አስተዋይ በመሆን ለሰዎች ልባዊ አሳቢነት አሳዩ
1 ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ የሰዎችን ፍላጎት ለይቶ በማወቅም ሆነ እርዳታ በመስጠት ረገድ የላቀ ችሎታ አላቸው። (2 ዜና 16:9፤ ማር. 6:34) በአገልግሎታችን ላይ የምናገኛቸውን ሰዎች ስሜት መረዳታችን እንዲሁም የሚያሳስቧቸውን ነገሮች ለይተን ማወቃችን ምሥራቹን የምንሰብክበትን መንገድ እንደሁኔታው ለመቀያየር ያስችለናል።
2 እያንዳንዱን ነገር አስተውሉ:- ኢየሱስ አስተዋይ ነበር። (ማር. 12:41-43፤ ሉቃስ 19:1-6) እኛም በተመሳሳይ ከቤት ወደ ቤት በምናገለግልበት ወቅት ሃይማኖታዊ ምስሎችን፣ መኪና ላይ የተለጠፉ አባባሎችን ወይም ግቢ ውስጥ መጫወቻዎችን ካየን ምሥራቹን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመመሥከር የሚያስችሉንን አጋጣሚዎች መፍጠር እንችላለን።
3 በአንድ ሰው ፊት ላይ የሚነበበው ስሜትና የሰውየው አጠቃላይ ሁኔታ ስለ አስተሳሰቡ የሚጠቁመው ነገር ይኖራል። (ምሳሌ 15:13) የሚወደውን ሰው በሞት በማጣቱ አሊያም በአንዳንድ ሁኔታዎች በመጨነቁ ማጽናኛ ያስፈልገው ይሆናል። ተስማሚ የሆኑ አንዳንድ ጥቅሶችን ብናካፍለው ሊደሰት ይችላል። (ምሳሌ 16:24) የቤቱ ባለቤት ለመውጣት ተቻኩሏል? ወይስ የሚያለቅስ ሕፃን ልጅ ታቅፏል? ከሆነ፣ ሌላ ጊዜ መጥተን ለመነጋገር ቀጠሮ መያዝ የተሻለ ይሆናል። የሰውየውን ስሜት ግምት ውስጥ አስገብተን ‘አሳቢነት’ ካሳየነው ተመልሰን ሄደን ስናነጋግረው ሊያዳምጠን ይችላል።—1 ጴጥ. 3:8
4 አቀራረባችሁን ከሁኔታዎች ጋር አስማሙ:- ሐዋርያው ጳውሎስ በአቴንስ ከተማ “ለማይታወቅ አምላክ” የቆመ አንድ መሰዊያ መኖሩን አስተዋለ። ይህ ደግሞ ምሥራቹን የሚሰብክበትን መንገድ መለወጥ እንዳለበት ስላስገነዘበው “ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እገልጽላችኋለሁ” አላቸው። ዘዴኛነት የተንጸባረቀበት የጳውሎስ አቀራረብ በዚያ የተገኙ አንዳንድ ሰዎች ለመንግሥቱ መልእክት ትኩረት እንዲሰጡና አማኞች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።—ሥራ 17:23, 34
5 እኛም እንዲሁ አስተዋይ መሆናችን የአንድን ሰው ስሜት ለይተን እንድናውቅ ስለሚረዳን አቀራረባችንን ከሁኔታዎች ጋር ማስማማት እንችላለን። የቤቱ ባለቤት የልቡን አውጥቶ እንዲናገር የሚገፋፉ ጥያቄዎችን ጠይቁ። የሰውየውን ፍላጎት ሊቀሰቅሱ የሚችሉ ጥቅሶችን ተጠቀሙ። (ምሳሌ 20:5) አስተዋይ መሆናችንና ለሰዎች ልባዊ አሳቢነት ማሳየታችን ምሥራቹን በተሳካ መንገድ እንድንሰብክ ያስችለናል።