‘አትፍሩ’
1. ልክ እንደ ኤርምያስ የትኞቹ ነገሮች ፈታኝ ሊሆኑብን ይችላሉ?
1 ኤርምያስ የነቢይነት ተልእኮ ሲሰጠው ብቃት እንደሌለው ተሰምቶት ነበር። ይሁን እንጂ ይሖዋ “አትፍራቸው” በማለት ያበረታታው ሲሆን ተልእኮውን ለመወጣት የሚያስፈልገውን ኃይልም በደግነት ሰጥቶታል። (ኤር. 1:6-10) በአሁኑ ጊዜም ቢሆን ዓይን አፋርነት ወይም በራስ ያለመተማመን ስሜት፣ በአገልግሎት የምናደርገውን ተሳትፎ ሊነካብን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ፣ ሰዎች ለእኛም ሆነ ለመልእክታችን ያላቸው አመለካከት ፍርሃት ሊያሳድርብንና ምሥክርነት እንዳንሰጥ እንቅፋት ሊሆንብን ይችላል። ታዲያ እንዲህ ዓይነቱን ፍርሃት ለማሸነፍ ምን ማድረግ እንችላለን? ይህስ በግለሰብ ደረጃ ምን በረከት ያስገኝልናል?
2. ከአገልግሎት ጋር በተያያዘ የሚሰማንን ፍርሃት ለማሸነፍ አስቀድመን መዘጋጀታችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?
2 አስቀድማችሁ ተዘጋጁ፦ በሚገባ መዘጋጀት ፍርሃትን ለማሸነፍ የሚረዳ ዓይነተኛ መንገድ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በአገልግሎት ሊያጋጥሙን ስለሚችሉ ውይይት የሚያስቆሙ ሐሳቦች አስቀድመን ካሰብን በተደጋጋሚ ለሚነሱ የተቃውሞ ሐሳቦች መልስ ለመስጠት የተዘጋጀን እንሆናለን። (ምሳሌ 15:28) ታዲያ በትምህርት ቤትና በአገልግሎት ለሚያጋጥሙ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አስቀድማችሁ መዘጋጀት እንድትችሉ በቤተሰብ አምልኮ ወቅት ለምን አትለማመዱም?—1 ጴጥ. 3:15
3. በይሖዋ መታመናችን ፍርሃት ለማሸነፍ የሚረዳን እንዴት ነው?
3 በይሖዋ ታመኑ፦ በአምላክ መታመን የፍርሃት ፍቱን ማርከሻ ነው። ይሖዋ እንደሚረዳን ዋስትና ሰጥቶናል። (ኢሳ. 41:10-13) ይህ ደግሞ ማንኛውም ሰው ሊኖረው ከሚችለው ዋስትና እጅግ የላቀ ነው! በተጨማሪም ኢየሱስ ያልተጠበቀ ሁኔታ በሚያጋጥመን ጊዜ እንኳ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ጥሩ ምሥክርነት መስጠት እንድንችል እንደሚረዳን ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (ማር. 13:11) ስለዚህ ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጠን ዘወትር እንለምነው።—ሉቃስ 11:13
4. ተፈታታኝ ነገሮች ቢኖሩም በአገልግሎት መጽናታችን ምን በረከቶች ያስገኝልናል?
4 ምን በረከት እናገኛለን? ተፈታታኝ ነገሮች ቢኖሩም በአገልግሎት መጽናታችን ወደፊት የሚያጋጥሙንን ሌሎች ፈተናዎች በተሳካ ሁኔታ ለመወጣት የሚያስችል ጥንካሬ ያስገኝልናል። በተጨማሪም በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ የሚገኘውን በድፍረት የመናገር ችሎታ እናዳብራለን። (ሥራ 4:31) በይሖዋ እርዳታ ፍርሃታችንን ስናሸንፍ በማዳን ኃይሉ ላይ ያለን እምነትና ትምክህትም ይጠናከራል። (ኢሳ. 33:2) ከዚህም በላይ በሰማይ ያለው አባታችንን እያስደሰትነው እንደሆነ ስለሚሰማን እርካታና ደስታ እናገኛለን። (1 ጴጥ. 4:13, 14) እንግዲያው የይሖዋ ድጋፍ ምንጊዜም እንደማይለየን በመተማመን የመንግሥቱን መልእክት በድፍረት እናውጅ!