ውጤታማ የሆነ የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ
1. የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ ዓላማ ምንድን ነው?
1 በአንድ ወቅት ኢየሱስ 70 ደቀ መዛሙርቱን እንዲሰብኩ ከመላኩ በፊት ከእነሱ ጋር ስብሰባ አድርጎ ነበር። (ሉቃስ 10:1-11) በሚሰብኩበት ጊዜ ብቻቸውን እንደማይሆኑና “የመከሩ ሥራ ኃላፊ” የሆነው ይሖዋ እንደሚመራቸው በመግለጽ ማበረታቻ ሰጣቸው። በተጨማሪም ለሥራው የሚያስታጥቃቸው መመሪያ የሰጣቸው ሲሆን የላካቸውም “ሁለት ሁለት አድርጎ” በማቀናጀት ነው። ዛሬም ወደ አገልግሎት ከመውጣታችን በፊት የምናደርጋቸው ስብሰባዎች ዓላማ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው፤ ስብሰባው የሚካሄደው እኛን ለማበረታታት፣ ለሥራው ለማስታጠቅና ለማቀናጀት ነው።
2. የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ ርዝመት ምን ያህል ሊሆን ይገባል?
2 በአሁኑ ወቅት የምናደርጋቸው የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎች ከ10 እስከ 15 ደቂቃ የሚወስዱ ሲሆን ስብሰባው አስፋፊዎቹን ማቀናጀትን፣ ክልል መስጠትንና ጸሎትን ያካትታል። ከአሁን በኋላ በዚህ አሠራር ላይ ማስተካከያ ይደረጋል። ከሚያዝያ ወር አንስቶ የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ የሚወስደው ከአምስት እስከ ሰባት ደቂቃ ይሆናል። የስምሪት ስብሰባው የሚካሄደው ከሌላ የጉባኤ ስብሰባ በኋላ ከሆነ ደግሞ አስፋፊዎች ግሩም የሆነ ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርት ሲያገኙ ስለቆዩ የስምሪት ስብሰባው ይበልጥ አጭር መሆን አለበት። የስምሪት ስብሰባው አጠር ማለቱ አስፋፊዎች በአገልግሎት ሰፋ ያለ ጊዜ ለማሳለፍ አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። በተጨማሪም አቅኚዎች ወይም አስፋፊዎች ከስምሪት ስብሰባው በፊት አገልግሎት ጀምረው ከሆነ ለስብሰባው ሲሉ አገልግሎታቸውን የሚያቋርጡት ለጥቂት ደቂቃዎች ብቻ ይሆናል።
3. የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ አስፋፊዎችን ይበልጥ የሚጠቅም እንዲሆን ምን ማድረግ ይቻላል?
3 የመስከ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ አስፋፊዎችን ይበልጥ በሚጠቅም መንገድ መዘጋጀት ይኖርበታል። በብዙ ጉባኤዎች የመስክ አገልግሎት ስምሪት ቡድኖች አንድ ላይ ከሚሰባሰቡ ይልቅ በተለያዩ ቦታዎች ስብሰባ ቢያደርጉ ይበልጥ ጠቃሚ ይሆናል። ይህም አስፋፊዎች የስምሪት ስብሰባ ወደሚደረግበት ቦታም ሆነ ወደ ክልላቸው መሄድ ቀላል እንዲሆንላቸው ያደርጋል። በተጨማሪም አስፋፊዎችን ለማቀናጀት ጊዜ የማይወስድ ከመሆኑም ሌላ የቡድን የበላይ ተመልካቾች በቡድናቸው ውስጥ ያሉትን አስፋፊዎች በቅርበት መከታተል ቀላል እንዲሆንላቸው ያደርጋል። የሽማግሌዎች አካል የአካባቢውን ሁኔታ ከግምት በማስገባት የተሻለውን ውሳኔ ማድረግ ይችላል። የስምሪት ስብሰባው አጠር ባለ ጸሎት ከመደምደሙ በፊት ሁሉም አስፋፊዎች የትና ከማን ጋር እንደሚያገለግሉ ማወቅ አለባቸው።
4. የስምሪት ስብሰባ የሌሎች የጉባኤ ስብሰባዎችን ያህል አስፈላጊ እንዳልሆነ ሊሰማን የማይገባው ለምንድን ነው?
