ከይሖዋ የምትችለውን ያህል ትምህርት እየቀሰምክ ነው?
1. ይሖዋ ትምህርትን የሚመለከተው እንዴት ነው?
1 ታላቅ “አስተማሪ” የሆነው ይሖዋ እንድንማር ይፈልጋል። (ኢሳ. 30:20) ይሖዋ ማስተማር የጀመረው የበኩር ልጁን ከፈጠረ በኋላ ነበር። (ዮሐ. 8:28) አዳም ካመፀም በኋላ ቢሆን ይሖዋ ማስተማሩን አላቆመም፤ እንዲያውም በፍቅር ተነሳስቶ ፍጽምና ለሌላቸው ሰዎች ሥልጠና መስጠቱን ቀጥሏል።—ኢሳ. 48:17, 18፤ 2 ጢሞ. 3:14, 15
2. በዛሬው ጊዜ ምን ዓይነት የትምህርት መርሃ ግብር እየተካሄደ ነው?
2 በዛሬው ጊዜ ይሖዋ በታሪክ ዘመናት ታይቶ የማያውቅ የትምህርት መርሃ ግብር እየመራ ነው። ኢሳይያስ በተነበየው መሠረት በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ምሳሌያዊው “የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተራራ” እየጎረፉ ነው። (ኢሳ. 2:2) ወደዚህ ተራራ መሄድ ያለብን ለምንድን ነው? የአምላክን መንገድ ለመማር ይኸውም ይሖዋ እንዲያስተምረን ነው። (ኢሳ. 2:3) በ2010 የአገልግሎት ዓመት የይሖዋ ምሥክሮች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሰዎች በመስበክና በማስተማር ከ1.6 ቢሊዮን ሰዓት በላይ አሳልፈዋል። በተጨማሪም በዓለም ዙሪያ ከ105,000 በሚበልጡ ጉባኤዎች ውስጥ በየሳምንቱ መንፈሳዊ ትምህርት የሚሰጥ ሲሆን በታማኝና ልባም ባሪያ የሚዘጋጁ ትምህርታዊ የሆኑ ክርስቲያናዊ ጽሑፎች ደግሞ ከ500 በሚበልጡ ቋንቋዎች ይዘጋጃሉ።
3. ይሖዋ ካዘጋጀው ትምህርት በግለሰብ ደረጃ የተጠቀምከው እንዴት ነው?
3 ሙሉ ጥቅም አግኙ፦ ከመለኮታዊ ትምህርት በእጅጉ ተጠቅመናል። አምላክ ስም እንዳለውና ስለ እኛ እንደሚያስብ ተምረናል። (ዘፀ. 6:3፤ 1 ጴጥ. 5:6, 7) ከዚህም በላይ በሕይወት ውስጥ ለሚነሱት እጅግ አንገብጋቢ ጥያቄዎች መልስ አግኝተናል፤ ከእነዚህ መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦ ሰዎች የሚሠቃዩትና የሚሞቱት ለምንድን ነው? እውነተኛ ደስታ ማግኘት የምችለው እንዴት ነው? የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው? ከዚህም ሌላ ይሖዋ ‘ያሰብነው እንዲቃናልን’ የሚረዱን የሥነ ምግባር መመሪያዎችን ሰጥቶናል።—ኢያሱ 1:8
4. ለአምላክ አገልጋዮች የቀረቡት አንዳንድ ሥልጠናዎች የትኞቹ ናቸው? ከይሖዋ የምንችለውን ያህል ትምህርት መቅሰም አለብን የምንለውስ ለምንድን ነው?
