የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በተባለው መጽሐፍ ጥናት ማስጀመር የሚቻልበት መንገድ
አብዛኞቻችን፣ ጥረት አድርገን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር ከቻልን ጥናቱን መምራት ያስደስተናል። ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለው አዲሱ መጽሐፍ በዚህ ረገድ ይረዳናል። በገጽ 3-7 ላይ ያለው መቅድም ጽሑፉን በመጠቀም አንድን የቤት ባለቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ለማስጀመር ታስቦ የተዘጋጀ ነው። ሌላው ቀርቶ በአገልግሎት ብዙም ተሞክሮ የሌላቸው አስፋፊዎችም ጥናት ለማስጀመር ቀላል ሆኖ ያገኙታል።
◼ ገጽ 3ን በመጠቀም ይህን አቀራረብ ልትሠራበት ትችላለህ:-
በአገልግሎት ክልልህ የምታገኛቸውን ሰዎች የሚያሳስባቸውን ዜና ላይ የሰሙትን ጉዳይ ወይም አንድ ችግር ከጠቀስህ በኋላ ለቤቱ ባለቤት በገጽ 3 ላይ ጎላ ተደርገው የተጻፉትን ጥያቄዎች አስነብበው፤ ቀጥሎም ሐሳብ እንዲሰጥ ጋብዘው። ከዚያም ገጽ 4-5ን አውጣና አሳየው።
◼ ወይም ደግሞ ገጽ 4ና 5 ላይ ያሉትን ነጥቦች በማጉላት ለመጀመር ትመርጥ ይሆናል:-
እንዲህ ልትል ትችላለህ:- “በሥዕሎቹ ላይ የሚታዩት ለውጦች በእውን ቢፈጸሙ በጣም አያስደስትም?” ወይም እንዲህ ብለህ ልትጠይቅ ትችላለህ:- “ከእነዚህ ተስፋዎች መካከል ሲፈጸም ለማየት የሚጓጉት የትኛውን ነው?” ከዚያም የሚሰጥህን መልስ በጥሞና አዳምጥ።
የቤቱ ባለቤት ከጥቅሶቹ አንዱ ትኩረቱን ከሳበው በዚህ ጉዳይ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ብሎ እንደሚያስተምር ለመግለጽ ከመጽሐፉ ውስጥ ይህንን ጉዳይ የሚያብራሩትን አንቀጾች መርጠህ አወያየው። (በዚህ አባሪ ላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት።) አንቀጾቹን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በምትመራበት መንገድ ሸፍናቸው። ይህንንም በመጀመሪያው ቀን በራፍ ላይ እንደቆማችሁ ከአምስት እስከ አሥር ደቂቃ በሚሆን ጊዜ ውስጥ ማድረግ ይቻላል።
◼ ሌላው አቀራረብ ደግሞ ገጽ 6ን በመጠቀም ግለሰቡ ሐሳቡን እንዲገልጽ ማድረግ ነው:-
ለቤቱ ባለቤት በገጽ 6 ላይ ከታች የሚገኙትን ጥያቄዎች ካስነበብከው በኋላ እንዲህ ብለህ ጠይቀው:- “ከዚህ ቀደም ከእነዚህ ጥያቄዎች መካከል የሚያሳስብዎት ነበር?” ከጥያቄዎቹ መካከል የአንዱን መልስ ማወቅ ከፈለገ በመጽሐፉ ውስጥ መልሱ የሚገኝባቸውን አንቀጾች አውጣ። (በዚህ አባሪ ላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት።) ትምህርቱን አንድ ላይ ከተወያያችሁበት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መራህ ማለት ነው።
◼ ገጽ 7ን ተጠቅመህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዴት እንደሚመራ ልታሳየው ትችላለህ:-
በገጹ ላይ ካለው አንቀጽ የመጀመሪያዎቹን ሦስት ዓረፍተ ነገሮች አንብብለት። ከዚያም ምዕራፍ 3ን ግለጥና አንቀጽ 1-3ን ተጠቅመህ ጥናቱ እንዴት እንደሚመራ አሳየው። በአንቀጽ 3 ላይ የቀረቡት ጥያቄዎች መልስ ምን እንደሆነ ለመወያየት ቀጠሮ ያዝ።
◼ ለተመላልሶ መጠየቅ ቀጠሮ መያዝ የሚቻልበት መንገድ:-
የመጀመሪያውን ቀን ጥናት እንደጨረስክ ውይይቱን ለመቀጠል ዝግጅት አድርግ። በቀላሉ እንዲህ ልትል ትችላለህ:- “በዚህች ትንሽ ደቂቃ ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ አቢይ ጉዳይ ላይ ምን እንደሚያስተምር አውቀናል። በሚቀጥለው ጊዜ [የምትወያዩበት አንድ ጥያቄ አንሣና] በዚህ ሐሳብ ላይ እንወያያለን። በሚቀጥለው ሳምንት በተመሳሳይ ሰዓት ብመጣ ይመቾታል?”
ይሖዋ ወደ ቀጠረው ቀን ይበልጥ እየቀረብን ስንመጣ እንድንሠራው ለሰጠን ሥራ እኛን ማስታጠቁን ይቀጥላል። (ማቴ. 28:19, 20፤ 2 ጢሞ. 3:17) በዚህ ግሩም የሆነ አዲስ መሣሪያ ውጤታማ በሆነ መንገድ በመጠቀም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እናስጀምር።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በገጽ 4-5 ላይ ያሉት ጥቅሶች የተብራሩበት ቦታ
◻ ራእይ 21:4 (ገጽ 27-28 አን. 1-3)
◻ ኢሳይያስ 33:24፤ 35:5, 6 (ገጽ 36 አን. 22)
◻ ዮሐንስ 5:28, 29 (ገጽ 72-73 አን. 17-19)
◻ መዝሙር 72:16 (ገጽ 34 አን. 19)
በገጽ 6 ላይ ያሉት ጥያቄዎች መልሳቸው የሚገኝበት ቦታ
◻ መከራና ሥቃይ የሚደርስብን ለምንድን ነው? (ገጽ 108-109 አን. 6-8)
◻ ኑሮ የሚያስከትልብንን ጭንቀት መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው? (ገጽ 184-185 አን. 1-3)
◻ የቤተሰባችንን ሕይወት አስደሳች ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? (ገጽ 142 አን. 20)
◻ ስንሞት ምን እንሆናለን? (ገጽ 58-59 አን. 5-6)
◻ በሞት ያጣናቸውን ሰዎች ዳግመኛ እናገኛቸው ይሆን? (ገጽ 72-73 አን. 17-19)
◻ አምላክ የወደፊቱን ጊዜ አስመልክቶ ቃል የገባቸውን ነገሮች እንደሚፈጽም እንዴት እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን? (ገጽ 25 አን. 17)