ዘዴኞችና እንደ ሁኔታው አቀራረባችሁን የምትለውጡ አገልጋዮች ሁኑ
“በሚቻለኝ ሁሉ አንዳንዶችን አድን ዘንድ፣ ከሁሉም ጋር ሁሉን ነገር ሆንሁ።”—1 ቆሮንቶስ 9:22
1, 2. (ሀ) ጳውሎስ ውጤታማ አገልጋይ የነበረው በምን መንገዶች ነው? (ለ) ጳውሎስ ስለተሰጠው ሥራ የነበረውን አመለካከት ምን በማለት ገልጿል?
በጣም ከተማሩ ሰዎችም ሆነ ከተራ ድንኳን ሰፊዎች ጋር በቀላሉ መግባባት ይችል ነበር። ሮማውያን ባለ ሥልጣናትንና የፍርግያ ገበሬዎችን ማሳመን አልቸገረውም። ጽሑፎቹ፣ ለዘብተኛ ግሪኮችንም ሆነ ወግ አጥባቂ አይሁዳውያንን ለእርምጃ አነሳስተዋል። ሰውየው የሚያቀርበው ማስረጃ መሬት ጠብ የማይል ከመሆኑም በላይ የሌሎችን ስሜት የመማረክ ትልቅ ችሎታ ነበረው። ከሁሉም ዓይነት ሰዎች ጋር ሲነጋገር በጋራ የሚስማሙበትን ነጥብ ለማግኘት በመሞከር አንዳንዶች በክርስቶስ እንዲያምኑ ለመርዳት ይጥር ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 20:21
2 ይህ ሰው ሐዋርያው ጳውሎስ ነው፤ ጳውሎስ ውጤታማና ዘዴኛ አገልጋይ እንደነበር ምንም አያጠራጥርም። (1 ጢሞቴዎስ 1:12) ኢየሱስ፣ ለጳውሎስ ‘በአሕዛብና በነገሥታት ፊት እንዲሁም በእስራኤል ሕዝብ ፊት [የክርስቶስን] ስም የመሸከም’ ተልእኮ ሰጥቶት ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 9:15) ለተሰጠው ሥራ ምን አመለካከት ነበረው? “በሚቻለኝ ሁሉ አንዳንዶችን አድን ዘንድ፣ ከሁሉም ጋር ሁሉን ነገር ሆንሁ። ይህን ሁሉ የማደርገው፣ ከወንጌል በረከት እካፈል ዘንድ፣ ስለ ወንጌል ብዬ ነው” በማለት ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 9:19-23) በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ ይበልጥ ውጤታማ እንድንሆን ጳውሎስ ከተወው ምሳሌ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?
ለውጥ ያደረገው ሰው ፈታኙን ሥራ ተወጣ
3. ጳውሎስ ከመለወጡ በፊት ለክርስቲያኖች ምን አመለካከት ነበረው?
3 ጳውሎስ ቀደም ሲል ትዕግሥተኛ፣ አሳቢና ለተሠጠው ሥራ ብቃት ያለው ሰው ነበር? በጭራሽ አልነበረም! ሳውል (ጳውሎስ ቀድሞ ይጠራበት የነበረው ስም ነው) አክራሪ ሃይማኖተኛ ስለነበር የክርስቶስን ተከታዮች በጭካኔ አሳድዷል። ጎልማሳ ሳለ በእስጢፋኖስ መገደል ተስማምቶ ነበር። ከዚያ በኋላ ክርስቲያኖችን እየተከታተለ ያለ ምሕረት ያሳድድ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 7:58፤ 8:1, 3፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:13) እንዲያውም “የጌታን ደቀ መዛሙርት ለመግደል” መዛቱን ቀጠለበት። በኢየሩሳሌም የነበሩትን አማኞች ማሳደዱ ስላላረካው የጥላቻ ዘመቻውን በስተ ሰሜን እስከ ደማስቆ ድረስ ያራምድ ጀመር።—የሐዋርያት ሥራ 9:1, 2
4. ጳውሎስ የተሰጠውን ሥራ ለማከናወን ምን ማስተካከያ ማድረግ አስፈልጎት ነበር?