4 ከዚህም ባሻገር ይሖዋ በርካታ አገልጋዮቹ ለእሱ የሚያቀርቡትን አገልግሎት እንዲያሻሽሉ ልዩ ሥልጠና አዘጋጅቷል። አንዳንዶች ሊሠለጥኑባቸው የሚችሉ ትምህርት ቤቶች ከገጽ 4-6 ላይ ተዘርዝረዋል። በዚህ ገጽ ላይ ከተዘረዘሩት ሥልጠናዎች መካከል በአንዳንዶቹ ለመካፈል ሁኔታችን ላይፈቅድልን ይችላል፤ ሆኖም እኛ ልንሳተፍባቸው በምንችላቸው ዝግጅቶች ሙሉ በሙሉ እየተጠቀምን ነው? ከፍተኛ ትምህርት እንዲከታተሉ በአስተማሪዎቻቸውና በሌሎች ሰዎች ጫና የሚደረግባቸውን ወጣቶች መንፈሳዊ ግቦች እንዲያወጡና ከሁሉ የላቀውን ትምህርት ይኸውም መለኮታዊውን ትምህርት እንዲከታተሉ እያበረታታናቸው ነው? ከይሖዋ የምንችለውን ያህል ትምህርት መቅሰማችን በዛሬው ጊዜ ደስተኛ ሕይወት እንድንመራ የሚያደርገን ከመሆኑም በተጨማሪ ወደፊት የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ ያስችለናል።—መዝ. 119:105፤ ዮሐ. 17:3
በይሖዋ ድርጅት አማካኝነት የምናገኛቸው አንዳንድ ሥልጠናዎች
መሠረተ ትምህርት
• ዓላማው፦ ሰዎች ማንበብና መጻፍ እንዲችሉ ማስተማር፤ ይህም መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናትና እውነትን ለሌሎች ለማካፈል ያስችላቸዋል።
• የሚፈጀው ጊዜ፦ እንደ አስፈላጊነቱ።
• ቦታ፦ በአካባቢው በሚገኝ የመንግሥት አዳራሽ።
• ተማሪዎቹ፦ ሁሉም አስፋፊዎችና ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች።
• መመዝገብ የሚቻለው እንዴት ነው? ሽማግሌዎች በጉባኤያቸው ውስጥ መሠረተ ትምህርት የሚያስፈልጋቸው ካሉ ትምህርቱ የሚሰጥበትን ዝግጅት ያደርጋሉ፤ ከዚያም እንዲህ ያለ ትምህርት የሚያስፈልጋቸው ሁሉ በዝግጅቱ እንዲጠቀሙ ያበረታታሉ።
ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት
• ዓላማው፦ አስፋፊዎች ምሥራቹን ውጤታማ በሆነ መልኩ መስበክና ማስተማር እንዲችሉ ማሠልጠን።
• የሚፈጀው ጊዜ፦ ሁልጊዜ የሚሰጥ።
• ቦታ፦ በአካባቢው በሚገኝ የመንግሥት አዳራሽ።
• መካፈል የሚችሉት፦ ሁሉም አስፋፊዎች። በተጨማሪም አዘውትረው በጉባኤ የሚገኙ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች የሚቀበሉ እንዲሁም አኗኗራቸው ከክርስቲያናዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚጣጣም ሰዎች መካፈል ይችላሉ።
• መመዝገብ የሚቻለው እንዴት ነው? የቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የበላይ ተመልካቹን አነጋግር።
የውጭ አገር ቋንቋ ትምህርት
• ዓላማው፦ አስፋፊዎች በሌላ ቋንቋ ምሥራቹን መስበክ እንዲችሉ ማሠልጠን።
• የሚፈጀው ጊዜ፦ አራት ወይም አምስት ወር። ትምህርቱ ብዙውን ጊዜ ቅዳሜ ጠዋት የሚሰጥ ሲሆን አንድ ወይም ሁለት ሰዓት ይወስዳል።
• ቦታ፦ ብዙውን ጊዜ በቅርብ በሚገኝ የመንግሥት አዳራሽ።
• መካፈል የሚችሉት፦ ጥሩ አቋም ያላቸውና በውጭ አገር ቋንቋ መስበክ የሚፈልጉ አስፋፊዎች።
• መመዝገብ የሚቻለው እንዴት ነው? ቅርንጫፍ ቢሮው እንደ አስፈላጊነቱ ትምህርት ቤቱን ያዘጋጃል።
የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ
• ዓላማው፦ የመንግሥት አዳራሾችን መገንባትና ማደስ። ይህ ዝግጅት ራሱን የቻለ ትምህርት ቤት ባይሆንም ፈቃደኛ ሠራተኞች በግንባታ ሥራ ላይ እገዛ ማድረግ እንዲችሉ የተለያዩ ሙያዎችን ይሠለጥናሉ።
• የሚፈጀው ጊዜ፦ እንደ ፈቃደኛ ሠራተኛው ሁኔታ።
