ልባቸው የተሰበረውን አጽናኑ
1 በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ የዛሬውን ያህል ማጽናኛ መስጠት አስፈላጊ የሆነበት ጊዜ የለም። እኛም የንጉሣችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አመራር በመከተል ‘ልባቸው የተሰበረውን ለመጠገን’ ጥረት እናደርጋለን።—ኢሳ. 61:1
2 አቀራረባችን:- ሰዎችን ለማጽናናት ከፈለግን በምናገለግልበት ጊዜ አቀራረባችን ሚዛናዊነት የሚንጸባረቅበትና የምናነጋግራቸውን ሰዎች የሚያበረታታ መሆን ይገባዋል። ከሰዎች ጋር ውይይት በምናደርግበት ወቅት በዓለም ውስጥ ስለሚፈጸሙ የክፋት ድርጊቶችም ሆነ የሐሰት ሃይማኖቶች ስለሚያስተምሯቸው መሠረተ ትምህርቶች ብዙ የማንናገር ከሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እንዲሁም አምላክ የሰጠን አጽናኝና አስደሳች ተስፋዎች ጎልተው ይወጣሉ። እንዲህ ሲባል ግን ፈጽሞ ስለ አርማጌዶን ማንሳት አያስፈልግም ማለት አይደለም። ተልዕኳችን ሁለቱንም ማለትም ‘የተወደደውን የአምላክን ዓመት’ እና ‘የአምላካችንን የበቀል ቀን’ በማወጅ ‘ኃጢአተኛው ከክፉ ሥራው እንዲመለስ’ ማስጠንቀቅ ነው። ሆኖም ስለ አርማጌዶንና ስለሚያስከትለው ጥፋት የምንናገረው ማስጠንቀቂያ የመንግሥቱን ወንጌል ወይም ምሥራች እስኪያደበዝዘው ድረስ መብዛት የለበትም።—ኢሳ. 61:2፤ ሕዝ. 3:18፤ ማቴ. 24:14
3 ከቤት ወደ ቤት:- በበሽታ፣ የሚወዱትን ሰው በሞት በማጣት፣ በፍትሕ መጓደል ወይም በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት የተጎዱ ሰዎችን ማግኘት እንግዳ ነገር አይደለም። የክርስቶስን ፈለግ የምንከተል እንደመሆናችን መጠን በአገልግሎት ላይ ለምናገኛቸው እንዲህ ዓይነት ሰዎች ‘ርኅራኄና’ አዘኔታ ልናሳያቸው ያስፈልጋል። (ሉቃስ 7:13፤ ሮሜ 12:15) ግለሰቡ ከገጠመው ችግር ጋር ተዛማጅነት ያላቸው አንድ ወይም ሁለት ጥቅሶችን ልናነብለት ብንችልም ስሜቱን እንዲገልጽ እድል በመስጠት ‘ለመስማት የፈጠንን’ መሆናችንን ማሳየት ይኖርብናል። (ያዕ. 1:19) በቅድሚያ የምናዳምጥ ከሆነ እንዴት ማጽናኛ መስጠት እንደምንችል ማወቅ አይቸግረንም።
4 በውይይታችን መሃል ተገቢ መስሎ በታየን ጊዜ ላይ እንዲህ ማለት እንችላለን:- “ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አንዳንድ የሚያጽናኑ ሐሳቦችን ባካፍልዎት ደስ ይለኛል።” ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ በመጠቀም ግለሰቡ ያለውን እያንዳንዱን የተሳሳተ አመለካከት ከማረም መቆጠብ ይኖርብናል። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅመን ልባቸውን ለማጠንከር የሚያስችል ማበረታቻና ማጽናኛ በመስጠት ላይ ልናተኩር ይገባናል። በዚህ ረገድ ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር በተባለው መጽሐፍ ላይ “ማበረታቻ” በሚል ርዕስ ሥር ገጽ117-121 ላይ ያሉትን ሐሳቦች መጠቀም ትችላለህ። ወይም ደግሞ ለተጨነቁ ሰዎች የሚሆን መጽናኛ የሚለውን ትራክት ልትሰጠውና ጽሑፉ በያዛቸው የሚያበረታቱ ሐሳቦች ላይ ልትወያዩ ትችላላችሁ።
5 ሌሎችን ለማጽናናት የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ፈልግ:- ከጎረቤቶችህ፣ ከሥራ ባልደረቦችህ፣ አብረውህ ከሚማሩ ተማሪዎች፣ ወይም ከቤተሰብህ አባላት መካከል ማጽናኛ የሚያስፈልገው ሰው አለ? ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚገኘውን ማጽናኛ የማካፈል ግብ በመያዝ ቤታቸው ሄደህ ለመጠየቅ ለምን ጥረት አታደርግም? በመጀመሪያ በምን ረገድ ማጽናኛ እንደሚያስፈልጋቸው ካወቅህ በዚያ ጉዳይ ላይ ልትዘጋጅ ትችላለህ። አንዳንዶች ደብዳቤ በመጻፍና ስልክ በመደወል ይህን አድርገዋል። ለሰዎች ያለን እውነተኛ ፍቅር እንድናዝንላቸውና ከቅዱሳን መጻሕፍት ላይ አስፈላጊውን ማጽናኛ እንድንሰጣቸው ያነሳሳናል።—ሉቃስ 10:25-37
6 አዎን፣ ያዘኑትንና የተከዙትን ሰዎች የማጽናናት እንዲሁም ስለወደፊቱ ጊዜ ብሩሕ ተስፋ እንዲኖራቸው የማድረግ ተልዕኮ ተሰጥቶናል። በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች የሚያስፈልጋቸው እንዲህ ዓይነቱ ማጽናኛ ነው። አምላክ፣ ቃል ስለገባቸው ብዙ መልካም ነገሮች አንስቶ በደስታ ስሜት መናገር ልበ ቅን ለሆኑ ሰዎች ማጽናኛና ተስፋ ያስገኝላቸዋል። እንግዲያው ልባቸው የተሰበረውን የመጠገንን አስፈላጊነት ምንጊዜም አንዘንጋ።