የጥናት ርዕስ 26
ፍቅር ፍርሃትን እንድናሸንፍ የሚረዳን እንዴት ነው?
“ይሖዋ ከጎኔ ነው፤ አልፈራም።”—መዝ. 118:6
መዝሙር 105 “አምላክ ፍቅር ነው”
ማስተዋወቂያa
1. ብዙዎች የትኞቹ ነገሮች ያስፈሯቸዋል?
አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች ያጋጠሟቸውን የሚከተሉትን ሁኔታዎች ለማሰብ ሞክር። ኔስተር እና ባለቤቱ ማሪያ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ተዛውረው ለማገልገል ፈልገው ነበር።b እዚህ ግባቸው ላይ ለመድረስ ግን የአኗኗር ዘይቤያቸውን መቀየር ያስፈልጋቸዋል። ሆኖም በአነስተኛ ገቢ ቢኖሩ ደስተኛ እንደማይሆኑ በማሰብ ፈርተው ነበር። ቢንያም እውነትን የሰማው በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ስደት በሚደርስበት አገር ውስጥ ነው። በመሆኑም የይሖዋ ምሥክር ከሆነ ስደት ሊደርስበት እንደሚችል ተገንዝቦ ነበር። ይህም ፍርሃት አሳደረበት። ሆኖም ‘ቤተሰቦቼ ስለ አዲሱ ሃይማኖቴ ቢያውቁ ምን ይሉኛል?’ የሚለው ጉዳይ ይበልጥ አስፈርቶት ነበር። ቫሌሪ ከባድ በሆነ የካንሰር በሽታ ተያዘች፤ እንዲሁም ከደም ጋር በተያያዘ ያላትን ቅዱስ ጽሑፋዊ አቋም የሚያከብርላት የቀዶ ጥገና ሐኪም ለማግኘት ተቸግራ ነበር። በመሆኑም ‘እሞታለሁ’ ብላ ፈርታ ነበር።
2. ፍርሃታችንን ለማሸነፍ ጥረት ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?
2 አንተስ እንዲህ ባሉ ነገሮች ምክንያት ፈርተህ ታውቃለህ? ብዙዎቻችን ፈርተን እናውቃለን። ፍርሃታችንን ለመቆጣጠር ጥረት ካላደረግን ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ሊያበላሽብን የሚችል መጥፎ ውሳኔ ልናደርግ እንችላለን። ሰይጣንም የሚፈልገው ይህንን ነው። በተጨማሪም ሰይጣን ፍርሃታችንን ተጠቅሞ የይሖዋን ሕጎች እንድንጥስ ለማድረግ ይሞክራል፤ ከእነዚህም መካከል ምሥራቹን እንድንሰብክ የተሰጠን ትእዛዝ ይገኝበታል። (ራእይ 12:17) ሰይጣን ክፉ፣ ጨካኝና ኃይለኛ ነው። ሆኖም ራስህን ከእሱ መጠበቅ ትችላለህ። እንዴት?
3. ፍርሃታችንን እንድናሸንፍ ምን ሊረዳን ይችላል?
3 ይሖዋ እንደሚወደንና ከጎናችን እንደሆነ ከተማመንን ሰይጣን ሊያስፈራን አይችልም። (መዝ. 118:6) ለምሳሌ የመዝሙር 118 ጸሐፊ በጣም የሚያስጨንቁ ሁኔታዎች አጋጥመውት ነበር። ብዙ ጠላቶች ነበሩት፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ ከፍተኛ ሥልጣን ነበራቸው (ቁጥር 9, 10)። ከባድ ጫና የደረሰበት ጊዜም ነበር (ቁጥር 13)። በተጨማሪም ይሖዋ ጠንከር ያለ ተግሣጽ ሰጥቶታል (ቁጥር 18)። ያም ቢሆን መዝሙራዊው “አልፈራም” ብሎ ለመዘመር ተነሳስቷል። እንዲህ ያለ የመረጋጋት ስሜት እንዲሰማው የረዳው ምንድን ነው? ይሖዋ ተግሣጽ ቢሰጠውም በጣም እንደሚወደው ያውቅ ነበር። መዝሙራዊው ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥመው አፍቃሪ የሆነው አምላኩ እሱን ለመርዳት ምንጊዜም ዝግጁ እንደሆነ እርግጠኛ ነበር።—መዝ. 118:29
4. አምላክ እንደሚወደን ከተማመንን የትኞቹን የፍርሃት ዓይነቶች ማሸነፍ እንችላለን?
