መብቶቻችንን ከፍ አድርገን እንመለከታለን!
1 የሰው ዘር ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ ይሖዋ ለአገልጋዮቹ የተለያዩ መብቶችን ሲሰጥ ቆይቷል። ይሖዋ ለአገልጋዮቹ እነዚህን መብቶች የሚሰጠው ጾታን፣ ዕድሜን ወይም የኑሮ ደረጃን መሠረት አድርጎ አይደለም። (ሉቃስ 1:41, 42፤ ሥራ 7:46፤ ፊልጵ. 1:29) በዛሬው ጊዜ ለምንኖር ክርስቲያኖችስ ምን ዓይነት መብቶችን ሰጥቶናል?
2 አንዳንዶቹ መብቶቻችን የትኞቹ ናቸው? ከይሖዋ የመማር መብት አግኝተናል። (ማቴ. 13:11, 15) በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ሐሳብ በመስጠት ይሖዋን ማወደስ ሌላው ከፍ አድርገን የምንመለከተው መብት ነው። (መዝ. 35:18) ሐሳብ ለመስጠት የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ስናገኝ ሐሳባችንን በጋለ ስሜት መግለጽ አለብን። በተመሳሳይም በጉባኤ ውስጥ የሚሰጠንን እያንዳንዱን ሥራ በአክብሮት የምንመለከት ከሆነ የተጣለብንን ኃላፊነት ለመወጣት የቻልነውን ሁሉ እናደርጋለን። የመንግሥት አዳራሹን በማጽዳቱና በማደሱ ሥራ ላይ አዘውትረን እንካፈላለን?
3 በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አምላክ የሚያቀርቡትን ጸሎት የመስማቱን ጉዳይ የሚጠራጠሩ ቢሆኑም፣ እኛ ግን በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ከሁሉ በላይ በሆነው አካል ተሰሚነት የማግኘት ልዩ መብት እንዳለን እናውቃለን። (ምሳሌ 15:29) ይሖዋ አገልጋዮቹ የሚያቀርቡትን ጸሎት እሱ ራሱ ይሰማል። (1 ጴጥ. 3:12) ምን ያህል ጊዜ ወደ እሱ በጸሎት መቅረብ እንዳለብን የሚገልጽ ገደብ አላስቀመጠም። “በማንኛውም ሁኔታ” መጸለይ መቻላችን እንዴት ያለ ትልቅ ስጦታ ነው!—ኤፌ. 6:18
4 ‘ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ ነን’:- ግሩም ከሆኑት መብቶቻችን መካከል አንዱ ‘ከአምላክ ጋር አብረን በመሥራት’ የእሱን መንግሥት ምሥራች ማወጅ መቻላችን ነው። (1 ቆሮ. 3:9) ይህ ሥራ እርካታና ደስታ ያስገኛል። (ዮሐ. 4:34) ይሖዋ ይህን ሥራ ለማከናወን የሰዎች እርዳታ አያስፈልገውም፤ ይሁንና ለእኛ ያለውን ፍቅር ለመግለጽ ሲል ይህን ኃላፊነት ሰጥቶናል። (ሉቃስ 19:39, 40) ሆኖም ይሖዋ ይህንን መብት የሰጠው ለማንም ሰው አይደለም። ከዚህ ይልቅ በአገልግሎት የሚካፈሉ ሰዎች አንዳንድ መንፈሳዊ ብቃቶችን ማሟላትና ይህንንም ይዘው መቀጠል ይኖርባቸዋል። (ኢሳ. 52:11) አገልግሎትን በሳምንት ውስጥ ከምናከናውናቸው አስፈላጊ እንቅስቃሴዎች መካከል አንዱ እንዲሆን በማድረግ ለዚህ መብት ትልቅ ቦታ እንደምንሰጥ እናሳያለን?
5 ከይሖዋ የምናገኛቸው መብቶች እርካታ ያለው ሕይወት ለመምራት ያስችሉናል። (ምሳሌ 10:22) በመሆኑም መብቶቻችንን ፈጽሞ አቅልለን አንመልከት! የተሰጡንን የአገልግሎት መብቶች ከፍ አድርገን እንደምንመለከታቸው በማሳየት ‘የበጎ ስጦታና የፍጹም በረከት ሁሉ’ ሰጪ የሆነውን በሰማይ የሚኖረውን አባታችንን እናስደስታለን።—ያዕ. 1:17