4 ጳውሎስ ክርስትናን ክፉኛ እንዲጠላ ያደረገው ዋነኛ ምክንያት፣ አዲሱ እምነት የአይሁድን ሃይማኖት መጥፎ ከሆነው የአሕዛብ አስተሳሰብ ጋር በመቀላቀል ይበክለዋል የሚል አመለካከት ስለነበረው ሳይሆን አይቀርም። እንዲያውም ጳውሎስ “ፈሪሳዊ” ነበር፤ ይህ ቃል “የተለየ” የሚል ትርጉም አለው። (የሐዋርያት ሥራ 23:6) ጳውሎስ አሕዛብን ጨምሮ ለሁሉም ሰዎች ስለ ክርስቶስ እንዲሰብክ አምላክ እንደ መረጠው ሲያውቅ ምን ያህል እንደደነገጠ መገመት አያዳግትም! (የሐዋርያት ሥራ 22:14, 15፤ 26:16-18) ምክንያቱም ፈሪሳውያን ኃጢአተኞች ናቸው ከሚሏቸው ሰዎች ጋር ምግብ እንኳን አይበሉም ነበር! (ሉቃስ 7:36-39) የአምላክ ፈቃድ ሰዎች ሁሉ እንዲድኑ ነው፤ ጳውሎስ አመለካከቱን ለመገምገምና ከዚህ የይሖዋ ፈቃድ ጋር ለመስማማት ትልቅ ጥረት ጠይቆበት እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም።—ገላትያ 1:13-17
5. በአገልግሎታችን የጳውሎስን ምሳሌ መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው?
5 እኛም ተመሳሳይ ነገር ማድረግ ይጠበቅብን ይሆናል። በዓለም ዙሪያ በብዙ ቋንቋዎች እየተካሄደ ያለውን የስብከት ሥራ ስናከናውን፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እያደገ የሚመጣውን የተለያዩ ዓይነት ሰዎች ስለምናገኝ አመለካከታችንን ለመገምገምና ጭፍን ጥላቻ ካለብን ለማስወገድ የታሰበበት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። (ኤፌሶን 4:22-24) አወቅነውም አላወቅነው፣ ያደግንበት ማኅበረሰብና የተማርነው ትምህርት ተጽዕኖ ያደርጉብናል። ይህም የምናዳላ፣ ሰውን በሩቁ የምንጠላና ግትር እንድንሆን ሊያደርገን ይችላል። በግ መሰል ሰዎችን በማግኘትና በመርዳት ረገድ እንዲሳካልን ከፈለግን እንዲህ ያሉትን ስሜቶች ማሸነፍ ይገባናል። (ሮሜ 15:7) ጳውሎስም ያደረገው ይህንኑ ነበር። አገልግሎቱን ለማስፋት ፈታኝ ሁኔታዎች አጋጥመውት ነበር። ቢሆንም በፍቅር ተነሳስቶ ሊኮረጁ የሚገባቸው የስብከት ዘዴዎችን አዳብሯል። “የአሕዛብ ሐዋርያ” ስለሆነው ስለ ጳውሎስ አገልግሎት ማጥናታችን በእርግጥም አስተዋይ፣ እንደ ሁኔታው አቀራረቡን የሚለውጥ እንዲሁም ዘዴኛ የሆነ ሰባኪና አስተማሪ እንደነበር ለመገንዘብ ያስችለናል።a—ሮሜ 11:13
እንደ ሁኔታው አቀራረቡን ይለዋውጥ የነበረ አገልጋይ
6. ጳውሎስ የአድማጮቹን ሁኔታ ያስተውል የነበረው እንዴት ነው? ይህን ማድረጉስ ምን ውጤት አስገኘለት?
6 ጳውሎስ ለአድማጮቹ አመለካከትና ሁኔታ ትኩረት የሚሰጥ አስተዋይ ሰው ነበር። በዳግማዊ አግሪጳ ፊት በቀረበ ጊዜ ንጉሡ ‘የአይሁድን ልማድና ክርክር ሁሉ በሚገባ እንደሚያውቅ’ ገልጿል። ከዚያም አግሪጳ እንደሚያምንባቸው የሚያውቃቸውን ነገሮች በዘዴ በመጥቀስ ጥሩ አድርጎ የሚረዳቸውን ጉዳዮች አንስቶ አወያየው። ጳውሎስ ያቀረባቸው ማስረጃዎች ግልጽና አሳማኝ ስለነበሩ አግሪጳ “አንተ እኮ በዚህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ክርስቲያን ልታደርገኝ ነው!” ብሎ እስከመናገር ደርሷል።—የሐዋርያት ሥራ 26:2, 3, 27, 28 የ1980 ትርጉም
7. ጳውሎስ በልስጥራን ለተሰበሰበው ሕዝብ በሚሰብክበት ጊዜ አቀራረቡን የለወጠው እንዴት ነው?