4 የሌሎቹን የጉባኤ ስብሰባዎች ያህል አስፈላጊ ነው፦ የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎች የሚካሄዱት አገልግሎት የሚወጡ አስፋፊዎችን ለመጥቀም በመሆኑ በስብሰባው ላይ የሚገኙት ሁሉም የጉባኤው አባላት ላይሆኑ ይችላሉ። ይህ ሲባል ግን የስምሪት ስብሰባውን አቅልለን ልንመለከተው ወይም የሌሎች የጉባኤ ስብሰባዎችን ያህል አስፈላጊ እንዳልሆነ ሊሰማን ይገባል ማለት አይደለም። እንደ ሌሎቹ የጉባኤ ስብሰባዎቻችን ሁሉ የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባም ይሖዋ እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች እንድንነቃቃ ለመርዳት ያደረገው ዝግጅት ነው። (ዕብ. 10:24, 25) በመሆኑም ስምሪቱን የሚመራው ወንድም በስብሰባው ላይ የሚያቀርበው ነጥብ ይሖዋን የሚያስከብርና አስፋፊዎቹን የሚጠቅም እንዲሆን በሚገባ መዘጋጀት ይኖርበታል። አገልግሎት የሚወጡ አስፋፊዎች፣ ሁኔታው የሚፈቅድላቸው ከሆነ በስምሪት ስብሰባው ላይ ለመገኘት ጥረት ማድረግ አለባቸው።
የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎችን አቅልለን ልንመለከታቸው ወይም የሌሎች የጉባኤ ስብሰባዎችን ያህል አስፈላጊ እንዳልሆኑ ሊሰማን አይገባም
5. (ሀ) የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎችን በማደራጀት ረገድ ምን ሚና ይጫወታል? (ለ) አንዲት እህት የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባን መምራት ያለባት እንዴት ነው?
5 የሚመራው ወንድም የሚያደርገው ዝግጅት፦ በስብሰባ ላይ ክፍል የሚያቀርብ ሰው በሚገባ እንዲዘጋጅ ክፍሉ ቀደም ብሎ ሊሰጠው ይገባል። ከመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ ጋር በተያያዘም ይህ መሆኑ ተገቢ ነው። የመስክ አገልግሎት ስምሪት ቡድኖች የሚሰበሰቡት በተለያየ ቦታ ከሆነ የስምሪት ስብሰባውን የሚመሩት የቡድን የበላይ ተመልካቾች ወይም ረዳቶቻቸው እንደሚሆኑ የታወቀ ነው። ይሁንና ጉባኤው የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባውን በአንድ ቦታ በሚያደርግበት ጊዜ የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ ስብሰባውን የሚመራ ሰው ይመድባል። አንዳንድ የአገልግሎት የበላይ ተመልካቾች፣ የስምሪት ስብሰባ ለሚመሩት ወንድሞች በሙሉ ፕሮግራሙን የሚሰጧቸው ከመሆኑም ሌላ የማስታወቂያ ሰሌዳው ላይ ይለጥፉታል። የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ ስብሰባውን የሚመሩ ወንድሞችን በሚመድብበት ጊዜ አስተዋይ መሆን ይኖርበታል፤ ምክንያቱም ስምሪቱን የሚመሩት ወንድሞች የማስተማርና የማቀናጀት ችሎታ ያላቸው መሆኑ ለስብሰባው ውጤታማነት አስተዋጽኦ ያደርጋል። በአንዳንድ ቀናት ስብሰባውን ሊመራ የሚችል የጉባኤ ሽማግሌ፣ አገልጋይ ወይም ብቃት ያለው የተጠመቀ ወንድም ከሌለ የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ ብቃት ያላት አንዲት የተጠመቀች እህት ስብሰባውን እንድትመራ ሊመድብ ይገባል።—“አንዲት እህት መምራት ሲኖርባት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
6. የስምሪት ስብሰባ እንዲመሩ የሚመደቡ ሁሉ በደንብ መዘጋጀታቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
6 በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ወይም በአገልግሎት ስብሰባ ላይ ክፍል ሲሰጠን በቁም ነገር ተመልክተን በሚገባ እንዘጋጃለን። ማናችንም ብንሆን ‘ክፍሉን ወደ ስብሰባው ስሄድ መንገድ ላይ አስብበታለሁ’ በማለት ሳንዘጋጅ እንደማንቆይ የታወቀ ነው። በተመሳሳይም የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ እንዲመሩ የሚመደቡ ሁሉ ኃላፊነቱን በቁም ነገር ሊመለከቱት ይገባል። የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ የሚወስደው ጊዜ እንዲያጥር ስለተደረገ ስብሰባው ትርጉም ያለው እንዲሆንና በሰዓቱ እንዲያበቃ ጥሩ ዝግጅት ማድረግ ይበልጥ አስፈላጊ ይሆናል። ጥሩ ዝግጅት ማድረግ ሲባል አስቀድሞ ክልል ማዘጋጀትንም ይጨምራል።
7. የስምሪት ስብሰባውን የሚመራው ወንድም የትኞቹን ነጥቦች ሊያቀርብ ይችላል?
