መጽሔቶችን ለማበርከት ምን ማለት ይቻላል?
መጠበቂያ ግንብ ጥቅምት 1
“በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች በፈጣሪ መኖር አያምኑም። ይህ የሆነው ለምን ይመስልዎታል? [ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው።] አንደኛው ምክንያት እዚህ ጥቅስ ላይ የተጠቀሰው ሐሳብ ሊሆን ይችላል። [ዕንባቆም 1:2, 3ን አንብብ።] ይህ ርዕሰ ትምህርት በአምላክ መኖር የማያምኑ ሰዎች እሱን በተመለከተ ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።” በገጽ 11 ላይ የሚገኘውን ርዕስ አስተዋውቀው።
ንቁ! ጥቅምት 2009
“በዛሬው ጊዜ ቤተሰቦች በርካታ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል ቢባል አይስማሙም? [ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው።] ብዙ ሰዎች፣ መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል ጠቃሚ ምክር እንደያዘ አያውቁም። እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት። [በመጽሔቱ ውስጥ የሚገኝ አንድ ጥቅስ አንብብ።] ልዩ እትም የሆነው ይህ የንቁ! መጽሔት እያንዳንዱ ቤተሰብ የሚያጋጥሙትን የተለያዩ ችግሮች በተሳካ ሁኔታ ለመወጣት መጽሐፍ ቅዱስ ምን እርዳታ እንደሚሰጥ ያብራራል።”
መጠበቂያ ግንብ ኅዳር 1
“ሰዎች በየቤተ ክርስቲያኖቻቸው የሚማሯቸው ትምህርቶች ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ይመስልዎታል? [ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው።] መጽሐፍ ቅዱስ በሐሰት ትምህርት እንዳንታለል መጠንቀቅ እንዳለብን ይነግረናል። [ቆላስይስ 2:8ን አንብብ።] ይህ መጽሔት ከአምላክ ቃል ጋር በቀጥታ የሚጋጩት ስድስት ትምህርቶች የትኞቹ እንደሆኑ ይናገራል።”
ንቁ! ኅዳር 2009
“እንደ ሞባይልና ኮምፒውተር ያሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሰዎች የዕለት ተዕለት ሕይወት ክፍል ሆነዋል። የቴክኖሎጂ ውጤቶች ጊዜ የሚቆጥቡልን ይመስልዎታል ወይስ ጊዜ የሚያባክኑብን? [ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው።] አብዛኞቹ ሰዎች ጊዜያችንን በጥበብ እንድንጠቀምበት የሚያበረታታን ይህ ጥቅስ በያዘው ሐሳብ ይስማማሉ። [ኤፌሶን 5:15, 16ን አንብብ።] ይህ መጽሔት የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ሚዛናዊ በሆነና ለሌሎች አሳቢ መሆናችንን በሚያሳይ መንገድ እንዴት መጠቀም እንደምንችል ይናገራል።”