7 ከዚህም በላይ ጳውሎስ እንደ አድማጮቹ ሁኔታ አቀራረቡን የሚለውጥ ሰው ነበር። በልስጥራን ከተማ ሕዝቡ እርሱንና በርናባስን እንደ አማልክት ቆጥሮ እንዳያመልካቸው ለማሳመን ለየት ያለ አቀራረብ ተጠቅሞ እንደነበር ልብ በል። እነዚህ የሊቃኦንያ ቋንቋ ተናጋሪዎች ከአጠቃላዩ ሕዝብ አንጻር ሲታዩ ብዙም ያልተማሩና አጉል እምነት የሚያጠቃቸው ሰዎች እንደነበሩ ይነገራል። ጳውሎስ እውነተኛው አምላክ የበላይ መሆኑን ለማስረዳት ፍጥረትንና የተፈጥሮ ስጦታዎችን ማስረጃ አድርጎ እንደገለጸላቸው በሐዋርያት ሥራ 14:14-18 ላይ ተዘግቧል። ያቀረበው ሐሳብ ለመረዳት ከባድ ስላልነበረ ሕዝቡ ለጳውሎስና ለበርናባስ ‘መሠዋቱን ተወው።’
8. ጳውሎስ የተበሳጨባቸው ጊዜያት ቢኖሩም ከሚያጋጥሙት ሁኔታዎች ጋር በሚስማማ መንገድ ራሱን መለወጥ እንደማይከብደው ያሳየው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
8 እርግጥ ጳውሎስ ፍጹም ሰው አልነበረም፤ እንዲያውም በአንዳንድ ምክንያቶች የተበሳጨባቸው ጊዜያት አሉ። ለምሳሌ ያህል በአንድ ወቅት ኢፍትሐዊ በሆነና በሚያዋርድ መልኩ በተመታ ጊዜ ሐናንያ በሚባል አይሁዳዊ ላይ ኃይለ ቃል ሰንዝሮ ነበር። ነገር ግን ሊቀ ካህናቱን እየተሳደበ መሆኑ ሲነገረው ወዲያውኑ ይቅርታ ጠየቀ። (የሐዋርያት ሥራ 23:1-5) በአቴና እያለ መጀመሪያ ላይ ‘ከተማዪቱ በጣዖት የተሞላች መሆኗን ሲያይ ተበሳጭቶ’ ነበር። ሆኖም በማርስ ኮረብታ ላይ ሆኖ ንግግር ባቀረበበት ጊዜ ምንም የብስጭት መንፈስ አልታየበትም። እንዲያውም “ለማይታወቅ አምላክ” የሚል ጽሑፍ ያለበትን መሠዊያ በመጥቀስና አንዱ ባለቅኔ ያለውን በማንሳት ከአቴናውያን ጋር በሚስማማበት ነጥብ ላይ ንግግር አድርጓል።—የሐዋርያት ሥራ 17:16-28
9. ጳውሎስ የተለያዩ ሰዎችን ሲያነጋግር ዘዴ ይጠቀም የነበረው እንዴት ነው?
