‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’ የተባለውን መጽሐፍ ጥናት ለመምራት ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው?
1. ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’ የተባለው መጽሐፍ የተዘጋጀበት ዓላማ ምንድን ነው?
1 “በአምላክ መንፈስ መመራት” የሚል ጭብጥ በነበረው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’ የተባለ አዲስ መጽሐፍ በማግኘታችን በጣም ተደስተናል። በስብሰባው ላይ በማስታወቂያ እንደተነገረው ይህ መጽሐፍ የተዘጋጀው፣ መሠረታዊ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ለማስተማር ሳይሆን የይሖዋን የጽድቅ መሥፈርቶች እንድናውቅና እንድንወዳቸው ለመርዳት ታስቦ ነው። ይህ መጽሐፍ ከቤት ወደ ቤት ወይም መንገድ ላይ በምናደርገው አገልግሎት የምናበረክተው አይደለም።
2. ይህን መጽሐፍ የምንጠቀምበት እንዴት ነው? እነማንንስ ለማስጠናት እንጠቀምበታለን?
2 ይህ ጽሑፍ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ አጥንተው የጨረሱ ተማሪዎቻችንን ለማስጠናት የምንጠቀምበት ሁለተኛ መጽሐፍ ይሆናል። ሰዎች መንፈሳዊ እድገት የሚያደርጉበት ፍጥነት እንደሚለያይ አትዘንጉ። በእያንዳንዱ የጥናት ክፍለ ጊዜ የሚሸፈነው ትምህርት የተማሪውን አቅም ያገናዘበ መሆን ይኖርበታል። ተማሪው እየተወያያችሁበት ያላችሁትን ነጥብ በሚገባ እንደተረዳው እርግጠኞች መሆን ይኖርባችኋል። ግምት ውስጥ መግባት ያለበት የተለየ ሁኔታ ከሌለ በስተቀር፣ ይህን መጽሐፍ ከዚህ ቀደም በርካታ መጻሕፍትን ቢያጠኑም በስብሰባ ላይ የማይገኙና አኗኗራቸውን ከተማሩት የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር ለማስማማት ጥረት የማያደርጉ ሰዎችን ጥናት ለማስጀመር አንጠቀምበትም።
3. በአሁኑ ወቅት አምላክን አምልክ የተባለውን መጽሐፍ እያስጠናን ከሆንን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
3 በአሁኑ ወቅት አምላክን አምልክ የተባለውን መጽሐፍ እያስጠናህ ከሆነና መጽሐፉን ለማጠናቀቅ ጥቂት ምዕራፎች ብቻ ቀርተዋችሁ ከሆነ፣ የጀመራችሁትን መጽሐፍ ለመጨረስና ጥናትህ ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’ የተባለውን መጽሐፍ በግሉ እንዲያነበው ለማበረታታት ልትወስን ትችላለህ። ካልሆነ ግን የጀመራችሁትን መጽሐፍ አቋርጣችሁ አዲሱን መጽሐፍ ከመጀመሪያው ጀምሮ ማጥናታችሁ የተሻለ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንደተባለው መጽሐፍ ሁሉ በአዲሱ መጽሐፍ ላይ የሚገኙትን ተጨማሪ ክፍሎች የማጥናቱ ጉዳይ እንደ አስፈላጊነቱ የሚወሰን ይሆናል።
4. የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪያችን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እና ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’ የተባሉትን መጻሕፍት ከመጨረሱ በፊት ቢጠመቅ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
4 አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሁለቱን መጻሕፍት ከመጨረሱ በፊት ቢጠመቅ ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’ የተባለውን መጽሐፍ እስኪጨርስ ድረስ ጥናቱን መቀጠል ይኖርበታል። ጥናትህ ቢጠመቅም እንኳ በማስጠናት ያሳለፍከውን ሰዓት፣ ተመላልሶ መጠይቅና ጥናት ሪፖርት ማድረግ ትችላለህ። በጥናቱ ላይ የሚጋበዝ አስፋፊም ሰዓቱን ሪፖርት ማድረግ ይችላል።
5. ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’ የተባለውን መጽሐፍ፣ ለተወሰነ ጊዜ አገልግሎት አቋርጠው የቆዩ አስፋፊዎችን ለመርዳት ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው?
5 አገልግሎት አቋርጦ ለቆየ ሰው ጥናት እንድትመራ ከተመደብክ ከጉባኤው የአገልግሎት ኮሚቴ አንዱ ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’ ከተባለው መጽሐፍ ላይ የተወሰኑ ምዕራፎችን እንድታስጠናው ሊነግርህ ይችላል። ይህ ሲባል ግን ግለሰቡን ለረጅም ጊዜ ታስጠናዋለህ ማለት አይደለም። “ከአምላክ ፍቅር” እንዳንወጣ ለመርዳት ታስቦ የተዘጋጀው ይህ አዲስ መጽሐፍ እንዴት ያለ ግሩም መሣሪያ ነው!—ይሁዳ 21