4 ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ እንደሚወደን ልንተማመን ይገባል። ይህን ማመናችን ሦስት የተለመዱ የፍርሃት ዓይነቶችን እንድናሸንፍ ይረዳናል፦ (1) ‘ቤተሰቤን ማስተዳደር ቢያቅተኝስ’ የሚል ፍርሃት፣ (2) ሰውን መፍራት እንዲሁም (3) ሞትን መፍራት። በመግቢያችን ላይ የተጠቀሱት ክርስቲያኖች አምላክ እንደሚወዳቸው በመተማመናቸው ፍርሃታቸውን ማሸነፍ ችለዋል።
‘ቤተሰቤን ማስተዳደር ቢያቅተኝስ’ የሚል ፍርሃት
አንድ ወንድም ቤተሰቡን ለማስተዳደር ዓሣ ሲያጠምድ፤ ልጁ በአቅራቢያው አለ (አንቀጽ 5ን ተመልከት)
5. አንድ የቤተሰብ ራስ የትኞቹ ጉዳዮች ሊያስጨንቁት ይችላሉ? (ሽፋኑን ተመልከት።)
5 ክርስቲያን የሆነ የቤተሰብ ራስ ቤተሰቡን የማስተዳደር ኃላፊነቱን በቁም ነገር ይመለከተዋል። (1 ጢሞ. 5:8) አንተም የቤተሰብ ራስ ከሆንክ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ‘ሥራዬን አጣለሁ’ የሚል ፍርሃት አድሮብህ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም ቤተሰብህን መመገብ ወይም የቤት ኪራይ መክፈል ሊያቅትህ እንደሚችል በማሰብ ተጨንቀህ ይሆናል። ሥራህን ካጣህ ሌላ ሥራ ላታገኝ እንደምትችል ፈርተህም ይሆናል። ወይም ቀደም ሲል እንደተጠቀሱት እንደ ኔስተርና እንደ ማሪያ በአነስተኛ ገቢ መኖር እንደማትችል በማሰብ በአኗኗርህ ላይ ለውጥ ለማድረግ አመንትተህ ሊሆን ይችላል። ሰይጣን እንዲህ ያለውን ፍርሃት በመጠቀም ብዙ ስኬት አግኝቷል።
6. ሰይጣን ምን ሊያሳምነን ይሞክራል?
6 ሰይጣን፣ ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ እንደማያስብልን እና ቤተሰባችንን ለመንከባከብ እንደማይረዳን ሊያሳምነን ይሞክራል። በመሆኑም ሥራችንን ላለማጣት ስንል ምንም ነገር ከማድረግ ወደኋላ ማለት እንደሌለብን ልናስብ እንችላለን፤ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ቢያስጥሰንም እንኳ ማለት ነው።
7. ኢየሱስ ምን ዋስትና ሰጥቶናል?
7 አብን ከማንም በተሻለ የሚያውቀው ኢየሱስ፣ አምላክ ‘ገና ሳንለምነው ምን እንደሚያስፈልገን እንደሚያውቅ’ ዋስትና ሰጥቶናል። (ማቴ. 6:8) ኢየሱስ፣ ይሖዋ የሚያስፈልጉንን ነገሮች ሊያሟላልን እንደሚፈልግም ያውቃል። ክርስቲያን እንደመሆናችን መጠን የአምላክ ቤተሰብ አባል ነን። ይሖዋ የቤተሰባችን ራስ እንደመሆኑ መጠን በ1 ጢሞቴዎስ 5:8 ላይ ካስጻፈው መሠረታዊ ሥርዓት ጋር የሚስማማ እርምጃ እንደሚወስድ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።
ይሖዋ የሚያስፈልገንን ነገር እንድናገኝ ያደርጋል። እኛን ለመርዳት ወንድሞቻችንን ሊጠቀም ይችላል (አንቀጽ 8ን ተመልከት)d
8. (ሀ) ‘ቤተሰቤን ማስተዳደር ቢያቅተኝስ’ የሚለውን ፍርሃት ለማሸነፍ ምን ሊረዳን ይችላል? (ማቴዎስ 6:31-33) (ለ) በሥዕላዊ መግለጫው ላይ እንደሚታየው ለአንዲት እህት ምግብ እየወሰዱ ያሉትን ባልና ሚስት ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?
