ቤታቸው ያላገኘናቸውን ሰዎች በማስታወሻ መያዝ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
1 ባልና ሚስት የሆኑ ምሥክሮች በማለዳ ተነስተው በመስክ አገልግሎት ተሠማርተው ነበር። በዚያው ቀን ረፋዱ ላይ በክልሉ ውስጥ ቀደም ሲል ቤታቸው ያላገኟቸውን ሰዎች ተመልሰው ለማነጋገር ሄዱ። አንድ ሰው ወደ ቤት እንዲገቡ ጋበዛቸውና በጥሞና አዳመጣቸው። ለዘላለም መኖር የተባለውን መጽሐፍ ወሰደና ምሥክሮቹን ደግመው ይመጡ እንደሆነ ጠየቀ። ከዚህ በፊት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ፈጽሞ ተነጋግሮ አያውቅም። እንዲመለሱለት የሚፈልጋቸው ብዙ ጥያቄዎችም ነበሩት። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረለት። እነዚህ ባልና ሚስት እንዲህ ያለ በግ መሰል ሰው በማግኘታቸው በጣም ተደሰቱ። እንዲህ የመሰለ ተሞክሮ እንዲኖርህ ትፈልጋለህን? እቤት ሰው እንዳልተገኘ የሚገልጽ ጥሩ ማስታወሻ መያዝና ወዲያውኑ ተመልሶ መሄድ እንዲህ ያለ ተሞክሮ እንድታገኝ ያስችልህ ይሆናል።
2 እቤት ሰው እንዳልተገኘ የሚገልጽ ትክክለኛ ማስታወሻ እንድንይዝና ወዲያውም ተመልሰን እንድንሄድ ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ተሰጥቶናል። ከላይ ያለው ተሞክሮ እንደሚያሳየው በተመሳሳይ ቀን ተመልሰን ብንሄድ ግሩም የሆነ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል። የተሰጠንን ክልል ለመሸፈን የምንጣጣር ሊሆን ቢችልም ቤታቸው ያላገኘናቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር በማስታወሻ በመያዝ በኩል ግን ግድየለሾች ሆነን ሊሆን ይችላል። አንዳንዶች ‘በየሁለት ወይም በየሦስት ሳምንቱ በክልላችን ውስጥ ስለምንሠራና ወዲያውም ተመልሰን መሄዳችን ስለማይቀር እንዲህ ያለ ማስታወሻ መያዝ አያስፈልግም’ ይላሉ። ይሁን እንጂ ይህ ራሱ ማስታወሻ እንድንይዝ ተጨማሪ ምክንያት ይሰጠናል። ክልሎች በተደጋጋሚ በሚሸፈኑበት ጊዜ ቤታቸው ያልተገኙ ሰዎችን በማስታወሻ መያዛችን የሚገባቸውን ሰዎች በመፈለግ በኩል የተሟላ ሥራ እንድንሠራ ያስችለናል። እንዴት?
3 በብዙ ቦታዎች 50 በመቶ ወይም ከዚያም በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎች በቀን ቤታቸው አይገኙም። ስለዚህ ቤታቸው ያልተገኙ ሰዎችን ፈልጎ በማግኘቱ ሥራ ላይ በማተኮር ብዙ የአገልግሎት ክልሎች እንዲገኙ ማድረግ ይቻላል። የአገልግሎት ክልሉ አልፎ አልፎ የሚሠራበት ቢሆንም እንኳን ክልሉ ተሸፍኗል ብለን ምልክት ከማድረጋችን በፊት እያንዳንዱን ሰው ለማግኘት ጥረት በማድረግ የተሻለ ውጤት ማግኘት እንችላለን።
4 ቤታቸው ያልተገኙ ሰዎችን ለማግኘት ብዙውን ጊዜ በሌላ ቀን ተመልሶ ወደ ቤታቸው ለመሄድ ዝግጅት ማድረግ ይቻላል። ይህም በዚያው ሳምንት ውስጥ ቢሆን ይመረጣል። ብዙዎች መጀመሪያ ከሄዱበት ቀንና ሰዓት በተለየ ጊዜ ተመልሰው መሄድን የተሻለ ሆኖ አግኝተውታል። በሳምንቱ መካከል ቤታቸው ያልተገኙትን ሰዎች ተከታትለህ ለማግኘት ቅዳሜ ወይም እሁድ ማንኛውንም ሰዓት መርጠህ መሄድ ትፈልግ ይሆናል። ወይም ደግሞ ብዙ ጉባኤዎች በአመሻሹ ላይ ተመልሶ መሄድ ፍሬያማ ሆኖ አግኝተውታል። ከግማሽ የሚበልጡ ሰዎችን ቤታቸው ሊያገኟቸው ይችላሉ።
5 ያደረካቸውን ተመላልሶ መጠየቆች በግል ማስታወሻህ ላይ ማስፈር ይኖርብሃል። ቀደም ሲል ቤታቸው ያላገኘሃቸውን ሰዎች ተመልሰህ ሄደህ ለማነጋገር የማትችል ከሆነ ቤታቸው ያላገኘሃቸውን ሰዎች የመዘገብክበትን ማስታወሻ ቡድኑን ለሚመራው ወንድም መስጠት አለብህ። እሱም እዚያ ክልል ለሚያገለግሉ ለሌሎች ሊሰጠው ይችላል።
6 ለዚህ የአገልግሎታችን መስክ ትኩረት መስጠታችን ፍሬያማነታችንን እንዲሁም ደስታችንን ይጨምርልናል። በግ መሰል ሰዎችን በመፈለጉና በመንከባከቡ ሥራ ረገድ ጥንቃቄ የተሞላበት ተግባር እያከናወንን መሆናችንን ማወቃችን እርካታ ይሰጠናል።—ሕዝ. 34:11–14