መስበክ በመንፈሳዊ ምንጊዜም ጠንካሮች እንድንሆን ያደርገናል
1. በስብከቱ ሥራ መካፈላችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?
1 በስብከቱ ሥራ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ በመንፈሳዊ ጠንካሮች እንድንሆንና ደስታችን እንዲጨምር ያደርጋል። በአገልግሎት የምንካፈልበት ዋነኛው ምክንያት ይሖዋን ለማስደሰት እንደሆነ ግልጽ ነው። ይሁንና ‘ቃሉን እንድንሰብክ’ የተሰጠንን መመሪያ የምንታዘዝ ከሆነ ከይሖዋ በረከት የምናገኝ ከመሆኑም ሌላ በሌሎች መንገዶችም እንጠቀማለን። (2 ጢሞ. 4:2፤ ኢሳ. 48:17, 18) መስበክ በመንፈሳዊ ጠንካሮችና ደስተኞች እንድንሆን የሚያደርገን እንዴት ነው?
2. አገልግሎት የሚያጠነክረን እንዴት ነው?
2 አገልግሎት ያጠነክረናል እንዲሁም በረከት ያስገኝልናል፦ ምሥራቹን መስበካችን አሁን ባሉት ችግሮች ላይ ከማተኮር ይልቅ የአምላክ መንግሥት በሚያመጣቸው በረከቶች ላይ እንድናተኩር ያደርገናል። (2 ቆሮ. 4:18) የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ለሰዎች ስናብራራ ይሖዋ ቃል በገባቸው ተስፋዎች ላይ ያለን እምነት ይጠናከራል፤ እንዲሁም ለእውነት ያለን አድናቆት ይጨምራል። (ኢሳ. 65:13, 14) ሰዎች ‘የዓለም ክፍል እንዳይሆኑ’ የሚያስችላቸውን መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ ለመርዳት ስንጥር እኛም ከዓለም የተለየን ሆነን ለመገኘት ያደረግነው ቁርጥ ውሳኔ እየተጠናከረ ይሄዳል።—ዮሐ. 17:14, 16፤ ሮም 12:2
3. አገልግሎታችን ክርስቲያናዊ ባሕርያትን እንድናዳብር የሚረዳን እንዴት ነው?
3 በአገልግሎት መካፈል ክርስቲያናዊ ባሕርያትን እንድናዳብር ያስችለናል። ለምሳሌ “ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ሁሉንም ነገር [ለመሆን]” መጣራችን ትሕትናን ይበልጥ እንድናዳብር ይረዳናል። (1 ቆሮ. 9:19-23) “እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተገፈውና ተጥለው” ከሚገኙ ሰዎች ጋር በምንነጋገርበት ጊዜ ለሌሎች አዛኝ መሆንን ለመማር ብሎም ስሜታቸውን የመረዳት ችሎታ ለማዳበር የሚያስችለንን አጋጣሚ እናገኛለን። (ማቴ. 9:36) ሰዎች ተቃዋሚዎችና ለምንሰብከው መልእክት ግድየለሾች ቢሆኑም መስበካችንን መቀጠላችን ጽናትን ያስተምረናል። ሕይወታችንን ሌሎችን ለመርዳት መጠቀማችንም ይበልጥ ደስተኞች እንድንሆን ያደርገናል።—ሥራ 20:35
4. ስለ አገልግሎትህ ምን ይሰማሃል?
4 አምልኳችን ለሚገባው ብቸኛ አካል ክብር በሚያመጣ አገልግሎት የመካፈል መብት በማግኘታችን ምንኛ ተባርከናል! በአገልግሎት መካፈላችን በመንፈሳዊ ያጠነክረናል። እንዲሁም ‘ምሥራቹን በሚገባ በመመሥከሩ’ ሥራ ሙሉ በሙሉ መጠመዳችን የተትረፈረፈ በረከት ያስገኝልናል።—ሥራ 20:24