8 ይሖዋ እኛንም ሆነ ቤተሰባችንን እንደሚወደን የምንተማመን ከሆነ የሚያስፈልገንን ነገር እናጣለን ብለን እንድንጠራጠር የሚያደርገን ምንም ምክንያት የለም። (ማቴዎስ 6:31-33ን አንብብ።) ይሖዋ የሚያስፈልገንን ነገር ሊያሟላልን ይፈልጋል። ደግሞም አፍቃሪና ለጋስ አምላክ ነው! ምድርን ሲፈጥር ለመኖር የሚያስፈልጉንን መሠረታዊ ነገሮች በመስጠት ብቻ አልተወሰነም። በፍቅር ተነሳስቶ በደስታ እንድንሞላ የሚያደርጉ ብዙ ነገሮችን ፈጥሮልናል። (ዘፍ. 2:9) አንዳንድ ጊዜ ያለን ገንዘብ ከመተዳደሪያ የማያልፍ ቢሆንም እንኳ ቢያንስ መተዳደሪያችንን እንዳላጣን ማስታወስ ይኖርብናል። ይህ የሆነው ይሖዋ የሚያስፈልገንን ነገር ስላሟላልን ነው። (ማቴ. 6:11) በአሁኑ ጊዜ መሥዋዕት የምናደርገው ማንኛውም ቁሳዊ ነገር አፍቃሪው አምላካችን ይሖዋ አሁንም ሆነ ወደፊት ከሚሰጠን በረከት ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። ኔስተር እና ማሪያም ይህን መገንዘብ ችለዋል።—ኢሳ. 65:21, 22
9. ኔስተርና ማሪያ ከተዉት ምሳሌ ምን እንማራለን?
9 ኔስተር እና ማሪያ ኮሎምቢያ ውስጥ የተደላደለ ሕይወት ነበራቸው። እንዲህ ብለዋል፦ “ሕይወታችንን ቀላል በማድረግ አገልግሎታችንን ለማስፋት አሰብን። ሆኖም በአነስተኛ ገቢ ብንኖር ደስታ ልናጣ እንችላለን ብለን ፈራን።” ታዲያ ፍርሃታቸውን እንዲያሸንፉ የረዳቸው ምንድን ነው? ይሖዋ እስካሁን በተለያዩ መንገዶች ፍቅር ያሳያቸው እንዴት እንደሆነ ለማስተዋል ሞከሩ። የይሖዋ እንክብካቤ እንደማይለያቸው በመተማመን ዳጎስ ያለ ገንዘብ የሚያስገኝላቸውን ሥራ ተዉ። ቤታቸውን ሸጠው ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት የአገሪቱ ክፍል ተዛወሩ። ስላደረጉት ውሳኔ ሲያስቡ ምን ይሰማቸዋል? ኔስተር እንዲህ ብሏል፦ “የማቴዎስ 6:33ን እውነተኝነት አይተናል። በቁሳዊ ምንም ነገር ጎድሎብን አያውቅም። እንዲያውም ሕይወታችን ከቀድሞው ይበልጥ አስደሳች ሆኗል።”
ሰውን መፍራት
10. ሰዎች ሌሎች ሰዎችን የሚፈሩ መሆኑ የማያስገርመው ለምንድን ነው?
