በአገልግሎት ላይ የምታሳልፉትን ጊዜ በሚገባ ተጠቀሙበት
1 በአገልግሎታችን ልናከናውናቸው የሚገቡን ብዙ ነገሮች እንዳሉ እሙን ነው፤ ሆኖም የቀረን ጊዜ አጭር ነው። (ዮሐ. 4:35፤ 1 ቆሮ. 7:29) በጥሩ ሁኔታ ከተደራጀንና አስቀድመን እቅድ ካወጣን ለአገልግሎት የመደብነውን አብዛኛውን ጊዜ በሚገባ ልንጠቀምበት እንችላለን።
2 አስቀድመህ ተዘጋጅ:- ወደ መስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ ከመሄድህ በፊት የሚያስፈልጉህን ጽሑፎች መያዝህን እርግጠኛ ሁን፤ መግቢያህንም በሚገባ ተለማመድ። ስብሰባው በጸሎት እንደተዘጋ በቀጥታ ወደ አገልግሎት ክልልህ ሂድ። እንዲህ ማድረግህ አንተም ሆንክ አብሮህ የተመደበው አስፋፊ በተቻለ መጠን ረዘም ያለ ሰዓት እንድታገለግሉ ያስችላችኋል።
3 የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባውን እንድትመራ የተመደብከው አንተ ከሆንክ በሰዓቱ ጀምር። ስብሰባው አጭር ማለትም ከ10 እስከ 15 ደቂቃ የማይበልጥ እንዲሆን አድርግ። ቡድኑ ወደ አገልግሎት እንዲሰማራ ከማሰናበትህ በፊት እያንዳንዱ አስፋፊ የት እና ከማን ጋር እንደሚያገለግል ያውቅ እንደሆነ እርግጠኛ ሁን።
4 በአገልግሎት ላይ ስትሆን:- የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባው ከተጠናቀቀ በኋላ ሳያስፈልግ ጊዜ አታባክን፤ ከዚያ ይልቅ በቀጥታ ወደ ክልልህ ሂድ። ቀደም ብለህ አገልግሎት ለማቆም ካሰብክ እንደ አንተው ለአጭር ሰዓት ከሚያገለግል አስፋፊ ጋር እንዲመድብህ ስምሪቱን ለሚመራው ወንድም ንገረው። በቡድን በምታገለግሉበት ወቅት ሌሎቹ የጀመርከውን ውይይት እስክትጨርስ ድረስ ብዙ እንዳይጠብቁህ አሳቢነት አሳይ። ይህም ተከራካሪ የሆነ ሰው ሲያጋጥም ውይይቱን በዘዴ ማቆም አሊያም ፍላጎት ካለው ደግሞ ሌላ ጊዜ ለመገናኘት ቀጠሮ መያዝ ሊጠይቅ ይችላል።—ማቴ. 10:11
5 ተመላልሶ መጠየቅ በምታደርግበት ወቅት ወደ ሌላ አካባቢ ከመሄድህ በፊት እዚያው ሰፈር ላነጋገርካቸው ሰዎች ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግ ከአላስፈላጊ ጉዞ መዳን ትችላለህ። ተመላልሶ ልናደርግላቸው ካሰብናቸው ሰዎች መካከል አንዳንዶቹን ቤታቸው ይገኙ እንደሆነና እንዳልሆነ ለማጣራት አስቀድመን ስልክ መደወላችን ጥሩ ሊሆን ይችላል። (ምሳሌ 21:5) ተመላልሶ መጠየቁ ረጅም ሰዓት እንደሚወስድ ከተሰማህ ሌሎች አንተን በመጠበቅ ጊዜ እንዳያባክኑ በዚያው አካባቢ እያገለገሉ እንዲቆዩ አሊያም ሌላ ተመላልሶ መጠየቅ እንዲያደርጉ ዝግጅት ማድረግ ትችላለህ።
6 ታላቅ የሆነ መንፈሳዊ የመከር ሥራ በሚከናወንበት ወቅት ላይ እንገኛለን። (ማቴ. 9:37, 38) በቅርቡ ሥራው ይደመደማል። እንግዲያው በአገልግሎት ላይ የምናሳልፈውን ጊዜ በሚገባ የመጠቀም ፍላጎት ሊያድርብን ይገባል።