ያለ አድልዎ በመስበክ ለሰዎች ልባዊ አሳቢነት አሳዩ
1 ሐዋርያው ዮሐንስ፣ አንድ መልአክ በሰማይ መካከል እየበረረ “ለሕዝብ፣ ለነገድ፣ ለቋንቋና ለወገን ሁሉ” የዘላለም ወንጌል ሲሰብክ በራእይ ተመልክቶ ነበር። (ራእይ 14:6) እኛስ ያለ አድልዎ በመስበክ ረገድ የመልአኩን ምሳሌ እንከተላለን? ለእኛ ባይታወቀንም የምናዳላ ወይም ጭፍን ጥላቻ የምናሳይ ልንሆን እንችላለን። ለምናገኛቸው ሰዎች ያለን አመለካከት ምሥራቹን በምንናገርበት መንገድ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። በመሆኑም ከእኛ የተለየ አስተዳደግ ላላቸው ሰዎች በምንሰብክበት ጊዜ ከልብ የመነጨ ፍቅራዊ አሳቢነት ማሳየት ይኖርብናል።
2 ስለ ክልላችሁ አስቡ:- በክልላችሁ ውስጥ ከውጭ አገር የመጡ ሰዎች ወይም ስደተኞች ይኖራሉ? ለምሳሌ በክልላችን ውስጥ ለተለያዩ ሥራዎች የመጡ ብዙ ቻይናውያን ይገኛሉ። እነዚህ ሰዎች በቀላሉ ችላ ሊባሉ ይችላሉ። እነዚህን ሰዎች ፈልጋችሁ ለማግኘትና ስለ እነርሱ በበለጠ ለማወቅ ጥረት አድርጉ። የሚያስፈልጓቸውና የሚያሳስቧቸው፣ የሚወዷቸውና የሚጠሏቸው እንዲሁም የሚያስጨንቋቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? እነርሱም ጭፍን ጥላቻ አድሮባቸው ይሆን? የመንግሥቱን መልእክት እነርሱ ከሚያሳስባቸው ሁኔታ ጋር እንደሚስማማ አድርገህ ለማቅረብ ጣር። (1 ቆሮ. 9:19-23) ልክ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ እኛም ከውጭ አገር የመጡትን፣ የተለየ ባህል ያላቸውን፣ ሌላ ቋንቋ የሚናገሩትን ወይም በጣም ሃብታሞች የሆኑትን ጨምሮ በክልላችን ውስጥ ለሚገኙት ሁሉ ምሥራቹን የመስበክ ግዴታ እንዳለብን ሊሰማን ይገባል።—ሮሜ 1:14
3 ሆኖም የማታውቁትን ቋንቋ ለሚናገር ሰው እንዴት መመሥከር ትችላላችሁ? ለሰዎች ሁሉ የሚሆን ምሥራች (እንግሊዝኛ) የተባለውን ቡክሌት በሚገባ መጠቀም ይቻላል። በክልላችሁ ውስጥ በብዛት በሚነገረው ቋንቋ የሚገኙ አንዳንድ ትራክቶችን ወይም ብሮሹሮችን መያዝ ትችላላችሁ። (ሐምሌ 2003 የመንግሥት አገልግሎታችን ገጽ 6 አን. 2-3ን ተመልከት።) ከዚህም በተጨማሪ አንዳንድ አስፋፊዎች ሰላምታና ቀለል ያሉ አቀራረቦችን በሌሎች ቋንቋዎች ለመማር ጥረት አድርገዋል። አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች፣ ሌሎች ቋንቋቸውን ለመናገር በተወሰነ መልኩም ቢሆን የሚያደርጉትን ጥረት ሲመለከቱ ይደነቃሉ፤ ይህ ደግሞ ምሥራቹን እንዲሰሙ ሊያደርጋቸው ይችላል።
4 ይሖዋን ምሰሉ:- የተለያየ ባሕልና አስተዳደግ ላላቸው ሰዎች በመስበክ “ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነትን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ” የሚፈልገውን የማያዳላውን አምላካችንን ይሖዋን እንምሰለው።—1 ጢሞ. 2:3, 4