10 ሰዎች ለበርካታ ዘመናት እርስ በርስ ሲጎዳዱ ኖረዋል። (መክ. 8:9) ለምሳሌ ባለሥልጣኖች ሥልጣናቸውን ያለአግባብ ይጠቀማሉ፤ ወንጀለኞች አሰቃቂ ድርጊቶችን ይፈጽማሉ፤ ጉልበተኛ ተማሪዎች አብረዋቸው የሚማሩ ልጆችን ይሳደባሉ እንዲሁም ያስፈራራሉ፤ ይባስ ብሎም በቤተሰባቸው አባላት ላይ የጭካኔ ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎች አሉ። በእርግጥም ሰዎች ሌሎች ሰዎችን የሚፈሩ መሆኑ የሚያስገርም አይደለም! ሰይጣን እኛን ለማጥቃት የሰው ፍርሃትን የሚጠቀመው እንዴት ነው?
11-12. ሰይጣን የሰው ፍርሃትን ተጠቅሞ እኛን የሚያጠቃን እንዴት ነው?
11 ሰይጣን የሰው ፍርሃትን ተጠቅሞ አቋማችንን እንድናላላ እና መስበካችንን እንድናቆም ሊያስገድደን ይሞክራል። አንዳንድ መንግሥታት በሰይጣን ግፊት ሥራችን ላይ እገዳ ይጥላሉ እንዲሁም ስደት ያደርሱብናል። (ሉቃስ 21:12፤ ራእይ 2:10) በሰይጣን ዓለም ውስጥ ያሉ ብዙ ሰዎች ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የተዛባ መረጃ ወይም ዓይን ያወጣ ውሸት ይናገራሉ። አንዳንድ ሰዎች እነዚህን ውሸቶች በማመን ሊያሾፉብን አልፎ ተርፎም አካላዊ ጥቃት ሊያደርሱብን ይችላሉ። (ማቴ. 10:36) ሰይጣን እነዚህን ዘዴዎች መጠቀሙ ሊያስገርመን ይገባል? በፍጹም! ምክንያቱም እነዚህን ዘዴዎች በመጀመሪያው መቶ ዘመንም ተጠቅሞባቸዋል።—ሥራ 5:27, 28, 40
ቤተሰቦቻችን ቢቃወሙንም እንኳ ይሖዋ እንደሚወደን እርግጠኞች መሆን እንችላለን (ከአንቀጽ 12-14ን ተመልከት)e
12 ሰይጣን የሚጠቀመው የመንግሥታትን ተቃውሞ ብቻ አይደለም። አንዳንድ ሰዎች እውነትን ሲቀበሉ ‘ቤተሰቦቼ ምን ይሉኛል’ የሚለው ነገር ከአካላዊ ጥቃት ይበልጥ ያስፈራቸዋል። ቤተሰቦቻቸውን በጣም ይወዷቸዋል፤ በመሆኑም ስለ ይሖዋ እንዲያውቁና እሱን እንዲወዱት ይፈልጋሉ። ቤተሰቦቻቸው ስለ እውነተኛው አምላክና ስለ አገልጋዮቹ መጥፎ ነገሮችን ሲናገሩ መስማት በጣም ያሳዝናቸዋል። እርግጥ አንዳንድ ጊዜ ተቃዋሚ የነበሩት ቤተሰቦቻቸው በኋላ ላይ እውነትን ይቀበላሉ። ሆኖም የይሖዋ ምሥክር ለመሆን በመወሰናችን ምክንያት ቤተሰቦቻችን ሙሉ በሙሉ ቢያገሉንስ? በዚህ ጊዜ ምን ምላሽ እንሰጣለን?
13. ይሖዋ እንደሚወደን ማመናችን ቤተሰቦቻችን ቢያገሉንም እንኳ እንድንጸና የሚረዳን እንዴት ነው? (መዝሙር 27:10)
13 በመዝሙር 27:10 ላይ የሚገኘው ግሩም ሐሳብ ያጽናናናል። (ጥቅሱን አንብብ።) ይሖዋ ምን ያህል እንደሚወደን ማስታወሳችን ተቃውሞ ቢያጋጥመንም እንድንረጋጋ ይረዳናል። ጽናታችንን እንደሚባርክልንም መተማመን እንችላለን። ይሖዋ አካላዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ከማንም በላይ ያሟላልናል። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ቢንያም ይህን መገንዘብ ችሏል።
14. ከቢንያም ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?
