‘ደስተኛ የሆነውን አምላካችንን’ ይሖዋን ምሰሉ
1 ይሖዋ ሰዎች ደስተኞች እንዲሆኑ ይፈልጋል። ቃሉ እርሱ ለሰው ልጆች ያዘጋጃቸውን አስደናቂ በረከቶች በጉጉት እንድንጠባበቅ ይረዳናል። (ኢሳ. 65:21-25) ‘የደስተኛውን አምላክ የክብር ወንጌል’ መስበክ እንደሚያስደስተን ለሌሎች በግልጽ ሊታይ ይገባል። (1 ጢሞ. 1:11 NW) ስለ አምላክ መንግሥት ምሥራች የምንናገርበት መንገድ ለእውነት ፍቅር እንዳለን እንዲሁም ለምናነጋግራቸው ሰዎች ከልብ እንደምናስብ የሚያንጸባርቅ መሆን አለበት።—ሮሜ 1:14-16
2 ሁልጊዜ ደስተኛ ሆኖ መኖር አስቸጋሪ እንደሆነ የታወቀ ነው። በአንዳንድ የአገልግሎት ክልሎች ውስጥ ለመንግሥቱ መልእክት ጥሩ ምላሽ የሚሰጡት ሰዎች ጥቂት ናቸው። እንዲሁም በሕይወታችን ውስጥ አስቸጋሪ ሁኔታ የሚያጋጥመን ጊዜ ይኖራል። በአካባቢያችን የሚኖሩ ሰዎች የምንሰብከውን የአምላክ መንግሥት ምሥራች መስማታቸው ብሎም ትክክለኛውን ነገር መረዳታቸው ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ማወቃችን የደስተኝነት መንፈሳችንን ጠብቀን እንድንኖር ይረዳናል። (ሮሜ 10:13, 14, 17) በዚህ ጉዳይ ላይ ማሰላሰላችን ይሖዋ ሰዎች እንዲድኑ ያዘጋጀውን የምሕረት ዝግጅት በደስታ ማወጃችንን እንድንቀጥል ይረዳናል።
3 አዎንታዊ በሆኑ ነገሮች ላይ አተኩሩ:- እኛም ብንሆን ለምንናገረው ነገር ትኩረት መስጠት አለብን። ምንም እንኳ ከሰዎች ጋር ውይይት ስንጀምር የሚያሳስባቸውን አንድ ችግር ወይም ዜና የምንጠቅስ ቢሆንም ሳያስፈልግ አሉታዊ በሆኑ ነገሮች ላይ ማተኮር የለብንም። ተልእኳችን ‘መልካም ዜናን ማብሰር’ ነው። (ኢሳ. 52:7፤ ሮሜ 10:15) ይህ የምሥራች የተመሠረተው አምላክ ወደፊት አመጣዋለሁ ብሎ በገባው ተስፋ ላይ ነው። (2 ጴጥ. 3:13) ይህንን በአእምሯችን ይዘን መጽሐፍ ቅዱስን በመጠቀም ‘የተሰበረ ልብ ያላቸውን እንጠግናለን።’ (ኢሳ. 61:1, 2) ይህ ደግሞ ሁላችንም የደስተኝነት መንፈስ እንዲሁም አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖረን ያደርጋል።
4 በስብከቱ ሥራ ስንካፈል ሰዎች የደስተኝነት መንፈስ እንዳለን በቀላሉ መገንዘባቸው አይቀርም። ስለዚህ በአገልግሎት ክልላችን ለምናገኛቸው ሰዎች የመንግሥቱን ምሥራች በምንናገርበት ጊዜ ‘ደስተኛ የሆነውን የአምላካችን’ የይሖዋን ባሕርይ ምንጊዜም እናንጸባርቅ።