አገልግሎታችንን ለማስፋት ጥረት እናድርግ
1 ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ክርስቲያኖች በአምላክ መንገድ እንዲመላለሱና ‘ይበልጥ በዚሁ እንዲገፉበት’ ምክር ሰጥቷቸዋል። (1 ተሰ. 4:1) ይህ ለእኛ ምን ትርጉም አለው? ሁልጊዜ ‘አገልግሎታችንን ሙሉ በሙሉ ለመፈጸም’ ተጨማሪ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ እንድናደርግ የሚያስችሉንን መንገዶች መፈለግ ይኖርብናል ማለት ነው።—2 ጢሞ. 4:5 NW
2 ውስጣዊ ግፊት:- አገልግሎታችንን ይበልጥ የማስፋት ግፊት ፈጣሪያችንን በተሟላ መንገድ ለማገልገል ካለን ፍላጎት የሚመነጭ ነው። መንፈሳዊ እድገት ማድረግ ስለምንሻ አገልግሎታችንን የምናሻሽልበትን መንገድ እንፈልጋለን። በበጎ ዓላማ ተነሳስተን ጥሩ ልማድ ማዳበራችን ቲኦክራሲያዊ ግቦቻችን ላይ እንድንደርስ ይረዳናል።—መዝ. 1:1, 2፤ ፊልጵ. 4:6፤ ዕብ. 10:24, 25
3 አገልግሎታችንን ማስፋት የሰጪነትንና የራስን ጥቅም የመሠዋትን መንፈስ ማዳበርን ይጠይቃል። ይህ ዓይነቱን መንፈስ፣ ኢየሱስ በተወው ግሩም ምሳሌ ላይ ጸሎት የታከለበት ማሰላሰል በማድረግ ማዳበር ይቻላል። (ማቴ. 20:28) ኢየሱስ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት ሌሎችን የሚጠቅም ሥራ መሥራቱ ከፍተኛ ደስታ አስገኝቶለታል። (ሥራ 20:35) ለሰዎች በግለሰብ ደረጃ አሳቢዎች በመሆን እንዲሁም አገልግሎታችንን ለማስፋት የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ምንጊዜም በመጠቀም ኢየሱስን መኮረጅ እንችላለን።—ኢሳ. 6:8
4 የወላጆች ድርሻ:- ልጆችን ገና ከሕፃንነታቸው ጀምሮ በማሠልጠን ሌሎችን የማገልገል ብሎም አገልግሎታቸውን የማስፋት ፍላጎት በውስጣቸው እንዲቀረጽ ማድረግ ይቻላል። ልጆች፣ የቤተሰቡ አባላት የሚያሳዩትን ትጋትና አገልግሎታቸውን ለማስፋት የሚያደርጉትን ብርቱ ጥረት ያስተውላሉ። አንድ ወንድም ከአያቱ ጋር በጉባኤ እንቅስቃሴዎች ላይ አብሮ ይካፈል ስለነበር ገና በልጅነቱ አገልግሎቱን ለማስፋት ተገፋፍቷል። የአያቱን ትጋትና ደስታ መመልከቱ ወንድሞቹን ለማገልገል የሚያስችሉትን አጋጣሚዎች እንዲፈልግ አነሳስቶታል። ይህ ወንድም በአሁኑ ወቅት የጉባኤ አገልጋይ ነው።
5 ወንድሞች ያስፈልጋሉ:- “ማንም ኤጲስቆጶስነትን ቢፈልግ፣ መልካም ሥራን ይመኛል።” (1 ጢሞ. 3:1) እነዚህ ቃላት ወንድሞች በይሖዋ ድርጅት ውስጥ የሚገኙ ተጨማሪ የአገልግሎት መብቶች ላይ ለመድረስ የሚያስችሏቸውን ብቃቶች ለማሟላት እንዲጣጣሩ ያበረታቷቸዋል። እነዚህ መብቶች ላይ መድረስ የተለየ ችሎታ አይጠይቅም። አገልግሎቱን ለማስፋት የሚፈልግ አንድ ወንድም መንግሥቱን ያስቀድማል እንዲሁም በአገልግሎት በቅንዓት ይካፈላል። (ማቴ. 6:33፤ 2 ጢሞ. 4:5) ለሌሎች ጥሩ ምሳሌ ለመሆንም ጥረት ያደርጋል።
6 በዓለም አቀፍ ደረጃ:- ይሖዋ የመከሩን ሥራ እያፋጠነው ነው። (ኢሳ. 60:22) የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የሚፈልጉ ሰዎች አገልግሎታቸውን በተሟላ መንገድ ለመፈጸም ጥረት ማድረጋቸው በጣም አጣዳፊ ነው። የ2006 የአገልግሎት ዓመት ዓለም አቀፍ ሪፖርት እንደሚያሳየው በዚያ ዓመት 248,327 ሰዎች ተጠምቀዋል። ይህ ደግሞ በየቀኑ በአማካይ ከ680 በላይ የሚሆኑ አዳዲስ ሰዎች ተጠምቀዋል ማለት ነው! እንግዲያው ሁላችንም አገልግሎታችንን በተሟላ መንገድ ለማከናወን የሚያስችሉንን አጋጣሚዎች መፈለጋችንን እንቀጥል።