የአቀራረብ ናሙናዎች
በወሩ የመጀመሪያ ቅዳሜ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር የሚረዳ አቀራረብ
“ጓደኛ የማያስፈልገው ሰው የለም ቢባል እንደሚስማሙ እርግጠኛ ነኝ። ለጓደኝነት የሚመርጡት ሰው በዋነኛነት ምን ዓይነት ባሕርይ እንዲኖረው ይፈልጋሉ? [ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው።] ይህ መጽሔት ጓደኞቻችንን በጥበብ መምረጥ የሚኖርብን ለምን እንደሆነ የሚገልጽ ጥሩ ሐሳብ ይዟል።” ከዚያም የታኅሣሥ 1ን መጠበቂያ ግንብ ስጠውና በገጽ 16 ላይ በሚገኘው በመጀመሪያው ንዑስ ርዕስ ሥር ያለውን ሐሳብ አብራችሁ ካነበባችሁ በኋላ ተወያዩበት። በተጨማሪም በንዑስ ርዕሱ ውስጥ ከሚገኙት ጥቅሶች መካከል ቢያንስ አንዱን አንብቡ። መጽሔቶቹን ካበረከትክለት በኋላ በሚቀጥለው ጥያቄ ላይ ለመወያየት ቀጠሮ ያዝ።
ታኅሣሥ 1 መጠበቂያ ግንብ
“ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተፈጥሮ አደጋዎች እየተበራከቱ የመጡት ለምን እንደሆነ አስበው ያውቃሉ? [ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው።] የሚገርመው፣ የተፈጥሮ አደጋዎች የሚበዙበት ዘመን እንደሚመጣ መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ ተናግሯል። [ማቴዎስ 24:7, 8ን አንብብ።] ይህ መጽሔት ‘በዛሬው ጊዜ የተፈጥሮ አደጋዎች ይህን ያህል የበዙት ለምንድን ነው? እነዚህ አደጋዎች የሚደርሱት አምላክ እየቀጣን ስለሆነ ነው? አምላክ በቅርቡ ማንኛውንም የተፈጥሮ አደጋ ሙሉ በሙሉ ያስቀራል ብለን እንድናምን የሚያደርጉን ምን ምክንያቶች አሉ?’ ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።”
ታኅሣሥ ንቁ!
2 ጢሞቴዎስ 3:16ን አንብብ። ከዚያም እንዲህ በል፦ “ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ እንደሆነ የሚያምኑ ቢሆንም አንዳንዶች ግን እንደዚህ አይሰማቸውም። እርስዎስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላሉ? [ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው።] ሰዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ያላቸው አመለካከት የተለያየ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥፋት በርካታ ሙከራዎች እንደተደረጉና የእሱን ያህል የጥቃት ዒላማ የሆነ መጽሐፍ እንደሌለ ብዙዎች ይስማማሉ። ይህ መጽሔት ባለፉት መቶ ዘመናት ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥፋትና ሰዎች እንዳያነቡት ለማገድ የተደረጉ አንዳንድ ጥረቶችን ይገልጻል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት ከጥፋት ሊተርፍ እንደቻለ ያብራራል።”