አገልግሎታችሁን ማስፋት ትችላላችሁ?
1. ከመስክ አገልግሎት ጋር በተያያዘ በጣም አጣዳፊ የሆነው ነገር ምንድን ነው? አጣዳፊ የሆነውስ ለምንድን ነው?
1 ኢየሱስ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የመንግሥቱን ምሥራች የመስማት ፍላጎት እንዳላቸው ስላስተዋለ ደቀ መዛሙርቱን “የመከሩ ሥራ ጌታ ወደ መከር ሥራው ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት” በማለት አዘዛቸው። (ማቴ. 9:37, 38) የምንኖረው የመከሩ ሥራ በሚካሄድበት የመጨረሻ ሰዓት ላይ በመሆኑ ምሥራቹን የመስበኩ ሥራ ከምንጊዜውም ይበልጥ አጣዳፊ ነው። ይህ ሁኔታ በመስክ አገልግሎት ላይ የበለጠ ተሳትፎ ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ በጸሎት ልናስብበት እንደሚገባ ያሳያል።—ዮሐ. 14:13, 14
2. አንዳንዶች ለመከሩ ሥራ ራሳቸውን እንዲያቀርቡ ለቀረበው ጥሪ ምላሽ የሰጡት እንዴት ነው?
2 አገልግሎታችሁን ማስፋት የምትችሉባቸው መንገዶች፦ ብዙዎች ከይሖዋ በሚያገኙት አመራርና እርዳታ ታግዘው በአቅኚነት አገልግሎት መካፈል ችለዋል። (መዝ. 26:2, 3፤ ፊልጵ. 4:6) አንዳንዶች ደግሞ በዓመት ውስጥ ለአንድ ወይም ከዚያ ለሚበልጡ ወራት ረዳት አቅኚ ሆነው ለማገልገል ልዩ ጥረት አድርገዋል። ይህ ደግሞ አገልግሎታቸውን ለማስፋት የሚያስችል ግሩም አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። ረዳት አቅኚ ሆነው በማገልገላቸው ያገኙት ደስታ አብዛኞቹ የዘወትር አቅኚ ስለ መሆን በቁም ነገር እንዲያስቡበት አድርጓቸዋል።—ሥራ 20:35
3. ከዚህ ቀደም አቅኚ ከነበራችሁ ስለ ምን ጉዳይ በቁም ነገር ማሰብ ትችላላችሁ?
3 እንደገና የዘወትር አቅኚ መሆን ትችላላችሁ? ከዚህ ቀደም የዘወትር አቅኚ ሆናችሁ አገልግላችሁ ከሆነ ስለዚያ ጊዜ ጥሩ ትዝታ እንደሚኖራችሁ ምንም ጥርጥር የለውም። እንደገና አቅኚ ለመሆን የምትችሉበት መንገድ ይኖር እንደሆነ በጸሎት አስባችሁበት ታውቃላችሁ? አቅኚነታችሁን እንድታቋርጡ ያደረጓችሁ ምክንያቶች አሁን ላይኖሩ ይችላሉ። በዚህ ልዩ መብት እንደገና መካፈል የምትችሉበት ጊዜ አሁን ሊሆን ይችላል።—1 ዮሐ. 5:14, 15
4. ለሁላችንም ምን ልዩ መብት ተከፍቶልናል?
4 በአሁኑ ጊዜ የመከሩ ሥራ በአስደሳች ሁኔታ እየተካሄደ ሲሆን በቅርቡ ይጠናቀቃል። (ዮሐ. 4:35, 36) ሁላችንም ሁኔታችንን አስተካክለን በመስክ አገልግሎት የምናደርገውን ተሳትፎ ማስፋት እንችል እንደሆነና እንዳልሆነ ለማወቅ አሁን ያለንበትን ሁኔታ እንመርምር። ከልብ ራሳችንን መርምረን አገልግሎታችንን ማስፋት እንደማንችል ከተሰማን በአገልግሎት ይበልጥ ውጤታማ መሆን የምንችልበት መንገድ መፈልግ እንችል ይሆናል። (ማር. 12:41-44) ይሖዋ ለዚህ ልዩ ሥራ እንዲጠቀምባቸው በሚያስችል ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ አስፋፊዎች ሁሉ በእርግጥም ግሩም መብት ተከፍቶላቸዋል!—መዝ. 110:3