9 ጳውሎስ ከተለያዩ ሰዎች ጋር በሚነጋገርበት ጊዜ የሚያስገርሙ ዘዴዎችን ይጠቀም ነበር። በአድማጮቹ አመለካከት ላይ ተጽዕኖ ያደረገውን ባሕልና የአካባቢ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገባል። በሮም ለሚገኙ ክርስቲያኖች ደብዳቤ በጻፈበት ወቅት በዘመኑ ኃያል መንግሥት ዋና ከተማ ውስጥ እንደሚኖሩ በሚገባ ያውቅ ነበር። ለእነዚህ ክርስቲያኖች የጻፈው ደብዳቤ ዋና ነጥብ የአዳም ኃጢአት ያለው አቋምን የማበላሸት ኃይል በክርስቶስ የማዳን ኃይል ድል እንደሚነሳ የሚገልጽ ነው። ሮማውያን ክርስቲያኖችንና በአካባቢያቸው የነበሩትን ሰዎች ልብ ለመንካት ሲል በሚገባቸው አነጋገር አስረድቷቸዋል።—ሮሜ 1:4፤ 5:14, 15
10, 11. ጳውሎስ ለአድማጮቹ ተስማሚ ምሳሌ ያቀርብ የነበረው እንዴት ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)
10 ጳውሎስ ጥልቅ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ለአድማጮቹ መግለጽ በሚፈልግበት ጊዜ ምን ያደርግ ነበር? ይህ ሐዋርያ ውስብስብ መንፈሳዊ ትምህርቶችን ለማስረዳት የተለመዱና በቀላሉ የሚገቡ ምሳሌዎችን በመጠቀም ረገድ የተዋጣለት ነበር። ለምሳሌ ያህል የሮም ነዋሪዎች በመላው የሮም ግዛት ስለነበረው የባሪያ ሥርዓት በደንብ እንደሚያውቁ አስተውሎ ነበር። እንዲያውም ጳውሎስ ከጻፈላቸው ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ባሮች ሳይሆኑ አይቀሩም። ስለዚህ አንድ ሰው ለኃጢአት ወይም ለጽድቅ የመገዛት ምርጫ እንዳለው በጻፈበት ወቅት ሐሳቡን ይበልጥ ለማጠናከር ባርነትን እንደ ምሳሌ አድርጎ ተጠቅሟል።—ሮሜ 6:16-20
11 “ሮማውያን ባሮቻቸውን በነፃ ሊያሰናብቷቸው ይችሉ ነበር፤ ወይም ባሪያው ራሱ ለጌታው ገንዘብ በመክፈል ነፃ መውጣት ይችል ነበር። እንዲሁም ባሪያው ለአማልክት ከተሰጠ ነፃ ሊወጣ ይችላል” በማለት አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ ገልጿል። ነፃ የወጣው ባሪያ ለጌታው በገንዘብ ተቀጥሮ ሊሠራ ይችል ነበር። ጳውሎስ ግለሰቦች ኃጢአትን አሊያም ጽድቅን ጌታቸው አድርገው መምረጥ እንደሚችሉ በጻፈላቸው ጊዜ ከላይ የተጠቀሰውን ልማድ በተዘዋዋሪ መጥቀሱ ሳይሆን አይቀርም። በወቅቱ በሮም የሚኖሩ ክርስቲያኖች ከኃጢአት ነፃ የወጡ የአምላክ ንብረቶች ነበሩ። እነዚህ ክርስቲያኖች አምላክን የማገልገል ነፃነት ቢያገኙም፣ ከፈለጉ የቀድሞ ጌታቸውን ኃጢአትን ለማገልገል የመምረጥ መብት ነበራቸው። ይህ ምሳሌ ቀላል ቢሆንም በደንብ ስለሚታወቅ በሮም የነበሩ ክርስቲያኖች ‘የማገለግለው የትኛውን ጌታ ነው?’ ብለው እንዲጠይቁ ያነሳሳቸዋል።b
ከጳውሎስ ምሳሌ መማር
12, 13. (ሀ) የተለያዩ አድማጮቻችንን ልብ ለመንካት ምን ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል? (ለ) የተለያየ ሁኔታ ላላቸው ሰዎች ለመስበክ ውጤታማ ሆኖ ያገኘኸው ዘዴ ምንድን ነው?
