መጽሔት የምናበረክትላቸውን ሰዎች ጥናት ማስጀመር የምንችለው እንዴት ነው?
1. መጽሔቶችን ስናበረክት ግባችን ምንድን ነው?
1 አብዛኛውን ጊዜ ቅዳሜ በአገልግሎት ላይ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን እናበረክታለን። ይሁን እንጂ ይህ፣ ልበ ቅን ለሆኑ ሰዎች እውነትን ለማስተማር ያለንን ግብ ለማሳካት የምንወስደው የመጀመሪያ እርምጃ ነው። በተመላልሶ መጠየቅ ወቅት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ ማበርከትና በዚህ መጽሐፍ ተጠቅመን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር ስለምንችልበት መንገድ የሚገልጹ አንዳንድ ሐሳቦች ከዚህ በታች ቀርበዋል። እነዚህ አቀራረቦች ለክልላችሁ ተስማሚ ሊሆኑ ስለሚችሉ ሐሳቡን በራሳችሁ አባባል ለመናገር ሞክሩ። ውጤታማ ሆኖ ያገኛችሁት ሌላ መንገድ ካለ መጠቀም ትችላላችሁ።
2. የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በተባለው መጽሐፍ መግቢያ ላይ የሚገኙትን ገጾች ጥናት ለማስጀመር እንዴት ልንጠቀምባቸው እንችላለን?
2 በመጽሐፉ መግቢያ ላይ የሚገኙትን ገጾች ተጠቀሙ:- ተመልሳችሁ ስትሄዱ እንዲህ ማለት ትችላላችሁ:- “ባለፈው ጊዜ ትቼልዎት የሄድኩት መጽሔት ለመጽሐፍ ቅዱስ ትኩረት እንዲሰጡ የሚያበረታታ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምን እንደሆነ እስቲ ይመልከቱ።” ከዚያም ኢሳይያስ 48:17, 18ን፣ ዮሐንስ 17:3ን ወይም ከእነዚህ ጋር የሚስማማ ሌላ ጥቅስ አንብቡ። ከዚያም ለቤቱ ባለቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ አስተዋውቃችሁ አንድ ቅጂ ስጡት። ቀጥሎም እንደሚከተለው ማለት ትችላላችሁ:-
◼ “መጽሐፍ ቅዱስ የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ አስተማማኝ ተስፋ ይሰጠናል።” ለቤቱ ባለቤት ገጽ 4 እና 5ን ካሳያችሁት በኋላ “ከእነዚህ ተስፋዎች መካከል ሲፈጸም ለማየት የሚጓጉት የትኛውን ነው?” ብላችሁ ጠይቁት። ከዚያም እሱ የመረጠውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ተስፋ የሚያብራራውን ምዕራፍ አውጥታችሁ ፈቃደኛ ከሆነ አንድ ወይም ሁለት አንቀጾችን በአጭሩ አወያዩት።
◼ ወይም እንዲህ ማለት ትችላላችሁ:- “መጽሐፍ ቅዱስ በሕይወታችን ውስጥ ለሚነሱ በጣም አስፈላጊ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።” ገጽ 6 ላይ የሚገኙትን ጥያቄዎች አሳዩት። ከዚያም ከታች ከሰፈሩት ጥያቄዎች መካከል ከዚህ ቀደም ያሳስበው የነበረው የቱ እንደሆነ ጠይቁት። ቀጥሎ ከመጽሐፉ ውስጥ መልሱ የሚገኝበትን ምዕራፍ አውጥታችሁ አንድ ወይም ሁለት አንቀጾችን በአጭሩ አወያዩት።
◼ ወይም በማውጫው ላይ ከሰፈሩት ርዕሶች መካከል አንዳንዶቹን ጠቆም ካደረጋችሁት በኋላ ስለ የትኛው ጉዳይ ማወቅ እንደሚፈልግ ጠይቁት። ከዚያም የመረጠውን ምዕራፍ አውጥታችሁ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዴት እንደሚካሄድ በአጭሩ አሳዩት።
3. (ሀ) እየተባባሱ ስለመጡት የዓለም ሁኔታዎች (ለ) ስለ ቤተሰብ ሁኔታ (ሐ) መጽሐፍ ቅዱስ እምነት የሚጣልበት መጽሐፍ ስለመሆኑ፣ የሚያብራሩ መጽሔቶችን ካበረከትን በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር የምንችለው እንዴት ነው?