• ቦታ፦ ለአካባቢ የግንባታ ኮሚቴው በተመደበው በማንኛውም ቦታ። አንዳንድ ፈቃደኛ ሠራተኞች በአደጋ በተጎዱ ራቅ ያሉ አካባቢዎች የእርዳታ ሥራ እንዲሠሩ ሊጋበዙ ይችላሉ።
• ብቃት፦ የተጠመቁ እንዲሁም የሽማግሌዎች አካል የድጋፍ ሐሳብ የጻፉላቸው ወንድሞችና እህቶች። የግንባታ ችሎታ ቢኖራቸውም ባይኖራቸውም በሥራው መካፈል ይችላሉ።
• መመዝገብ የሚቻለው እንዴት ነው? የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ፈቃደኛ ሠራተኞች መጠይቅ (S-82) የተባለውን ቅጽ ከጉባኤህ ሽማግሌዎች ጠይቀህ መሙላት ትችላለህ።
የአቅኚዎች አገልግሎት ትምህርት ቤት
• ዓላማው፦ አቅኚዎች ‘አገልግሎታቸውን በተሟላ ሁኔታ መፈጸም’ እንዲችሉ መርዳት።—2 ጢሞ. 4:5
• የሚፈጀው ጊዜ፦ ሁለት ሳምንት።
• ቦታ፦ ቅርንጫፍ ቢሮው በወሰነው ቦታ፤ ብዙውን ጊዜ በቅርብ በሚገኝ የመንግሥት አዳራሽ።
• ብቃት፦ ቢያንስ ለአንድ ዓመት ዘወትር አቅኚ ሆነው ያገለገሉ።
• መካፈል የሚችሉት፦ ብቃቱን ያሟሉ አቅኚዎች ሁሉ በትምህርት ቤቱ የሚመዘገቡ ሲሆን በወረዳ የበላይ ተመልካቹ አማካኝነት ይህን እንዲያውቁ ይደረጋል።
ለአዲስ ቤቴላውያን የተዘጋጀ ትምህርት ቤት
• ዓላማው፦ ይህ ትምህርት ቤት አዲሶች በቤቴል አገልግሎታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ይረዳቸዋል።
• የሚፈጀው ጊዜ፦ አሥራ ስድስት ሳምንት የሚወሰድ ሲሆን በየሳምንቱ ለአንድ ሰዓት ይካሄዳል።
• ቦታ፦ ቤቴል።
• ብቃት፦ የቤቴል ቤተሰብ ቋሚ አባል የሆነ አሊያም ለረጅም ጊዜ (አንድ ዓመት ወይም ከዚያ በላይ) የሚያገለግል ጊዜያዊ ፈቃደኛ ሠራተኛ።
• መካፈል የሚችሉት፦ ብቃቱን ያሟሉ የቤቴል ቤተሰብ አባላት ሁሉ።
የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት
• ዓላማው፦ ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች መንጋውን እንዲንከባከቡና ድርጅታዊ ኃላፊነቶቻቸውን እንዲወጡ ማሠልጠን። (ሥራ 20:28) ይህ ትምህርት ቤት በየተወሰነ ዓመት እንዲካሄድ የበላይ አካሉ መመሪያ ይሰጣል።
• የሚፈጀው ጊዜ፦ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለሽማግሌዎች አንድ ቀን ተኩል ሲሆን ለጉባኤ አገልጋዮች ደግሞ አንድ ቀን።
• ቦታ፦ ብዙውን ጊዜ በቅርብ በሚገኝ የመንግሥት አዳራሽ ወይም የትልቅ ስብሰባ አዳራሽ።
• ብቃት፦ ሽማግሌዎች ወይም የጉባኤ አገልጋዮች መሆን አለባቸው።
• መካፈል የሚችሉት፦ የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ብቃቱን ያሟሉ ሽማግሌዎችንና የጉባኤ አገልጋዮችን ይጋብዛል።
የጉባኤ ሽማግሌዎች ትምህርት ቤትa
• ዓላማው፦ ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነቶቻቸውን እንዲወጡ መርዳት።
• የሚፈጀው ጊዜ፦ አምስት ቀናት።
• ቦታ፦ ቅርንጫፍ ቢሮው በወሰነው ቦታ፤ ብዙውን ጊዜ በቅርብ በሚገኝ የመንግሥት አዳራሽ ወይም የትልቅ ስብሰባ አዳራሽ።
• ብቃት፦ ሽማግሌዎች መሆን አለባቸው።
• መካፈል የሚችሉት፦ ቅርንጫፍ ቢሮው ብቃቱን ያሟሉ ሽማግሌዎችን ይጋብዛል።
ለተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና ለሚስቶቻቸው የተዘጋጀ ትምህርት ቤትb
• ዓላማው፦ የወረዳና የአውራጃ የበላይ ተመልካቾች ጉባኤዎችን በማገልገል ረገድ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ፣ “በመናገርና በማስተማር ተግተው [እንዲሠሩ]” እንዲሁም ለመንጋው ጥሩ እረኛ መሆን እንዲችሉ መርዳት።—1 ጢሞ. 5:17፤ 1 ጴጥ. 5:2, 3
