የንቁ! መጽሔት ልዩ እትም በኅዳር ወር ውስጥ ይበረከታል!
1 ብዙ ሰዎች በቅን ልቦና ተነሳስተው የመጽሐፍ ቅዱስን ዋጋማነት በተመለከተ ጥያቄዎችን ያነሳሉ። ‘መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉት ሰዎች ከሆኑ እንዴት የአምላክ ቃል ነው ሊባል ይችላል? አካሄዴን ያቀናልኛል ብዬ እንድተማመንበት የሚያደርጉ ምን ምክንያቶች አሉ? መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብና ለማጥናት መጣጣሬም ሆነ ጊዜ ማጥፋቴ የሚያስገኝልኝ ጥቅም ምንድን ነው? መጠቀም ያለብኝ የትኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ነው?’ እነዚህ ጥያቄዎች “በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነት መጣል ትችላለህ?” የሚል ርዕስ ባለው የኅዳር ወር ንቁ! መጽሔት ልዩ እትም ውስጥ መልስ ከተሰጠባቸው መካከል አንዳንዶቹ ናቸው።
2 ይህን የንቁ! መጽሔት ልዩ እትም በክልላችን ውስጥ በስፋት ማሰራጨት እንፈልጋለን። ከቻልክ በኅዳር ወር ውስጥ ባሉት ቅዳሜዎች ጉባኤው ከቤት ወደ ቤት በሚያደርገው አገልግሎት ላይ ተካፈል። ይህን ንቁ! መጽሔት ለዘመዶችህ፣ ለጎረቤቶችህ፣ ለሥራ ባልደረቦችህ፣ ለአስተማሪዎችህ፣ ለክፍል ጓደኞችህና ተመላልሶ መጠየቅ ለምታደርግላቸው ሰዎች አበርክት። ወደ ገበያ ስትወጣም ሆነ ስትጓዝ የተወሰኑ ቅጂዎችን ያዝ። ሽማግሌዎች ጉባኤው በቂ አቅርቦት እንዲኖረው ተጨማሪ ቅጂዎችን አዘዋል።
3 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አስጀምር፦ መጽሔቱን በምታበረክትበት ወቅት ውይይቱን ከመደምደምህ በፊት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር የሚያስችል መሠረት መጣል ትችላለህ። ለምሳሌ እንዲህ ማለት ትችላለህ:- “በሚቀጥለው ጊዜ ‘አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ምንድን ነው?’ ለሚለው ጥያቄ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን መልስ ባሳይዎት ደስ ይለኛል።” ተመልሰህ ስትሄድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ ይዘህ ሂድና በገጽ 4 እና 5 ላይ ያሉትን ሐሳቦች አሳየው ወይም በምዕራፍ 3 አንቀጽ ከ1-3 ላይ ያሉትን ሐሳቦች አወያየው። አሊያም ደግሞ “በሚቀጥለው ጊዜ በዘመናችን በመፈጸም ላይ ስላለ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ባወያይዎት ደስ ይለኛል” ማለት ትችላለህ። ተመልሰህ በምትሄድበት ወቅት ምዕራፍ 9ን አውጣና ከ1-3 ባሉት አንቀጾች ላይ ተወያዩባቸው። ወይም እንዲህ ማለት ትችላለህ:- “ብዙዎች መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚያነቧቸውን ነገሮች መረዳት ያስቸግራቸዋል። በሚቀጥለው ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስዎን እንዴት በተሻለ መንገድ መረዳት እንደሚችሉ ባሳይዎት ደስ ይለኛል።” ተመላልሶ መጠየቅ በምታደርግበት ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ አስተዋውቀውና ጥናቱ እንዴት እንደሚካሄድ አሳየው።
4 “መዳን የሚገኝበትን ጥበብ” ሊሰጡን የሚችሉት “ቅዱሳት መጻሕፍት” የሚገኙት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብቻ ነው። (2 ጢሞ. 3:15) በመሆኑም ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያላቸውን እምነት እንዲያሳድጉ ለመርዳት ይህን የንቁ! መጽሔት ልዩ እትም በማሰራጨቱ ሥራ በቅንዓት እንሳተፍ!