12 እንደ ጳውሎስ ሁሉ እኛም የተለያዩ አድማጮቻችንን ልብ ለመንካት አስተዋይ፣ ዘዴኛና እንደ ሁኔታው አቀራረባችንን የምንለውጥ መሆን አለብን። አድማጮቻችን ስለ ምሥራቹ እንዲገነዘቡ ለመርዳት ስንል እንዲያው ኃላፊነታችንን ለመወጣት ያህል ሰዎችን ከማነጋገር፣ የተዘጋጀንበትን መልእክት ከማስተላለፍ ወይም አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ከመስጠት የበለጠ ነገር ማድረግ እንሻለን። ፍላጎታቸውንና ጭንቀታቸውን፣ የሚወዱትንና የሚጠሉትን ነገር እንዲሁም የሚያስፈራቸውን ጉዳይና ጭፍን ጥላቻ ይኖራቸው እንደሆነ ለመረዳት እንጥራለን። ይህ ብዙ ማሰብና ከፍተኛ ጥረት ማድረግ የሚጠይቅ ቢሆንም በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የመንግሥቱ ሰባኪዎች በትጋት እንዲህ እያደረጉ ነው። ለምሳሌ ያህል በሃንጋሪ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ እንደሚከተለው ብሏል:- “ወንድሞች የሌላ አገር ዜጎችን ባሕልና የአኗኗር ዘይቤ ያከብራሉ፤ እንዲሁም እነዚህ የውጪ ዜጎች በአገሩ ባሕል መሠረት እንዲኖሩ አይጠብቁባቸውም።” በሌላ ቦታ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮችም ተመሳሳይ ነገር ለማድረግ ይጥራሉ።
13 በሩቅ ምሥራቅ በሚገኝ አንድ አገር ውስጥ አብዛኞቹ ሰዎች የጤንነት፣ ልጆችን የማሳደግና የትምህርት ጉዳይ በጣም ያሳስባቸዋል። በዚያ የሚገኙ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ስለ ዓለም ሁኔታ መበላሸት ወይም ውስብስብ ስለሆኑ ማኅበራዊ ችግሮች ከማንሳት ይልቅ ከላይ የተጠቀሱትን ነገሮች አንስተው ያወያዩዋቸዋል። በተመሳሳይ በአንድ ትልቅ የዩናይትድ ስቴትስ ከተማ የሚገኙ የምሥራቹ ሰባኪዎች፣ በክልላቸው ውስጥ ባሉ አንዳንድ ቦታዎች የሚገኙ ሰዎች እንደ ሙስና፣ የትራፊክ መጨናነቅና ዓመጽ ያሉ ነገሮች እንደሚያሳስቧቸው አስተውለዋል። የይሖዋ ምሥክሮች እነዚህን ጉዳዮች የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ለመጀመር ጥሩ አድርገው ይጠቀሙባቸዋል። ውጤታማ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች ምንም ዓይነት ርዕስ ቢመርጡ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች በሥራ ላይ ማዋል አሁን ለሚያስገኘው ጥቅምና አምላክ ለወደፊቱ ላዘጋጀው አስደሳች ተስፋ አጽንዖት በመስጠት ሁልጊዜ ገንቢና አበረታች ሐሳብ ለማካፈል ይጥራሉ።—ኢሳይያስ 48:17, 18፤ 52:7
14. የምንጠቀምባቸውን አቀራረቦች ሰዎች ካላቸው የተለያየ ፍላጎትና ሁኔታ ጋር ማስማማት የምንችልባቸውን መንገዶች ግለጽ።
14 በተጨማሪም ሰዎች ሰፊ የሆነ የባሕል፣ የትምህርትና የሃይማኖት ልዩነት ስለሚኖራቸው በአገልግሎት ላይ የምንጠቀምባቸውን አቀራረቦች መቀያየራችን ጠቃሚ ነው። ፈጣሪ እንዳለ ለሚያምኑ ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስን ለማይቀበሉ ሰዎች የምንጠቀምበት አቀራረብና አምላክ የለም የሚሉ ሰዎችን የምናነጋግርበት መንገድ የተለያየ ነው። ሃይማኖታዊ ጽሑፎች ሁሉ ፕሮፖጋንዳ መንዣ እንደሆኑ ለሚያምን ሰውና የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ለሚቀበል ሰው የምንጠቀምበት መግቢያም ቢሆን ተመሳሳይ አይደለም። እንዲሁም የተለያየ የትምህርት ደረጃ ያላቸውን ሰዎች በምናነጋግርበት ጊዜ እንደ ሁኔታው ለውጥ ማድረግ ያስፈልገናል። ጥሩ ችሎታ ያላቸው አስተማሪዎች በወቅቱ ላለው ሁኔታ ተስማሚ የሆኑ ማስረጃዎችንና ምሳሌዎችን ይጠቀማሉ።—1 ዮሐንስ 5:20
አዳዲስ ክርስቲያኖችን መርዳት
15, 16. አዳዲስ ክርስቲያኖች ሥልጠና ማግኘታቸው አስፈላጊ የሆነው ከምን የተነሳ ነው?
