ተቀዳሚ ሥራችን የሆነው ክርስቲያናዊ አገልግሎት
1 ሁላችንም ልናከናውናቸው የሚገቡን የተለያዩ ሥራዎች አሉ። አምላክ የቤተሰባችንን መሠረታዊ ፍላጎቶች እንድናሟላ ይጠብቅብናል። (1 ጢሞ. 5:8) ይሁን እንጂ ይህ ኃላፊነታችን የመንግሥቱን ምሥራች የመስበክና ደቀ መዝሙር የማድረግ ሥራችንን ችላ እንድንል ሊያደርገን አይገባም።—ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20
2 ኢየሱስ ‘የአምላክን መንግሥት ማስቀደምን’ በተመለከተ ልንከተለው የሚገባ ምሳሌ ትቶልናል። (ማቴ. 6:33፤ 1 ጴጥ. 2:21) በቁሳዊ ነገር ረገድ ብዙም ያልነበረው ቢሆንም የአባቱን ፈቃድ በመፈጸሙ ሥራ ሙሉ በሙሉ ተጠምዶ ነበር። (ሉቃስ 4:43፤ 9:58፤ ዮሐ. 4:34) ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለመመስከር ጥረት ያደርግ ነበር። (ሉቃስ 23:43፤ 1 ጢሞ. 6:13) ደቀ መዛሙርቱም የመከሩን ሥራ በተመለከተ ተመሳሳይ ዝንባሌ እንዲያድርባቸው አሳስቧቸዋል።—ማቴ. 9:37, 38
3 የኢየሱስን ምሳሌ መኮረጅ:- ኑሯችንን ቀላል በማድረግና በክርስቲያናዊ አገልግሎታችን ላይ በማተኮር የኢየሱስን ምሳሌ መኮረጅ እንችላለን። ለሕይወት የሚያስፈልጉት መሠረታዊ ነገሮች ካሉን ዓለም የሚያቀርባቸውን ነገሮች በመሰብሰብ እንዳንጠመድ የሚያሳስበውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተግባራዊ እናድርግ። (ማቴ. 6:19, 20፤ 1 ጢሞ. 6:8) በስብከቱ ሥራ የምናደርገውን ተሳትፎ ከፍ ለማድረግ መጣራችን ምንኛ የተሻለ ነው! በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙን ልዩ ልዩ የኑሮ ጭንቀቶች ዋነኛ ሥራችን የሆነውን የመንግሥቱን ምሥራች የማወጁን ተልእኮ ቸል እንድንል እንዲያደርጉን ባለመፍቀድ የኢየሱስን ምሳሌ እንከተል።—ሉቃስ 8:14፤ 9:59-62
4 ብዙ ኃላፊነቶች ያሉባቸው ወንድሞችና እህቶች እንኳ ለስብከቱ ሥራ ቅድሚያ ይሰጣሉ። ትልቅ ቤተሰብ የሚያስተዳድር፣ በመሥሪያ ቤቱ በኃላፊነት ቦታ ላይ የሚሠራና የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ የሚያገለግል አንድ ወንድም “አገልግሎቱን እንደ ተቀዳሚ ሥራዬ አድርጌ እመለከተዋለሁ” ሲል ተናግሯል። አንዲት አቅኚ እህት ደግሞ “አቅኚነት ከማንኛውም ጥሩ የሚባል ሰብዓዊ ሥራ የተሻለ ነው” ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች።
5 ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ እንከተል። እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ክርስቲያናዊውን አገልግሎት ተቀዳሚ ሥራችን በማድረግ ነው።