በአገልግሎታችሁ ክርስቶስን ምሰሉ
1 ኢየሱስ በአገልግሎታችን ልንከተለው የሚገባንን ምሳሌ ትቶልናል። ለአምላክና ለሰዎች ጥልቅ ፍቅር እንዳለው በተለያዩ አጋጣሚዎችና መንገዶች አሳይቷል። ትሑት ለሆኑ ሰዎች እውነትን ያስተማረ ከመሆኑም በላይ በችግር ለተጎዱና ለተደቆሱ ሰዎች ፍቅራዊ ደግነት የተንጸባረቀባቸውን ሥራዎች አከናውኗል።—ማቴ. 9:35
2 የኢየሱስ ምሳሌነትና ትምህርቶች:- ኢየሱስ በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ በመግባት ወይም የኅብረተሰቡን ኑሮ በሚያሻሽሉ የበጎ አድራጎት ተግባራት በመካፈል ትኩረቱ እንዲከፋፈል አላደረገም። እንዲሁም በበጎ ዓላማ የሚከናወን የትኛውም ተግባር ዋነኛ ሥራውን ከመሥራት እንዲያዘናጋው አልፈቀደም። (ሉቃስ 8:1) ለሰው ዘር ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ የሚያመጣውን የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመስበኩ ሥራ ላይ አተኩሯል። ኢየሱስ በጣም አስፈላጊ ሥራ የነበረው ሲሆን ይህንን ለማከናወን የነበረው ጊዜም ውስን ነበር። በቅፍርናሆም የሚገኙ ሰዎች እዚያ እንዲቆይ በፈለጉ ጊዜ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “ከዚህ ተነሥተን . . . እንሂድ፤ እዚያም ልስበክ፤ የመጣሁት ለዚሁ ነውና” ብሏቸዋል።—ማር. 1:38
3 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ካሠለጠናቸው በኋላ “‘መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች’ ብላችሁ ስበኩ” የሚል ግልጽ መመሪያ በመስጠት ልኳቸዋል። (ማቴ. 10:7) ለተከታዮቹ የመንግሥቱ ጉዳዮች በሕይወታቸው ውስጥ ትልቁን ቦታ ሊይዙ እንደሚገባ አስተምሯቸዋል። (ማቴ. 6:33) ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ለደቀ መዛሙርቱ የተናገራቸው የመሰነባበቻ ቃላት ምን መሥራት እንዳለባቸው በግልጽ አስገንዝበዋቸዋል። “ስለዚህ ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” ብሏቸዋል።—ማቴ. 28:19
4 የመንግሥቱ አስፈላጊነት:- ኢየሱስ ይሰብከው የነበረው ዋነኛው ርዕሰ ጉዳይ የአምላክ መንግሥት የነበረ ሲሆን ደቀ መዛሙርቱም በዚህ ረገድ የእርሱን ምሳሌ እንዲከተሉ አበረታቷቸዋል። ሰዎች ችግሮቻቸውን በራሳቸው ለመፍታት የሚያደርጉት ጥረት አይሳካም። (ኤር. 10:23) የአምላክን ስም የሚያስቀድሰውም ሆነ ለሰው ዘር ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ የሚያመጣው የአምላክ መንግሥት ብቻ ነው። (ማቴ. 6:9, 10) በዛሬው ጊዜ ‘በሚሠራው ጸያፍ ተግባር ለሚያዝኑና ለሚያለቅሱ’ ሰዎች የመንግሥቱን እውነቶች ማስተማር በአሁኑ ጊዜ ደስተኛና ስኬታማ ሕይወት እንዲኖሩ፣ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ደግሞ አስተማማኝ ተስፋ እንዲኖራቸው ይረዳቸዋል።—ሕዝ. 9:4
5 ኢየሱስ አሁንም የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመስበኩ ሥራ ላይ ትልቅ ሚና የሚጫወት ሲሆን እኛንም እንደሚደግፈን ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (ማቴ. 28:20) አገልግሎታችን ኢየሱስ ከተወልን ምሳሌ ጋር ምን ያህል ይስማማል? (1 ጴጥ. 2:21) በጣም ወሳኝ በሆኑት በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ውስጥ ኢየሱስ በአገልግሎቱ የተወውን ምሳሌ በጥብቅ ለመከተል አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እናድርግ!