኝ ከሆነ ለምታገኙት ሰው ሁሉ አበርክቱት እንዲሁም ሰው በሌለባቸው ቤቶች ትታችሁላቸው ሂዱ።
5 ተባብራችሁ ሥሩ፦ ሰፋፊ ክልሎችን መሸፈን በጉባኤው ውስጥ ያለ የሁሉንም ሰው ትብብር ይጠይቃል። ወደ ክልሉ ለመድረስ ረዥም ርቀት መጓዝ የሚያስፈልግ ከሆነ በአንድ መኪና አብረው የሚሄዱት የቤንዚን ወጪውን ሊጋሩ ይችላሉ። መወያየት የሚፈልጉ የቤት ባለቤቶች ስታገኙ አስተዋዮች መሆን አለባችሁ። አጠቃላይ ክልሉን መሸፈን እንደሚያስፈልግ አስታውሱ እንዲሁም በአገልግሎት ቡድናችሁ ውስጥ ላሉት ለሌሎቹ አስፋፊዎች አሳቢ ሁኑ። ፍላጎት ካሳየው ሰው ጋር ሰፋ ያለ ውይይት ማድረግ ከፈለጋችሁ በቡድኑ ውስጥ ያሉት ሌሎቹ ሥራ እንዳይፈቱ ዝግጅት ማድረግ ይቻል ይሆን?
6 ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ሁሉ ተከታትላችሁ ለመርዳት ዝግጅት አድርጉ። ፍላጎት ካሳየው ግለሰብ ጋር በስልክ ተገናኝታችሁ ቀጣይ የስልክ ምሥክርነት ለመስጠት እንድትችሉ ከአድራሻው በተጨማሪ የስልክ ቁጥርም ለመቀበል ሞክሩ። ገጠራማ ቦታዎች ላይ ያሉ ቤቶች የቤት ቁጥር ከሌላቸው ተመላልሶ መጠይቅ ስታደርጉ ፍላጎት ያሳየውን ሰው ማግኘት እንድትችሉ በጥንቃቄ ካርታ ሥሩ ወይም ዝርዝር መግለጫዎችን ጻፉ።
7 “በምትገቡባትም በማናቸይቱም ከተማ ወይም መንደር፣ በዚያ የሚገባው ማን እንደ ሆነ በጥንቃቄ መርምሩ” ሲል ኢየሱስ የሰጠውን መመሪያ የመፈጸም ውድ መብት አግኝተናል። (ማቴ. 10:11) በዚህ እጅግ የሚክስ ሥራ ራሳችሁን በፈቃደኝነት ስታቀርቡ ይሖዋም ጥረታችሁን ይባርከዋል!