15 ጳውሎስ የሚያሳስበው የራሱን የማስተማሪያ ዘዴዎች የማሻሻሉ ጉዳይ ብቻ አልነበረም። እንደ ጢሞቴዎስና ቲቶ ያሉ ወጣቶች ውጤታማ አገልጋዮች እንዲሆኑ ሥልጠናና መመሪያ ማግኘት እንደሚገባቸው ተሰምቶት ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 2:2፤ 3:10, 14፤ ቲቶ 1:4) ዛሬም በተመሳሳይ ሥልጠና መስጠትም ሆነ መቀበል አንገብጋቢ ጉዳይ ነው።
16 በ1914 በዓለም ዙሪያ ወደ 5,000 የሚጠጉ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ነበሩ፤ ዛሬ ግን 5,000 ገደማ የሚሆኑ አዳዲስ ሰዎች በየሳምንቱ ይጠመቃሉ! (ኢሳይያስ 54:2, 3፤ የሐዋርያት ሥራ 11:21) አዳዲሶች በክርስቲያን ጉባኤ መሰብሰብ ሲጀምሩና በአገልግሎት መካፈል ሲፈልጉ ሥልጠናና መመሪያ ማግኘት ይኖርባቸዋል። (ገላትያ 6:6) ደቀ መዛሙርትን በማስተማርና በማሠልጠን ረገድ የጌታ ኢየሱስን ዘዴዎች መጠቀሙ በጣም አስፈላጊ ነው።c
17, 18. አዲሶች በልበ ሙሉነት በአገልግሎት እንዲካፈሉ እንዴት መርዳት እንችላለን?
17 ኢየሱስ ሐዋርያቱን ብዙ ሕዝብ ወደተሰበሰበበት ቦታ ወስዶ ትምህርት እንዲሰጡ አልጠየቃቸውም። በመጀመሪያ የስብከቱ ሥራ ያስፈለገበትን ምክንያት ከመግለጹም በተጨማሪ ስለ አገልግሎታቸው ሳያቋርጡ እንዲጸልዩ አበረታቷቸዋል። ከዚያም ሦስት መሠረታዊ ዝግጅቶችን አድርጎላቸዋል፤ እነርሱም የአገልግሎት ጓደኛ፣ የአገልግሎት ክልልና የሚሰብኩት መልእክት ናቸው። (ማቴዎስ 9:35-38፤ 10:5-7፤ ማርቆስ 6:7፤ ሉቃስ 9:2, 6) እኛም ተመሳሳይ ነገር ማድረግ እንችላለን። የምንረዳው ልጃችንንም ይሁን አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ወይም ደግሞ ለተወሰነ ጊዜ አገልግሎት አቋርጦ የነበረን ሰው እነዚህን መንገዶች ተጠቅመን ሥልጠና መስጠታችን ተገቢ ነው።
18 አዲሶች የመንግሥቱን መልእክት በልበ ሙሉነት ለመስበክ ሰፋ ያለ ሥልጠና ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። ቀላልና የሚማርክ አቀራረብ እንዲዘጋጁና ልምምድ እንዲያደርጉ ልትረዳቸው ትችላለህ? ከቤት ወደ ቤት ስታገለግሉ የመጀመሪያዎቹን ጥቂት ሰዎች አንተ ስታነጋግር እንዲመለከቱ አድርግ። አብረውት በውጊያ የተሰለፉትን ሰዎች “እኔን ተመልከቱ፤ የማደርገውንም አድርጉ” በማለት የተናገረውን የጌዴዎንን ምሳሌ መከተል ትችላለህ። (መሳፍንት 7:17) ከዚያ እነርሱም እንዲያናግሩ አጋጣሚ ስጣቸው። ላደረጉትም ጥረት ሞቅ ያለ ምስጋና አቅርብላቸው፤ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ ለመሻሻል የሚረዳቸውን አጠር ያለ አስተያየት ስጣቸው።
19. ሙሉ በሙሉ ‘አገልግሎትህን ለመፈጸም’ ስትጥር ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው?