• የሚፈጀው ጊዜ፦ ሁለት ወር።
• ቦታ፦ ቅርንጫፍ ቢሮው በወሰነው ቦታ።
• ብቃት፦ የወረዳ ወይም የአውራጃ የበላይ ተመልካቾች መሆን አለባቸው።
• መካፈል የሚችሉት፦ ቅርንጫፍ ቢሮው ብቃቱን ያሟሉ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችንና ሚስቶቻቸውን ይጋብዛል።
ለነጠላ ወንድሞች የተዘጋጀ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት
• ዓላማው፦ ነጠላ የሆኑ ሽማግሌዎችንና የጉባኤ አገልጋዮችን ለተጨማሪ ኃላፊነት ማዘጋጀት። አብዛኞቹ ተመራቂዎች፣ በሚኖሩበት አገር ውስጥ ብቃት ያላቸው ወንድሞች በሚያስፈልጉበት ቦታ ይመደባሉ። ከአገራቸው ውጪ ለማገልገል ፈቃደኞች የሆኑ አንዳንድ ወንድሞች በሌላ አገር ሊመደቡ ይችላሉ።
• የሚፈጀው ጊዜ፦ ሁለት ወር።
• ቦታ፦ ቅርንጫፍ ቢሮው በወሰነው ቦታ፤ ብዙውን ጊዜ በመንግሥት አዳራሽ ወይም በትልቅ ስብሰባ አዳራሽ።
• ብቃት፦ ከ23 እስከ 62 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ፣ ጥሩ ጤንነት ያላቸው እንዲሁም በተመደቡበት ቦታ ሁሉ ወንድሞቻቸውን የማገልገልና የስብከቱን ሥራ የማከናወን ፍላጎት ያላቸው ነጠላ ወንድሞች። (ማር. 10:29, 30) ቢያንስ ለሁለት ተከታታይ ዓመታት የጉባኤ አገልጋይ ወይም ሽማግሌ ሆነው እያገለገሉ ያሉ መሆን አለባቸው።
• መካፈል የሚችሉት፦ የምትኖርበትን አካባቢ በበላይነት በሚከታተለው ቅርንጫፍ ቢሮ ሥር ይህ ትምህርት ቤት የሚካሄድ ከሆነ በወረዳ ስብሰባ ወቅት ከአመልካቾች ጋር ስብሰባ ይደረጋል። በዚህ ስብሰባ ላይ ተጨማሪ መረጃ ይሰጣል።
ለባለትዳሮች የተዘጋጀ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤትc
• ዓላማው፦ ይሖዋና ድርጅቱ ይበልጥ ሊጠቀሙባቸው እንዲችሉ ለባለትዳሮች ልዩ ሥልጠና መስጠት። አብዛኞቹ ተመራቂዎች በሚኖሩበት አገር ውስጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ይመደባሉ። ከአገራቸው ውጪ ለማገልገል ፈቃደኞች የሆኑ አንዳንዶች በሌላ አገር ሊመደቡ ይችላሉ።
• የሚፈጀው ጊዜ፦ ሁለት ወር።
• ቦታ፦ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ክፍሎች ፓተርሰን፣ ኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የትምህርት ማዕከል ውስጥ በአሁኑ ጊዜ እየተካሄዱ ነው። ከዚያ በኋላ ቅርንጫፍ ቢሮው በወሰነው ቦታ፣ ብዙውን ጊዜ በመንግሥት አዳራሽ ወይም በትልቅ ስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ይካሄዳል።
• ብቃት፦ ከ25 እስከ 50 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ፣ ጥሩ ጤንነት ያላቸው፣ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉባቸው ቦታዎች ሁሉ ለማገልገል ሁኔታቸው የሚፈቅድላቸውና “እነሆኝ፤ እኔን ላከኝ” የሚል ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ የሆኑ ባለትዳሮች። (ኢሳ. 6:8) በተጨማሪም ከተጋቡ ቢያንስ ሁለት ዓመት የሆናቸውና ለሁለት ዓመታት ያለማቋረጥ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እየተካፈሉ ያሉ መሆን አለባቸው።
• መካፈል የሚችሉት፦ የምትኖርበትን አካባቢ በበላይነት በሚከታተለው ቅርንጫፍ ቢሮ ሥር ይህ ትምህርት ቤት የሚካሄድ ከሆነ በልዩ ስብሰባ ወቅት ከአመልካቾች ጋር ስብሰባ ይደረጋል። በዚህ ስብሰባ ላይ ተጨማሪ መረጃ ይሰጣል።
ጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት
• ዓላማው፦ አቅኚዎችንና ሌሎች የሙሉ ጊዜ አገልጋዮችን ለሚስዮናዊነት ማዘጋጀት።
• የሚፈጀው ጊዜ፦ አምስት ወር።
• ቦታ፦ ፓተርሰን፣ ኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የትምህርት ማዕከል።
• ብቃት፦ ከተጠመቁ ሦስት ዓመት የሆናቸውና ለመጀመሪያ ጊዜ ማመልከቻ ሲያስገቡ ከ21 እስከ 38 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ባለትዳሮች። እንግሊዝኛ መናገር የሚችሉ፣ ከተጋቡ ቢያንስ ሁለት ዓመት የሆናቸውና ለሁለት ዓመታት ያለማቋረጥ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እየተካፈሉ ያሉ መሆን አለባቸው። አመልካቾች በጥሩ ጤንነት ላይ የሚገኙ ሊሆኑ ይገባል። በሌላ አገር እያገለገሉ ያሉ አቅኚዎች (እንደ ሚስዮናውያን የሚታዩትን ይጨምራል)፣ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች፣ የቤቴል ቤተሰብ አባላት እንዲሁም ከዚህ ቀደም ከአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት፣ ለነጠላ ወንድሞች ከተዘጋጀው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት እና ለባለትዳሮች ከተዘጋጀው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የተመረቁና ብቃቶቹን የሚያሟሉ ሁሉ ሊያመለክቱ ይችላሉ።
• መካፈል የሚችሉት፦ በተወሰኑ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ በዚህ ትምህርት ቤት መካፈል ከሚፈልጉ ጋር በአውራጃ ስብሰባ ወቅት ስብሰባ ይደረጋል። በዚህ ስብሰባ ላይ ተጨማሪ መረጃ ይሰጣል። በትምህርት ቤቱ ለመካፈል የምትፈልጉ ከሆነና በምትኖሩበት አካባቢ በአውራጃ ስብሰባ ወቅት እንዲህ ዓይነቱ ስብሰባ የማይካሄድ ከሆነ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው መጻፍ ትችላላችሁ።
ለቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላትና ለሚስቶቻቸው የተዘጋጀ ትምህርት ቤት
• ዓላማው፦ የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላት ሆነው የሚያገለግሉ ወንድሞች የቤቴል ቤቶችን የመምራት፣ ጉባኤዎችን የሚመለከቱ የአገልግሎት ጉዳዮችን የመመርመር፣ በክልላቸው ውስጥ ያሉ ወረዳዎችንና አውራጃዎችን በበላይነት የመምራት እንዲሁም ከትርጉም፣ ከኅትመትና ጽሑፎችን ከመላክ ጋር የተያያዙ ሥራዎችንና ሌሎች ክፍሎችን በበላይነት የመከታተል ኃላፊነታቸውን በተሻለ መንገድ እንዲወጡ መርዳት።—ሉቃስ 12:48ለ
• የሚፈጀው ጊዜ፦ ሁለት ወር።
• ቦታ፦ ፓተርሰን፣ ኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የትምህርት ማዕከል።
• ብቃት፦ የቅርንጫፍ ወይም የአገር ኮሚቴ አባል የሆኑ አሊያም በትምህርት ቤቱ ከተካፈሉ በኋላ በዚህ ኃላፊነት እንዲያገለግሉ የሚሾሙ።
• መካፈል የሚችሉት፦ የበላይ አካሉ ብቃቱን ያሟሉ ወንድሞችንና ሚስቶቻቸውን ይጋብዛል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ይህ ትምህርት ቤት በአሁኑ ጊዜ የሚካሄደው በሁሉም አገሮች ውስጥ አይደለም።
b ይህ ትምህርት ቤት በአሁኑ ጊዜ የሚካሄደው በሁሉም አገሮች ውስጥ አይደለም።
c ይህ ትምህርት ቤት በአሁኑ ጊዜ የሚካሄደው በሁሉም አገሮች ውስጥ አይደለም።
ይህ ትምህርት ቤት በአሁኑ ጊዜ የሚካሄደው በሁሉም አገሮች ውስጥ አይደለም።