7 የትኞቹን ነጥቦች ማቅረብ ይቻላል? በየአካባቢው ያሉት ሁኔታዎች ስለሚለያዩ ታማኝና ልባም ባሪያ ለእያንዳንዱ የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ የሚያገለግል አስተዋጽኦ አላዘጋጀም። “በመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ ላይ ሊቀርቡ የሚችሉ ነጥቦች” በሚለው ሣጥን ውስጥ አንዳንድ ሐሳቦች ተጠቅሰዋል። በአብዛኛው ስብሰባው የሚካሄደው በውይይት ነው። አልፎ አልፎ፣ ጥሩ ዝግጅት የተደረገበት ሠርቶ ማሳያ ወይም ከjw.org ላይ የተወሰደ ተስማሚ ቪዲዮ ማቅረብ ይቻላል። የስምሪት ስብሰባውን የሚመራው ወንድም ለስብሰባው ሲዘጋጅ፣ በዚያ ዕለት አገልግሎት የሚወጡትን አስፋፊዎች ሊያበረታታቸውና ለአገልግሎት ሊያስታጥቃቸው የሚችለው ምን እንደሆነ በቁም ነገር ሊያስብበት ይገባል።
የስምሪት ስብሰባውን የሚመራው ወንድም ለስብሰባው ሲዘጋጅ፣ በዚያ ዕለት አገልግሎት የሚወጡትን አስፋፊዎች ሊያበረታታቸውና ለአገልግሎት ሊያስታጥቃቸው የሚችለው ምን እንደሆነ በቁም ነገር ሊያስብበት ይገባል
8. ቅዳሜ እና እሁድ በሚደረጉ የስምሪት ስብሰባዎች ላይ የትኞቹን ነገሮች መወያየቱ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል?
8 ለምሳሌ ያህል፣ ቅዳሜ ቀን አብዛኞቹ አስፋፊዎች የሚያበረክቱት መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! ነው። ቅዳሜ አገልግሎት የሚወጡ ብዙዎቹ አስፋፊዎች በሳምንቱ መሃል ስለማይወጡ በቤተሰብ አምልኮ ወቅት የተለማመዱትን መግቢያ ማስታወስ ሊከብዳቸው ይችላል። በመሆኑም የስምሪት ስብሰባውን የሚመራው ወንድም በመንግሥት አገልግሎታችን ጀርባ ላይ ከሚወጡት የአቀራረብ ናሙናዎች አንዱን መከለሱ ጠቃሚ ነው። ሌላው አማራጭ ደግሞ በዜና ላይ የቀረበን አንድ ጉዳይ፣ በአካባቢው የተፈጸመን ክስተት ወይም አንድን በዓል በመጥቀስ እንዴት መጽሔት ማበርከት እንደሚቻል አሊያም አስፋፊዎች መጽሔት ካበረከቱ በኋላ ለተመላልሶ መጠየቅ መሠረት መጣል የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ማወያየት ነው። በስምሪት ስብሰባው ላይ ከተገኙት መካከል አንዳንዶቹ በወሩ የሚበረከቱትን መጽሔቶች ማበርከት ጀምረው ከሆነ ጥሩ ሆነው ያገኟቸውን ሐሳቦች ወይም የሚያበረታቱ ተሞክሮዎችን በአጭሩ እንዲናገሩ ስምሪቱን የሚመራው ወንድም ሊጠይቃቸው ይችላል። እሁድ ቀን የሚመራው ወንድም ደግሞ በወሩ ከሚበረከተው ጽሑፍ ጋር በተያያዘ ከላይ የቀረቡትን ነጥቦች ተግባራዊ ሊያደርግ ይችላል። ምሥራች እና አምላክን ስማ የተባሉትን ብሮሹሮች እንዲሁም ትክክለኛው የተባለውን መጽሐፍ የመሳሰሉ ለጥናት የምንጠቀምባቸው ጽሑፎች በማንኛውም ቀን ሊበረከቱ ስለሚችሉ የስምሪት ስብሰባ የሚመራው ወንድም እነዚህ ጽሑፎች እንዴት እንደሚበረከቱ በአጭሩ ሊከልስ ይችላል።
9. በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ልዩ ዘመቻ በሚኖርበት ጊዜ የስምሪት ስብሰባውን የሚመራው ወንድም ምን ማቅረብ ይችላል?
