የይሖዋን ክብር አውጁ
1 መዝሙራዊው “ምድር ሁሉ፤ ለእግዚአብሔር ዘምሩ። . . . ክብሩን በሕዝቦች መካከል፣ ድንቅ ሥራውንም በሰዎች ሁሉ ፊት ተናገሩ” ሲል አውጆአል። ይሖዋ ከዚህ በፊት ባደረጋቸው፣ አሁን በሚያደርጋቸው እንዲሁም ወደፊት አደርግላችኋለሁ ብሎ ቃል በገባልን ነገሮች ላይ ስናሰላስል ልባችን ክብሩን እንድናውጅ ይገፋፋናል!—መዝ. 96:1, 3
2 በአገልግሎታችን:- የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክን ስም የመሸከምና በምድር ሁሉ ላይ የማወጅ መብት አግኝተዋል። (ሚል. 1:11) ይህ ደግሞ የአምላክን ስም በማን አለብኝነት ከመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞቻቸው ውስጥ ካስወጡት የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ምንኛ የተለየ ነው! ሰዎች ከሚመጣው ታላቅ መከራ ለመዳን የአምላክን ስም በእምነት መጥራት ስለሚኖርባቸው ይህን ስም እንዲያውቁት የማድረጉ ሥራ እጅግ አጣዳፊ ነው። (ሮሜ 10:13-15) ከዚህም በተጨማሪ የምድር ነዋሪዎችን ጨምሮ የአጽናፈ ዓለሙ ሰላም የተመካው በአምላክ ስም መቀደስ ላይ ነው። በእርግጥም አምላክ የሚያከናውነው ማንኛውም ነገር ከስሙ ጋር ተያያዥነት አለው።
3 ‘እግዚአብሔር ታላቅ ነው፤ ውዳሴም የሚገባው ነው።’ ሆኖም ሰዎች “ለስሙ የሚገባ ክብርን ለእግዚአብሔር” እንዲሰጡ ስለ እርሱ እውነቱን ማወቅ አለባቸው። (መዝ. 96:4, 8) ይሁንና አንዳንዶች አምላክ መኖሩን ይክዳሉ። (መዝ. 14:1) ሌሎች ደግሞ አቅም የለውም አሊያም ስለ ሰው ልጅ ችግሮች ደንታ የለውም እያሉ ስሙን ያጠፋሉ። ልበ ቅን ሰዎች ስለ ፈጣሪያችን፣ ስለ ዓላማዎቹና ስለ ድንቅ ባሕርያቱ ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ በመርዳት የይሖዋን ክብር እናውጃለን።
4 በአኗኗራችን:- ከይሖዋ የጽድቅ ሥርዓቶች ጋር ተስማምተን ስንኖር እርሱን እናስከብራለን። ሰዎች የምናሳየውን መልካም ምግባር ማየታቸው አይቀርም። (1 ጴጥ. 2:12) ለምሳሌ ያህል፣ ሥርዓታማና ንጹሕ ሆነን መታየታችን ሌሎች ስለ እኛ ገንቢ አስተያየቶችን እንዲሰነዝሩ የሚያደርጋቸው ከመሆኑም ባሻገር በይሖዋ ቃል ውስጥ ከሚገኙ መመሪያዎች ጋር ተስማምቶ መኖር ስለሚያስገኛቸው ጥቅሞች ለመናገር አመቺ አጋጣሚ ሊከፍትልን ይችላል። (1 ጢሞ. 2:9, 10) ሌሎች ሰዎች ‘መልካም ሥራችንን አይተው በሰማይ ያለውን አባታችንን ሲያከብሩ’ መመልከት ምንኛ ያስደስታል!—ማቴ. 5:16
5 በቃላችንም ሆነ በተግባራችን ድንቅ የሆነውን አምላክ በየዕለቱ እናክብረው፤ እንዲህ ስናደርግ “ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ ስሙንም ባርኩ፤ ማዳኑንም ነጋ ጠባ አውሩ” ለሚለው ጥሪ ምላሽ እንሰጣለን።—መዝ. 96:2