19 ሙሉ በሙሉ ‘አገልግሎታችንን ለመፈጸም’ ስንል ሰዎችን በምናነጋግርበት ጊዜ አቀራረባችንን እንደ ሁኔታው ለመቀያየር ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል፤ አዳዲስ ክርስቲያኖችም እንዲሁ እንዲያደርጉ ማሠልጠን እንፈልጋለን። ግባችን መዳን የሚያስገኘውን የአምላክ እውቀት ማስተማር ነው፤ ይህ ግባችን ያለውን ጠቀሜታ ስንመረምር “አንዳንዶችን [እናድን] ዘንድ፣ ከሁሉም ጋር ሁሉን ነገር” ለመሆን ብርቱ ጥረት ማድረግ የሚያስቆጭ እንዳልሆነ እንገነዘባለን።—2 ጢሞቴዎስ 4:5፤ 1 ቆሮንቶስ 9:22
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ጳውሎስ በአገልግሎቱ እነዚህን ባሕርያት እንዴት እንዳሳየ ለመመልከት የሚከተሉትን ጥቅሶች አንብብ:- የሐዋርያት ሥራ 13:9, 16-42፤ 17:2-4፤ 18:1-4፤ 19:11-20፤ 20:34፤ ሮሜ 10:11-15፤ 2 ቆሮንቶስ 6:11-13
b በተጨማሪም ጳውሎስ በአምላክና በመንፈስ በተቀቡት ‘ልጆቹ’ መካከል ስለተመሠረተው አዲስ ዝምድና በሚያብራራበት ጊዜ በሮም ግዛት ውስጥ የሚኖሩ አንባቢዎች ጠንቅቀው የሚያውቁትን ሕግ ነክ ሐሳብ ተጠቅሞ ነበር። (ሮሜ 8:14-17) “ሮማውያን ያልወለዱትን ሰው እንደ ልጃቸው የመቀበል ልማድ ነበራቸው፤ ይህ ልማድ ስለ ቤተሰብ ካላቸው አመለካከት ጋር በቅርብ የተያያዘ ነው” በማለት ሴንት ፖል አት ሮም የተባለው መጽሐፍ ዘግቧል።
c በአሁኑ ጊዜ ሁሉም የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች አቅኚዎች ሌሎችን ይረዳሉ የተባለውን ዝግጅት ተግባራዊ እያደረጉ ነው። ይህ ዝግጅት የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ያካበቱትን ልምድና ያገኙትን ሥልጠና ብዙም ተሞክሮ የሌላቸው አስፋፊዎችን ለመርዳት እንዲጠቀሙበት ያስችላል።
ታስታውሳለህ?
• በአገልግሎታችን ጳውሎስን መምሰል የምንችለው በምን መንገዶች ነው?
• በአስተሳሰባችን ላይ ምን ዓይነት ለውጦች ማድረግ ሊያስፈልገን ይችላል?
• መልእክታችን ገንቢ እንዲሆን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
• አዳዲስ ክርስቲያኖች ልበ ሙሉ እንዲሆኑ ምን ማግኘት ያስፈልጋቸዋል?
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ሐዋርያው ጳውሎስ አስተዋይ፣ እንደ ሁኔታው አቀራረቡን የሚለውጥ እንዲሁም ዘዴኛ የሆነ ሰባኪና አስተማሪ ነበር
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ሦስት መሠረታዊ ዝግጅቶችን አድርጎላቸዋል፤ እነርሱም የአገልግሎት ጓደኛ፣ የአገልግሎት ክልልና የሚሰብኩት መልእክት ናቸው
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጳውሎስ እንደ ሁኔታው ለውጥ በማድረጉ የተለያዩ ዓይነት ሰዎችን ማነጋገር ችሏል
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ውጤታማ አገልጋዮች የአድማጮቻቸውን ባሕል ግምት ውስጥ ያስገባሉ
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እንደ ሁኔታው አቀራረባቸውን የሚለውጡ አገልጋዮች አዲሶች ለአገልግሎት ጥሩ ዝግጅት እንዲያደርጉ ይረዷቸዋል