ይሖዋ ለዚህ ሥራ ሥልጠና እየሰጠን ነው
1. ይሖዋ ለሰዎች ኃላፊነት ሲሰጥ ከዚያው ጋር በተያያዘ ምን ያደርግላቸዋል?
1 ይሖዋ ለሰዎች ኃላፊነት ሲሰጥ ኃላፊነቱን መወጣት እንዲችሉ አስፈላጊውን እርዳታ ያደርግላቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ ለኖኅ ከዚያ በፊት ሠርቶት የማያውቀውን ነገር ማለትም መርከብ እንዲሠራ ባዘዘው ጊዜ እንዴት አድርጎ እንደሚሠራ ነግሮታል። (ዘፍ. 6:14-16) ይሖዋ፣ የእስራኤልን ሽማግሌዎችና ፈርዖንን እንዲያነጋግር ትሁት እረኛ የነበረውን ሙሴን በላከው ጊዜ “እኔ እንድትናገር አደርግሃለሁ፤ የምትናገረውንም አስተምርሃለሁ” በማለት ማረጋገጫ ሰጥቶታል። (ዘፀ. 4:12) ይሖዋ ለእኛም ምሥራቹን የመስበክ ሥራ የሰጠን ሲሆን ይህን ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስችለንን ሥልጠና የምናገኝበትን ዝግጅት አድርጎልናል። ለዚህ ሥራ ሥልጠና የሚሰጠን በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤትና በአገልግሎት ስብሰባ አማካኝነት ነው። ከዚህ ሥልጠና ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
2. ከቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ጥቅም ለማግኘት ምን ማድረግ እንችላለን?
2 ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት፦ በእያንዳንዱ ስብሰባ ላይ ከመገኘትህ በፊት ትምህርቱን አንብበው እንዲሁም አጥናው። ከዚያም ተማሪዎች ክፍላቸውን በሚያቀርቡበት ጊዜ ሐሳቡን እንዴት እንዳዳበሩት ስትመለከት የማስተማር ችሎታህ እየተሻሻለ ይሄዳል። (ምሳሌ 27:17) በትምህርት ቤቱ ላይ ስትገኝ የትምህርት ቤቱ መማሪያ መጽሐፍ አይለይህ። እንዲሁም ማሻሻል የምትፈልጋቸውን ነገሮች በመጽሐፉ ላይ ጻፍ። እያንዳንዱ የተማሪ ክፍል ከቀረበ በኋላ የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች ከመጽሐፉ በሚጠቅስበት ጊዜ ልትሠራባቸው በሚገቡ ነጥቦች ላይ አስምር፤ በተጨማሪም ኅዳጎቹ ላይ ጠቃሚ ሐሳቦችን መጻፍ ትችላለህ። ይሁንና ከትምህርት ቤቱ የተሟላ ጥቅም ማግኘት የምትችልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ተሳትፎ ማድረግ ነው። ታዲያ በዚህ ትምህርት ቤት እየተካፈልክ ነው? ክፍል ሲሰጥህ አስቀድመህ ጥሩ ዝግጅት አድርግ እንዲሁም የሚሰጥህን ምክር ሥራበት። አገልግሎት ስትወጣ ደግሞ የተማርከውን በሥራ ላይ አውል።
3. ከአገልግሎት ስብሰባ ጥቅም ለማግኘት ምን ሊረዳን ይችላል?
3 የአገልግሎት ስብሰባ፦ በዚህ ስብሰባ ላይ የሚቀርቡትን ክፍሎች አስቀድመን ማንበባችን እንዲሁም ሐሳብ ለመስጠት ዝግጅት ማድረጋችን ትምህርቱን በሚገባ ለማስታወስ ይረዳናል። አጠር አጠር ያለ ሐሳብ መስጠታችን ብዙ ሰዎች ተሳትፎ እንዲያደርጉ ያስችላል። የሚቀርቡትን ሠርቶ ማሳያዎች በትኩረት ተከታተል፤ አገልግሎትህን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የሚረዱህን ሐሳቦች ተግባራዊ አድርግ። በመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የሚወጡ አገልግሎትህን ለማሻሻል የሚረዱ ርዕሶችን ወደፊት እንድትጠቀምባቸው በቅርብ አስቀምጣቸው።
4. የምናገኘውን ቲኦክራሲያዊ ሥልጠና ጥሩ አድርገን መጠቀም የሚኖርብን ለምንድን ነው?
4 ለኖኅና ለሙሴ እንደተሰጡት ኃላፊነቶች ሁሉ ምሥራቹን በመላው ምድር እንድንሰብክ የተሰጠን ተልእኮም ተፈታታኝ ነው። (ማቴ. 24:14) በታላቁ አስተማሪያችን በይሖዋ ከታመንን እንዲሁም እሱ በሚሰጠን ሥልጠና ጥሩ አድርገን ከተጠቀምን ወጤታማ መሆን እንችላለን።—ኢሳ. 30:20