መልካሙን የምሥራች እንሰብካለን
1 “መልካሙን የምሥራች” ለሌሎች የመስበክ ኃላፊነት መቀበላችን እንዴት ያለ ግሩም መብት ነው! (ሮሜ 10:15) በሁከትና በተስፋ መቁረጥ ተከበው ለሚኖሩ ሰዎች አስደሳች መልእክት እናካፍላለን። ሰዎች ‘የመልካም ወሬ ምሥራች’ እንደያዝን እንዲገነዘቡ እንዴት ልንረዳቸው እንችላለን?—ኢሳ. 52:7
2 አዎንታዊ መልእክት አዘጋጁ:- አገልግሎት ላይ ከሰዎች ጋር ስንነጋገር በመልካም ነገሮች ላይ ትኩረት ካደረግን ጥሩ ውጤት እናገኛለን። በመሆኑም አቀራረባችንን በምንዘጋጅበትም ሆነ የምናበረክተውን ጽሑፍ በምንከልስበት ጊዜ በመልእክቱ አዎንታዊ ገጽታ ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልገናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን ተስፋችንን በልበ ሙሉነትና በግለት በመናገር አበረታች ውጤቶችን ልንጠብቅ እንችላለን።—ምሳሌ 25:11
3 ሰዎች እየተባባሱ በመሄድ ላይ ባሉት የዓለም ሁኔታዎች ምን ያህል እየተነኩ እንዳሉ ሲናገሩ ስንሰማ ብናዝንላቸውም ለሰው ልጅ ችግሮች እውነተኛ መፍትሔ የሚያስገኘው የአምላክ መንግሥት እንደሆነ ልንጠቁማቸው ይገባናል። ሌላው ቀርቶ ስለ መጪው የይሖዋ ‘የበቀል ቀን’ በምንናገርበት ጊዜ እንኳ ይህ መልእክት በእርግጥም “ለድሆች [“የዋሆች፣” NW ] የምሥራች” ነው ሊባል የሚችለው እንዴት እንደሆነ ማስረዳት አለብን። (ኢሳ. 61:1, 2) ይሖዋ የሚወስደው ማንኛውም እርምጃ በመጨረሻ ታላቅ ደስታና እጅግ የተሻለ ውጤት እንደሚያስገኝ ለአድማጮቻችን ልናረጋግጥላቸው እንችላለን።
4 እውነትን ከልብ በመነጨ ደስታ አቅርብ:- ሰዎች በፊታችን ላይ የሚነበበውን የደስታ ስሜት ሲመለከቱና በድምፃችን ቃና የሚንጸባረቀውን የመተማመን መንፈስ ሲያስተውሉ የበለጠ ጆሮአቸውን ይሰጣሉ። ብሩህ አመለካከት የምናንጸባርቅ ከሆነ አድማጮቻችን ‘በተስፋው እንደተደሰትን’ ይገነዘባሉ። (ሮሜ 12:12) በዚህ ምክንያት ምሥራቹን ወደ መቀበል የበለጠ ሊያዘነብሉ ይችላሉ። በእርግጥም በሁሉም የአገልግሎታችን ገጽታዎች ምንጊዜም አዎንታዊና ደስተኛ መንፈስ የምናንጸባርቅበት በቂ ምክንያት አለን።
5 የምሥራቹ አገልጋዮች በመሆን የምናከናውነው ነገር እንዲሁ መልእክት የማድረስ ጉዳይ ብቻ አይደለም። ስብከታችን አሁንም ሆነ ወደፊት የተሻለ ሕይወት መምራት እንደሚቻል እርግጠኛ ተስፋ ይሰጣል። (1 ጢሞ. 4:8) እያንዳንዱን ሰው ቀርበን ስናነጋግር ያለን አዎንታዊ አመለካከት በምንናገረው ነገር በግልጽ ይንጸባረቅና ሰዎች ምሥራቹን እንዲቀበሉ ይረዳል። ምን እንደምንናገርና እንዴት እንደምንናገር በጥንቃቄ በማሰብ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች የምንሰብከውን አስደሳች መልካም ምሥራች እንዲቀበሉ እናነሳሳቸው!