9 ጉባኤው በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት በልዩ ዘመቻ የሚካፈል ከሆነ የስምሪት ስብሰባውን የሚመራው ወንድም በወሩ ውስጥ የሚበረከቱትን መጽሔቶች ከመጋበዣው ወይም ከትራክቱ ጋር እንዴት ማበርከት እንደሚቻል አሊያም ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ሲያጋጥሙ ምን ማድረግ እንደሚቻል ሊያብራራ ይችላል። ሌላው አማራጭ ደግሞ እንዲህ ያሉ ዘመቻዎች ያላቸውን ጠቀሜታ የሚያጎሉ ተሞክሮዎችን መናገር ነው።
10, 11. የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ ውጤታማ እንዲሆን አስፋፊዎች ዝግጅት ማድረጋቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
10 አስፋፊዎች የሚያደርጉት ዝግጅት፦ የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ ውጤታማ እንዲሆን አስፋፊዎችም የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ አለ። ለአገልግሎት አስቀድመው ከተዘጋጁ (ለምሳሌ በቤተሰብ አምልኳቸው ወቅት) ለሌሎች አስፋፊዎች የሚያካፍሉት ነገር ይኖራቸዋል። ጥሩ ዝግጅት ማድረግ በስምሪት ስብሰባው ላይ ከመገኘታችን በፊት መጽሔቶችንና ሌሎች ጽሑፎችን ከጉባኤ መውሰድንም ይጨምራል፤ ይህም ከስብሰባው በኋላ ሳይዘገዩ ወደ ክልላቸው ለመሄድ ያስችላቸዋል።
11 በተጨማሪም የስምሪት ስብሰባው ከመጀመሩ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ለመድረስ ጥረት ማድረግ አስፈላጊ ነው። እርግጥ ነው፣ በሁሉም የጉባኤ ስብሰባዎቻችን ላይ በሰዓቱ ለመድረስ ጥረት እናደርጋለን። ይሁንና በተለይ በስምሪት ስብሰባ ላይ ዘግይተን መድረሳችን አስቸጋሪ ሁኔታ ሊፈጥር ይችላል። እንዴት? ስብሰባውን የሚመራው ወንድም አስፋፊዎቹን ከማቀናጀቱ በፊት የተለያዩ ነገሮችን ከግምት ያስገባል። በስብሰባው ላይ የተገኙት ጥቂት አስፋፊዎች ከሆኑ ሁሉንም ሰው፣ በከፊል ወደተሸፈነ ክልል ለመላክ ሊወስን ይችላል። አንዳንዶች ወደ ስብሰባው የመጡት በእግራቸው ተጉዘው ከሆነና ክልሉ የሚገኘው ደግሞ ራቅ ባለ አካባቢ ከሆነ እነዚህን አስፋፊዎች መኪና ካላቸው ወንድሞች ጋር ይመድባቸው ይሆናል። ክልሉ የሚገኘው ወንጀል በሚበዛበት አካባቢ ከሆነ እህቶች ከወንድሞች ጋር እንዲሠሩት አሊያም ወንድሞች በአቅራቢያቸው ሆነው እንዲያገለግሉ ሊያደርግ ይችላል። አቅመ ደካማ የሆኑ አስፋፊዎች መንገዱ ወጣ ገባ ባልሆነበት ወይም ብዙ ደረጃ የሌላቸው ቤቶች በሚገኙበት አካባቢ እንዲያገለግሉ ሊመደቡ ይችላሉ። አዳዲስ አስፋፊዎች ደግሞ ተሞክሮ ካላቸው ጋር ይመደቡ ይሆናል። ይሁንና አስፋፊዎች ዘግይተው ከደረሱ ስምሪቱን የሚመራው ወንድም እነሱን ለማስተናገድ ሲል ቀደም ሲል ያቀናጃቸውን አስፋፊዎች መቀያየር ወይም እንደገና ማቀናጀት ይኖርበታል። እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ጊዜ አርፍደን እንድንደርስ የሚያደርግ ነገር ይገጥመን ይሆናል። የማርፈድ ልማድ ካለን ግን ይህ የሚሆነው ለመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባው አድናቆት ስለጎደለን አሊያም ፕሮግራማችንን አስቀድመን ሳናደራጅ በመቅረታችን እንዳይሆን ራሳችንን መመርመር ይኖርብናል።
12. አብዛኛውን ጊዜ አገልግሎት ስትወጡ እርስ በርሳችሁ የምትመዳደቡ ከሆነ የትኞቹን ነጥቦች ልታስቡባቸው ይገባል?
12 ወደ ስምሪት ስብሰባ የሚመጡ አስፋፊዎች ከማን ጋር እንደሚወጡ ከስብሰባው በፊት ራሳቸው ሊያመቻቹ አሊያም በስብሰባው ላይ ጓደኛ ሊመደብላቸው ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ እርስ በርስ ተመዳድባችሁ የምትመጡ ከሆነ ሁልጊዜ ከቅርብ ጓደኞቻችሁ ጋር ብቻ ከማገልገል ይልቅ ከተለያዩ አስፋፊዎች ጋር በማገልገል ‘ልባችሁን ወለል አድርጋችሁ ልትከፍቱ’ ትችላላችሁ? (2 ቆሮ. 6:11-13) ከአዳዲስ አስፋፊዎች ጋር አልፎ አልፎ በማገልገል የማስተማር ችሎታቸውን እንዲያሻሽሉ ልትረዷቸው ትችላላችሁ? (1 ቆሮ. 10:24፤ 1 ጢሞ. 4:13, 15) መስበክ መጀመር ያለባችሁ የት እንደሆነ የሚሰጣችሁን መመሪያ ጨምሮ የሚነገራችሁን ማንኛውንም ነገር በትኩረት አዳምጡ። የስምሪት ስብሰባው ሲያበቃ የሚመራው ወንድም ያቀናጀውን ከመለወጥ ይልቅ ወዲያውኑ ወደ ክልላችሁ ሂዱ።
13. ሁሉም ሰው ኃላፊነቱን በትጋት የሚወጣ ከሆነ የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎች ምን ጥቅም ያስገኙልናል?
13 ኢየሱስ አቀናጅቶ የላካቸው 70ዎቹ ደቀ መዛሙርት ከአገልግሎት የተመለሱት “ደስ እያላቸው” ነበር። (ሉቃስ 10:17) መስበክ ከመጀመራቸው በፊት ኢየሱስ ከእነሱ ጋር ያደረገው ስብሰባ ውጤታማ እንዲሆኑ እንደረዳቸው ጥርጥር የለውም። ዛሬም የምናደርጋቸው የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎች ተመሳሳይ ጥቅም አላቸው። ሁሉም ሰው ኃላፊነቱን በትጋት የሚወጣ ከሆነ የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎች ‘ለብሔራት ሁሉ ምሥክርነት’ የመስጠት ተልእኳችንን ለመፈጸም እንድንበረታታ፣ የታጠቅን እንድንሆን እንዲሁም ለሥራው እንድንቀናጅ ይረዱናል።—ማቴ. 24:14