የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመምራት ግብ አውጣ
1 “አዝመራው ለመከር እንደ ደረሰ ቀና ብላችሁ ማሳውን ተመልከቱ።” (ዮሐ. 4:35) ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገራቸው እነዚህ ቃላት በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያን አገልጋዮች ሰፊ ሥራ እንደሚጠብቃቸው የሚያሳዩ ናቸው።
2 የይሖዋን መንገዶች የመማር ፍላጎት ያላቸው ልበ ቅን የሆኑ ሰዎች አሁንም ድረስ እየተገኙ ነው። በየዓመቱ በርካታ ቁጥር ያላቸው አዳዲስ ደቀ መዛሙርት መጠመቃቸው ለዚህ ግሩም ማስረጃ ነው። አንተም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የመምራት ልባዊ ፍላጎት ካለህ ምን ማድረግ ትችላለህ?
3 ግብ አውጣ:- በመጀመሪያ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመርና በቋሚነት ለመምራት ግብ አውጣ። አገልግሎት ላይ ስትሰማራ ያወጣኸውን ይህን ግብ በአእምሮህ ያዝ። ክርስቲያናዊ ተልዕኳችን ከስብከቱ ሥራ ጎን ለጎን ማስተማርንም ስለሚጨምር ሁላችንም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲኖረን ተጨማሪ ጥረቶችን ማድረግ ይገባናል።—ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20
4 ልትዘነጋቸው የማይገቡ ሌሎች ነጥቦች:- የመንግሥቱ አስፋፊዎች ልባዊ ጸሎት ማቅረባቸው የግድ አስፈላጊ ነው። አንዳንድ ጊዜ መንፈሳዊ እርዳታ እንዲደረግላቸው ሲጸልዩ የነበሩ ሰዎች ያጋጥሙናል። ይሖዋ እንደነዚህ ያሉ ሰዎችን አግኝተን እንድናስተምራቸው በእኛ መጠቀሙ እንዴት ያለ በረከት ነው!—ሐጌ 2:7፤ ሥራ 10:1, 2
5 አንዲት እህት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲኖራት ከጸለየች በኋላ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ ማወቅ ትፈልጋለህ? የተባለውን ትራክት የተወሰኑ ቅጂዎች በምትሠራበት ቦታ አስቀመጠች። አንዲት ሴት አንዱን ትራክት አንስታ ሙሉ በሙሉ አንብባ ከጨረሰች በኋላ በትራክቱ ላይ የሚገኘውን ቅጽ መሙላት ጀመረች፤ በዚህ ጊዜ እህት ያነጋገረቻት ሲሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመርም ችላለች።
6 ከዚህም በላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በማስጀመርና በመምራት ረገድ ውጤታማ የሆኑ አስፋፊዎች ጥናት ለማግኘት ያወጣኸው ግብ ላይ እንድትደርስ ሊረዱህ ይችላሉ። ጥናት ለማግኘት ከመጸለይ ባሻገር እዚህ ግብህ ላይ ለመድረስ በሚያስችሉህ ዝግጅቶች ሁሉ ተጠቀም። እንዲህ ካደረግህ ብዙም ሳይቆይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በመምራት የሚገኘውን ደስታ መቅመስ ትችላለህ።