ምሽግን እያፈረስን ነው
1 ሰይጣን የሐሰት ትምህርቶችንና የማታለያ ዘዴ በመጠቀም የበርካታ ሰዎችን ልብና አእምሮ ለዘመናት ሲያሳውር ኖሯል። ሰይጣን፣ የማትሞት ነፍስ አለች የሚለውን ጨምሮ ሥላሴንና የሲኦል እሳትን የመሰሉ መሠረተ ትምህርቶችን ሲያስፋፋ ቆይቷል። በተጨማሪም ሰዎች፣ የፈጣሪን መኖር እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛነት እንዲጠራጠሩ ያደርጋል። ዘረኝነትና ብሔራዊ ስሜት ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዳይቀበሉ የሚያደርጉ ሌሎች ከባድ እንቅፋቶች ናቸው። (2 ቆሮ. 4: 4) ታዲያ እንደነዚህ የመሰሉትን እንደ ምሽግ ጠንካራ የሆኑ አመለካከቶችን ማፍረስ የምንችለው እንዴት ነው?—2 ቆሮ. 10:4, 5
2 ከስሜት ጋር የተያያዘ ነው:- ሰዎች ለረጅም ጊዜ እውነት እንደሆነ ሲማሩ የቆዩት ነገር በአብዛኛው ከስሜታቸው ጋር ይያያዛል። አንዳንዶች የተሳሳቱ ትምህርቶችን ከልጅነታቸው ጀምረው ሲማሩ ቆይተዋል። እንዲህ ያሉ ሰዎችን ለመርዳት አመለካከታቸውን እንደምናከብር በሚያሳይ መንገድ መናገር ይኖርብናል።—1 ጴጥ. 3:15
3 ከላይ እንደተጠቀሱት ዓይነት ሰዎች በሚያጋጥሙን ጊዜ ምን ብለው እንደሚያምኑና እንደዚህ ያለ አመለካከት የያዙት ለምን እንደሆነ እንዲናገሩ በማድረግ እንደምናከብራቸው ማሳየት እንችላለን። (ያዕ. 1:19) በድጋሚ ሊያዩዋቸው የሚናፍቋቸው የሚወዷቸውን ሰዎች በሞት በማጣታቸው የተነሳ ነፍስ አትሞትም የሚል ጠንካራ እምነት ይኖራቸው ይሆናል። ወይም ዓመት በዓሎችን የሚያከብሩት ከቤተሰባቸው ጋር ጥሩ ጊዜ ለማሳለፍ ስለሚፈልጉ ይሆናል። አመለካከታቸውን ሲገልጹልን ማዳመጣችን ስሜታቸውን እንድንረዳ ከማስቻሉም በተጨማሪ ውጤታማ በሆነ መንገድ ምላሽ እንድንሰጥ ይረዳናል።—ምሳሌ 16:23 የ1980 ትርጉም
4 ኢየሱስን ኮርጁ:- ኢየሱስ፣ አንድ ሕግ አዋቂ ጥያቄዎችን ባቀረበለት ወቅት ምላሽ የሰጠበት መንገድ ለእኛ ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል። በዚህ ወቅት ኢየሱስ ለጥያቄው ቀጥተኛ መልስ አልሰጠም፤ ይህንንም ያደረገው ግለሰቡ በጉዳዩ ላይ ባለው ጠንካራ እምነት የተነሳ መልሱን መቀበል አዳጋች እንዳይሆንበት በማሰብ ሊሆን ይችላል። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ፣ ግለሰቡ ትኩረቱን ወደ ቅዱሳን መጻሕፍት እንዲያዞር ካደረገ በኋላ በጥቅሱ ላይ ያለውን አመለካከት እንዲገልጽ አደረገው፤ ከዚያም ምሳሌ በመጠቀም ወደ ትክክለኛ መደምደሚያ ላይ እንዲደርስ ረዳው።—ሉቃስ 10:25-37
5 የአምላክ ቃል፣ ሰዎች የሚያምኑባቸውን የሐሰት ትምህርቶች እንዲተዉ ያደርጋቸዋል። (ዕብ. 4:12) የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሰዎች በትዕግሥት የምናብራራላቸው ከሆነ የሐሰት ትምህርቶችን በመተው ነፃ የሚያወጣቸውን እውነት እንዲቀበሉ ልንረዳቸው እንችላለን።—ዮሐ. 8:32