14 ቢንያም ከፍተኛ ተቃውሞ እንደሚያጋጥመው ቢያውቅም የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ወሰነ። ቢንያም ይሖዋ እንደሚወደው ማወቁ የሰው ፍርሃትን ለማሸነፍ የረዳው እንዴት እንደሆነ እንመልከት። እንዲህ ብሏል፦ “ስደቱ ከጠበቅኩት በላይ ነበር። ባለሥልጣናት ከሚያደርሱብኝ ስደት ይበልጥ ያስፈራኝ ግን የቤተሰቦቼ ተቃውሞ ነው። የይሖዋ ምሥክር ለመሆን በመወሰኔ አማኝ ያልሆነው አባቴ እንደሚያዝንብኝና የቤተሰቦቼን ተቀባይነት እንደማጣ በማሰብ ፈርቼ ነበር።” ሆኖም ቢንያም፣ ይሖዋ የሚወዳቸውን ሰዎች ምንጊዜም እንደሚንከባከብ እርግጠኛ ነበር። ቢንያም እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ ሕዝቦቹ ያጋጠማቸውን የኢኮኖሚ ችግር፣ ጭፍን ጥላቻ እና ሕዝባዊ ተቃውሞ እንዲቋቋሙ የረዳቸው እንዴት እንደሆነ ለማሰብ ሞከርኩ። እኔም ይሖዋን የሙጥኝ እስካልኩ ድረስ እንደሚባርከኝ እርግጠኛ ነበርኩ። በተደጋጋሚ በታሰርኩበትና አካላዊ ሥቃይ በደረሰብኝ ጊዜ፣ በታማኝነት እስከጸናን ድረስ የይሖዋ እርዳታ መቼም ቢሆን እንደማይለየን በገዛ ዓይኔ ተመልክቻለሁ።” ይሖዋ ለቢንያም አባት ሆኖለታል፤ ሕዝቦቹ ደግሞ ቤተሰብ ሆነውለታል።
ሞትን መፍራት
15. ሞትን መፍራት ተፈጥሯዊ ነው የምንለው ለምንድን ነው?
15 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሞት ጠላት እንደሆነ ይናገራል። (1 ቆሮ. 15:25, 26) ስለ ሞት ስናስብ እንጨነቅ ይሆናል፤ በተለይ የምንወደው ሰው ወይም እኛ ራሳችን በጠና ስንታመም ሞት ይበልጥ ሊያስፈራን ይችላል። ሞት የሚያስፈራን ለምንድን ነው? ምክንያቱም ይሖዋ የፈጠረን ለዘላለም የመኖር ፍላጎት እንዲኖረን አድርጎ ነው። (መክ. 3:11) ሞትን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መፍራት ሕይወታችንን ሊታደግልን ይችላል። ለምሳሌ ከአመጋገብና አካላዊ እንቅስቃሴ ከማድረግ ጋር በተያያዘ ጥሩ ውሳኔ እንድናደርግ፣ ከታመምን ሕክምና እንድናገኝና መድኃኒት እንድንወስድ እንዲሁም ሕይወታችንን አላስፈላጊ አደጋ ላይ እንዳንጥል ሊያነሳሳን ይችላል።
16. ሰይጣን ለሞት ያለንን ተፈጥሯዊ ፍራቻ ተጠቅሞ ሊያጠቃን የሚሞክረው እንዴት ነው?