3 በመጀመሪያው ቀን ጥያቄ በመጠየቅ ለተመላልሶ መሠረት ጣሉ:- ሌላው አማራጭ ደግሞ በመጀመሪያው ቀን ለተመላልሶ መጠየቅ መሠረት መጣል ነው። የቤቱ ባለቤት መጽሔቶችን ከወሰደ በኋላ አንድ ጥያቄ ጠይቁት፤ ከዚያም ጥያቄውን በሚቀጥለው ጊዜ እንደምትመልሱለት ንገሩት። ቁርጥ ያለ ቀጠሮ ለመያዝ ጥረት አድርጉ እንዲሁም ቀጠሯችሁን አክብሩ። (ማቴ. 5:37) ተመልሳችሁ ስትሄዱ ለቤቱ ባለቤት ባለፈው ጊዜ ያነሳችሁትን ጥያቄ አስታውሱትና መልሱን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ከተባለው መጽሐፍ ላይ ካነበባችሁለት በኋላ በአጭሩ አወያዩት። ከዚያም ግለሰቡ መጽሐፉን ይዞ መከታተል እንዲችል አንድ ቅጂ ስጡት። ከዚህ በታች አንዳንድ ምሳሌዎች ቀርበዋል:-
◼ የሰጣችሁት መጽሔት የዓለም ሁኔታዎች እየተባባሱ ስለመምጣታቸው የሚያብራራ ከሆነ እንዲህ ማለት ትችላላችሁ:- “በሚቀጥለው ጊዜ አምላክ በምድር ላይ የሚያመጣቸውን ለውጦች በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ በሚሰጠው ማብራሪያ ላይ ውይይት ማድረግ እንችላለን።” ተመልሳችሁ ስትሄዱ ገጽ 4 እና 5 ላይ በሚገኙት ሐሳቦች ተጠቀሙ። ወይም “አሳዛኝ መከራዎች እንዲደርሱ የአምላክ ፈቃድ ነው?” የሚል ጥያቄ ካነሳችሁ በኋላ ተመላልሶ መጠየቅ ስታደርጉ ለቤቱ ባለቤት ምዕራፍ 1 አንቀጽ 7 እና 8 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ አወያዩት።
◼ የሰጣችሁት መጽሔት ስለ ቤተሰብ ሁኔታ የሚያብራራ ከሆነ ተሰናብታችሁት ከመሄዳችሁ በፊት እንዲህ ማለት ትችላላችሁ:- “የቤተሰብ ሕይወት ደስታ የሰፈነበት እንዲሆን እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ምን ማድረግ ይችላል?” ተመልሳችሁ ስትሄዱ ምዕራፍ 14 አንቀጽ 4 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ አወያዩት።
◼ የሰጣችሁት መጽሔት መጽሐፍ ቅዱስ እምነት የሚጣልበት መጽሐፍ ስለመሆኑ የሚያብራራ ከሆነ በሚቀጥለው ጊዜ ለምታደርጉት ውይይት እንዲረዳችሁ የሚከተለውን ጥያቄ ጠይቁት:- “መጽሐፍ ቅዱስ ከሳይንስ አንጻር ትክክል ነው?” ተመላልሶ መጠየቅ በምታደርጉበት ወቅት ምዕራፍ 2 አንቀጽ 8 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ አወያዩት።
4. የቤቱ ባለቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ ለመውሰድ ፍላጎት ከሌለው ምን ማድረግ ይኖርብናል?
4 ሁልጊዜ ውይይታችሁን ስትጨርሱ በቀጣዩ ጊዜ የምትመልሱለትን ሌላ ጥያቄ ጠይቁት። ቋሚ ጥናት ከተጀመረ መጽሐፉን ከመጀመሪያው አንስታችሁ አስጠኑት። የቤቱ ባለቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ ባይፈልግስ? መጽሔቶችን ይዛችሁለት መሄዳችሁንና ቅዱስ ጽሑፋዊ ውይይት ማድረጋችሁን አታቋርጡ። ፍላጎቱን እያሳደጋችሁ የምትሄዱ ከሆነ ውሎ አድሮ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ፈቃደኛ ሊሆን ይችላል።
5. ለሰዎች መጽሔቶችን ከማበርከት የበለጠ ነገር ማድረግ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
5 መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች አንድ ሰው ትክክለኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ለመማር ፍላጎቱን ያነሳሱ ይሆናል። በመሆኑም መጽሔት የሚወስዱ ሰዎችን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ልዩ ጥረት አድርጉ። በዚህ መንገድ ኢየሱስ፣ ሰዎችን ‘እያስተማርን ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ’ የሰጠንን ትእዛዝ ተግባራዊ እናደርጋለን።—ማቴ. 28:19, 20