እርስ በርስ ለመበረታታት የሚያስችል ዝግጅት
1. ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች የሚያደርጉት ጉብኝት ምን ልዩ አጋጣሚ ይከፍታል?
1 ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ለሚገኘው ጉባኤ የሚከተለውን ጽፎ ነበር:- “እንድትጸኑ የሚያስችላችሁን መንፈሳዊ ስጦታ አካፍላችሁ ዘንድ፣ ላያችሁ እናፍቃለሁ። ይኸውም እናንተና እኔ በእያንዳንዳችን እምነት እርስ በርሳችን እንድንበረታታ ነው።” (ሮሜ 1:11, 12) በዘመናችንም ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች የሚያደርጉት ጉብኝት እርስ በርስ ለመበረታታት የሚያስችል አጋጣሚ ይከፍታል።
2. የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ጉብኝት ቀደም ብሎ በማስታወቂያ የሚነገረው ለምንድን ነው?
2 ጉባኤው:- አብዛኛውን ጊዜ የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ጉባኤውን መቼ እንደሚጎበኝ ከሦስት ወር ቀደም ብሎ በማስታወቂያ ይነገራል። ይህም ከጉብኝቱ ሙሉ ተጠቃሚ መሆን እንድንችል ፕሮግራማችንን አስቀድመን እንድናስተካክል ጊዜ ይሰጠናል። (ኤፌ. 5:15, 16) ሠራተኛ ከሆንክ በሳምንቱ ውስጥ በመስክ አገልግሎት ለመካፈል እረፍት መጠየቅ ትችል ይሆናል። አንዳንዶች በጉብኝቱ ወር ረዳት አቅኚ ሆነው ለማገልገል ዝግጅት ያደርጋሉ። ወደ ሌላ አካባቢ ለመሄድ አስበህ ከነበረ ጉብኝቱ እንዳያመልጥህ አንዳንድ ማስተካከያዎችን ማድረግ ትችል ይሆን?
3. በጉብኝቱ ሳምንት ማበረታቻ ለማግኘት በግለሰብ ደረጃ ምን ማድረግ እንችላለን?
3 የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ጉባኤዎችን የሚጎበኙበት ዋነኛ ዓላማ ወንድሞችን በግል ማበረታታት እንዲሁም በመስክ አገልግሎት ላይ ሥልጠና መስጠት ነው። ከእሱ ወይም ያገባ ከሆነ ከባለቤቱ ጋር ለማገልገል ለምን ጥያቄ አታቀርብም? የወረዳ የበላይ ተመልካቹ በአገልግሎት ብዙም ልምድ የሌላቸውን ወይም ችሎታቸውን ማሻሻል የሚፈልጉትን ጨምሮ ከተለያዩ አስፋፊዎች ጋር ማገልገል ያስደስተዋል። ሁላችንም በመስክ አገልግሎት ላይ ከሚጠቀምባቸው አቀራረቦች ትምህርት ልናገኝ ብሎም በደግነት የሚሰጠን ሐሳቦች ካሉ ተግባራዊ ልናደርጋቸው እንችላለን። (1 ቆሮ. 4:16, 17) ከዚህም በላይ የወረዳ የበላይ ተመልካቹን ምግብ መጋበዝህ ማበረታቻ ለማግኘት የሚያስችል ተጨማሪ አጋጣሚ ይፈጥርልሃል። (ዕብ. 13:2) ንግግሮቹ ከጉባኤው ሁኔታ ጋር በሚስማማ መንገድ ስለሚቀርቡ በጥሞና ለማዳመጥ ጥረት አድርግ።
4. የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ጉባኤያችንን ሲጎበኝ በምን መንገድ ማበረታታት እንችላለን?
4 የወረዳ የበላይ ተመልካቹ:- ሐዋርያው ጳውሎስ በየጉባኤው ከሚገኙ ወንድሞች የተለየ አልነበረም። እሱም ቢሆን ፈተናዎችና አስጨናቂ ሁኔታዎች ስለሚያጋጥሙት ማበረታቻ ያስፈልግው ነበር፤ ለዚህም አመስጋኝ ነበር። (2 ቆሮ. 11:26-28) በሮም የሚገኘው ጉባኤ አባላት፣ ታስሮ የነበረው ጳውሎስ ወደ እነሱ በመምጣት ላይ መሆኑን ሲሰሙ አንዳንዶቹ ሊቀበሉት 74 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ወደ አፍዩስ ፋሩስ ተጉዘዋል! “ጳውሎስም ባያቸው ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ተጽናናም።” (ሥራ 28:15) አንተም ጉባኤያችሁን የሚጎበኘውን የወረዳ የበላይ ተመልካች ማበረታታት ትችላለህ። ጉብኝቱን ሞቅ ባለ ስሜት በመደገፍ “ዕጥፍ ክብር” እንደሚገባው አሳይ። (1 ጢሞ. 5:17) ለሚያደርጋቸው ጥረቶች ልባዊ አድናቆት ይኑርህ፤ እንዲሁም ይህን አድናቆትህን በተግባር ለማሳየት ጥረት አድርግ። እሱም ሆነ ባለቤቱ እምነትህን፣ ፍቅርህንና ጽናትህን ሲያዩ ይደሰታሉ።—2 ተሰ. 1:3, 4
5. ዛሬ ሁላችንም ማበረታቻ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
5 በዚህ “የሚያስጨንቅ ጊዜ” ውስጥ ከመካከላችን ማበረታቻ የማያስፈልገው ማን አለ? (2 ጢሞ. 3:1) ከወረዳ የበላይ ተመልካቹ ጋር ልዩ እንቅስቃሴ በሚደረግበት በዚህ ሳምንት ሙሉ ተሳትፎ ለማድረግ አሁኑኑ ዝግጅት አድርግ። የወረዳ የበላይ ተመልካቾችም ሆንን የጉባኤ አስፋፊዎች አንዳችን ሌላውን ለማበረታታት የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናድርግ። በዚህ መንገድ ‘እርስ በርስ መጽናናትና መተናነጽ’ እንችላለን።—1 ተሰ. 5:11