16 ሰይጣን ሕይወታችንን እንደምንወድ ያውቃል። በመሆኑም ዕድሜያችንን ለማራዘም ስንል ከይሖዋ ጋር ያለንን ወዳጅነት ጨምሮ ማንኛውንም ነገር መሥዋዕት ከማድረግ ወደኋላ እንደማንል ተናግሯል። (ኢዮብ 2:4, 5) ሰይጣን ምንኛ ተሳስቷል! ያም ቢሆን “ለሞት የመዳረግ አቅም ያለው” ሰይጣን፣ ለሞት ያለንን ተፈጥሯዊ ፍራቻ ተጠቅሞ ይሖዋን እንድንተው ለማድረግ ይሞክራል። (ዕብ. 2:14, 15) አንዳንድ ጊዜ የሰይጣን ወኪሎች፣ የይሖዋ አገልጋዮች እምነታቸውን ካልካዱ እንደሚገድሏቸው ይዝቱባቸዋል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሰይጣን፣ ያለብንን ከባድ የጤና እክል ተጠቅሞ አቋማችንን እንድናላላ ለማድረግ ይሞክራል። ሐኪሞች ወይም የማያምኑ ቤተሰቦቻችን ደም እንድንወስድ ይገፋፉን ይሆናል፤ ደም መውሰድ ደግሞ የአምላክን ሕግ መጣስ ነው። አንዳንዶች ደግሞ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚጋጭ ሕክምና እንድንከታተል ሊያግባቡን ይሞክሩ ይሆናል።
17. በሮም 8:37-39 መሠረት ሞትን መፍራት የማይኖርብን ለምንድን ነው?
17 መሞት እንደማንፈልግ የታወቀ ነው። ሆኖም ብንሞትም እንኳ ይሖዋ እኛን መውደዱን እንደማያቆም ማስታወስ ይኖርብናል። (ሮም 8:37-39ን አንብብ።) ይሖዋ ወዳጆቹ ቢሞቱም እንኳ በሕይወት ያሉ ያህል ያስታውሳቸዋል። (ሉቃስ 20:37, 38) በትንሣኤ ሊያስነሳቸው ይናፍቃል። (ኢዮብ 14:15) ይሖዋ ‘የዘላለም ሕይወት እንዲኖረን’ ሲል ውድ ዋጋ ከፍሏል። (ዮሐ. 3:16) ይሖዋ በጣም እንደሚወደንና እንደሚያስብልን እናውቃለን። ስለዚህ ስንታመም ወይም ከሞት ጋር ስንፋጠጥ ይሖዋን ከመተው ይልቅ ማጽናኛ፣ ጥበብና ብርታት እንዲሰጠን ወደ እሱ መቅረብ ይኖርብናል። ቫሌሪ እና ባለቤቷ ያደረጉትም ይህንኑ ነው።—መዝ. 41:3
18. ከቫሌሪ ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?
18 ቫሌሪ 35 ዓመት ሲሆናት ብዙ ጊዜ የማይከሰትና በፍጥነት የሚሰራጭ ካንሰር እንዳለባት ታወቀ። ፍቅር የሞት ፍርሃቷን እንድታሸንፍ የረዳት እንዴት እንደሆነ እንመልከት። ቫሌሪ እንዲህ ብላለች፦ “ካንሰር እንዳለብኝ ሲታወቅ ሕይወታችን በአንድ ጀንበር ተቀየረ። ከባድ ቀዶ ሕክምና ማድረጌ የግድ ነበር። ብዙ የቀዶ ጥገና ሐኪሞችን አማከርኩ። ሆኖም ሁሉም ያለደም ቀዶ ሕክምና ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆኑም። እኔ ግን የአምላክን ሕግ ጥሼ ደም ለመውሰድ ፈቃደኛ አልነበርኩም። ይሖዋ ሕይወቴን ሙሉ በተለያዩ መንገዶች ፍቅር አሳይቶኛል። አሁን እኔም ለእሱ ያለኝን ፍቅር የማሳይበት አጋጣሚ አገኘሁ። ከጤናዬ ጋር በተያያዘ መጥፎ ዜና በሰማሁ ቁጥር ይሖዋን ለማስደሰትና ሰይጣን እንዳያሸንፍ ለማድረግ ያለኝ ቁርጠኝነት ይጨምር ነበር። በኋላም ያለደም የተሳካ ቀዶ ሕክምና አደረግኩ። አሁንም የጤና ችግር ቢኖርብኝም ይሖዋ በሚያስፈልገን ሁሉ ከጎናችን ተለይቶ አያውቅም። ለምሳሌ ካንሰር እንዳለብኝ ከመታወቁ በፊት ባደረግነው የሳምንቱ መጨረሻ ስብሰባ ላይ ያጠናነው መጠበቂያ ግንብ ‘በዛሬው ጊዜ የሚያጋጥሙንን መከራዎች በድፍረት መቋቋም’ የሚል ርዕስ ነበረው።c ይህ ርዕስ በእጅጉ አጽናንቶናል። ደጋግመን አነበብነው። እንዲህ ያሉ ርዕሰ ጉዳዮችን ማንበባችንና ጥሩ የሆነ መንፈሳዊ ልማድ ማዳበራችን እኔና ባለቤቴ ውስጣዊ ሰላም እንዲኖረን፣ ሚዛናችንን እንድንጠብቅ እንዲሁም ጥሩ ውሳኔ እንድናደርግ ረድቶናል።”
ፍርሃታችንን ማሸነፍ
19. በቅርቡ ምን ይከሰታል?
