ለሌሎች በምክንያት የማስረዳት ችሎታ ማዳበር
1. የትኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እያየን እንሄዳለን? ለምንስ?
1 በሐዋርያት ሥራ 13:16-41 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ሐዋርያው ጳውሎስ በጲስድያ ውስጥ ባለችው በአንጾኪያ በሚገኝ ምኩራብ ውስጥ ያደረገው ንግግር ለሌሎች በምክንያት ማስረዳት ስለምንችልበት መንገድ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል። ጳውሎስ የአድማጮቹን ሁኔታና አስተሳሰብ ግምት ውስጥ በማስገባት ምሥራቹን በዚያ መሠረት ያቀርብ ነበር። ይህን ዘገባ ስንመረምር እኛም በአገልግሎታችን ላይ እንዴት ልንጠቀምበት እንደምንችል እናስተውል።
2. ጳውሎስ ንግግሩን ከጀመረበት መንገድ ምን እንማራለን?
2 የጋራ ነጥብ መፈለግ:- የጳውሎስ ዋና መልእክት ኢየሱስ የአምላክን ዓላማ በማስፈጸም በኩል ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት የሚገልጽ ቢሆንም ንግግሩን ግን በዚህ አልጀመረም። ከዚህ ይልቅ አድማጮቹ በአብዛኛው አይሁዳውያን ስለነበሩ ሁሉም የሚያውቁትን የአይሁዳውያን ታሪክ በማንሳት ንግግሩን ጀምሯል። (ሥራ 13:16-22) እኛም በተመሳሳይ የጋራ ነጥብ ለመፈለግ የምንጥር ከሆነ የሌሎች ሰዎችን ልብ በመንካት ረገድ ይበልጥ ውጤታማ እንሆናለን። ይህ ደግሞ በዘዴ አንዳንድ ጥያቄዎችን በማቅረብ አስተሳሰባቸውን እንዲገልጹ ማበረታታትና ለእነሱ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር ምን እንደሆነ ለመረዳት በጥሞና ማዳመጥ ይጠይቅብናል።
3. የጳውሎስ አድማጮች ኢየሱስ ተስፋ የተደረገበት መሲሕ መሆኑን ለማመን የተቸገሩት ለምን ነበር?
3 ጳውሎስ ለአድማጮቹ የአይሁዳውያንን ታሪክ በሚናገርበት ጊዜ አምላክ፣ ከዳዊት የትውልድ መሥመር አዳኝ እንደሚያስነሳ የተናገረውን ተስፋ አስታውሷቸዋል። ይሁን እንጂ በርካታ አይሁዳውያን ይጠብቁት የነበረው አዳኝ፣ ከሮም አገዛዝ ነፃ የሚያወጣቸውና የአይሁድን ሕዝብ ከሌሎች ሁሉ በላይ የሚያደርግ ወታደራዊ ጀግና ነበር። አድማጮቹ፣ ኢየሱስ በኢየሩሳሌም በሚገኙ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ዘንድ ተቀባይነት እንዳላገኘና እንዲገደል ለሮም ባለ ሥልጣናት አልፎ እንደተሰጠ አሳምረው ያውቃሉ። ታዲያ ጳውሎስ፣ ኢየሱስ ተስፋ የተደረገበት መሲሕ መሆኑን እንዴት ሊያሳምናቸው ይችላል?
4. ጳውሎስ አይሁዳውያን አድማጮቹን በምክንያት ያስረዳቸው እንዴት ነው?
4 አቀራረባችንን እንደ ሁኔታው መለዋወጥ:- ጳውሎስ የአድማጮቹን አመለካከት ከተገነዘበ በኋላ ቀደም ብለው የተቀበሉትን ትምህርት መሠረት በማድረግ ቅዱሳን ጽሑፎችን እየጠቀሰ በምክንያት አስረድቷቸዋል። ለምሳሌ፣ ኢየሱስ የዳዊት ዘር እንደሆነ እንዲሁም እንደ አምላክ ነቢይ ይታይ የነበረው መጥምቁ ዮሐንስ የኢየሱስን ማንነት እንዳሳወቀ ተናግሯል። (ሥራ 13:23-25) ጳውሎስ፣ የሃይማኖት መሪዎቹ ኢየሱስን መቃወማቸውና እንዲገደል ማድረጋቸው “የነቢያት ቃል እንዲፈጸም” እንዳደረገ ገልጿል። (ሥራ 13:26-28) በተጨማሪም ኢየሱስ ከሞት መነሳቱን ያዩ የዓይን ምሥክሮች እንደነበሩ ከተናገረ በኋላ አይሁዳውያን አድማጮቹ የሚያውቋቸውንና በኢየሱስ ትንሣኤ ላይ ተፈጻሚነት ያገኙ የቅዱሳን ጽሑፎች ክፍሎችን ጠቅሷል።—ሥራ 13:29-37
5. (ሀ) ጳውሎስ ለግሪካውያን ሲናገር አቀራረቡን ከአድማጮቹ ሁኔታ ጋር ያስማማው እንዴት ነበር? (ለ) በክልላችን ውስጥ ስናገለግል የጳውሎስን ምሳሌ እንዴት መኮረጅ እንችላለን?
5 በሌላ በኩል ደግሞ ጳውሎስ በአቴና ውስጥ በአርዮስፋጎስ ለነበሩ ግሪካውያን ሲናገር የተጠቀመው ሌላ ዓይነት አቀራረብ ነበር። (ሥራ 17:22-31) ያም ሆኖ ግን በሁለቱም ወቅት የተናገረው መልእክት መሠረታዊ ሐሳብ አንድ ዓይነት ሲሆን ጥሩ ውጤትም አስገኝቷል። (ሥራ 13:42, 43፤ 17:34) ዛሬም በተመሳሳይ ከአድማጮቻችን ጋር የሚስማማ የጋራ ነጥብ ለመፈለግ የምንጥርና አቀራረባችንን ከአስተሳሰባቸው ወይም ከሁኔታቸው ጋር የምናስማማ ከሆነ በአገልግሎታችን ውጤታማ እንሆናለን።