19 በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ክርስቲያኖች በይሖዋ እርዳታ ከባድ ፈተናዎችን መቋቋምና ሰይጣንን ስኬታማ በሆነ መንገድ መቃወም ችለዋል። (1 ጴጥ. 5:8, 9) አንተም እንዲህ ማድረግ ትችላለህ። ይሖዋ በቅርቡ ለኢየሱስና አብረውት ለሚገዙት መመሪያ በመስጠት ‘የዲያብሎስን ሥራ እንዲያፈርሱ’ ያደርጋል። (1 ዮሐ. 3:8) ከዚያ በኋላ በምድር ላይ ያሉ የአምላክ አገልጋዮች በሙሉ ‘ምንም ነገር አይፈሩም፤ የሚያሸብራቸውም ነገር አይኖርም።’ (ኢሳ. 54:14፤ ሚክ. 4:4) እስከዚያው ግን ፍርሃታችንን ለማሸነፍ ጥረት ማድረጋችንን መቀጠል ይኖርብናል።
20. ፍርሃታችንን እንድናሸንፍ ምን ሊረዳን ይችላል?
20 ይሖዋ አገልጋዮቹን እንደሚወድና እንደሚጠብቅ ያለንን እምነት ማጠናከር ይኖርብናል። ይሖዋ ከዚህ ቀደም አገልጋዮቹን የጠበቃቸው እንዴት እንደሆነ ማሰላሰላችንና ለሌሎች መናገራችን በዚህ ረገድ ይረዳናል። ከባድ ፈተናዎች ሲያጋጥሙን እኛን በግለሰብ ደረጃ የረዳን እንዴት እንደሆነም ማስታወስ ይኖርብናል። በይሖዋ እርዳታ ፍርሃታችንን ማሸነፍ እንችላለን!—መዝ. 34:4
መዝሙር 129 ጸንተን እንጠብቃለን
a ፍርሃት ተፈጥሯዊ ስሜት ነው፤ ከአደጋ ሊጠብቀንም ይችላል። ጤናማ ያልሆነ ፍርሃት ግን በተቃራኒው ሊጎዳን ይችላል። እንዴት? ሰይጣን እንዲህ ያለውን ፍርሃት ተጠቅሞ ሊያጠቃን ይሞክራል። በመሆኑም እንዲህ ያለውን ፍርሃት ለመቆጣጠር ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። በዚህ ረገድ ምን ሊረዳን ይችላል? ይሖዋ ከጎናችን እንደሆነና እንደሚወደን መተማመናችን ፍርሃታችንን እንድናሸንፍ የሚረዳን እንዴት እንደሆነ በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን።
b አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
c የጥቅምት 15, 2012 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 7-11ን ተመልከት።
d የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ባልና ሚስት በጉባኤያቸው ላለች አንዲት ታታሪ እህትና ለቤተሰቧ ምግብ ይዘው ሲመጡ።
e የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ወጣት ወንድም ወላጆቹ ቢቃወሙትም አምላክ እንደሚደግፈው እርግጠኛ ነው።