የማስተማር ችሎታን ለማሻሻል የሚረዱ ሦስት ነጥቦች
1. የማስተማር ችሎታችንን ለማሻሻል ጥረት ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?
1 ሁሉም የይሖዋ ምሥክሮች አስተማሪዎች ናቸው። ሰዎችን ለመጀመሪያ ጊዜ ስናነጋግር፣ ፍላጎታቸውን ለማሳደግ ተመላልሶ መጠይቅ ስናደርግ ወይም መጽሐፍ ቅዱስን ስናስጠና ሌሎችን እያስተማርን ነው። የምናስተምረው ትምህርት ደግሞ ትልቅ ዋጋ አለው። ሰዎችን ስናስተምር “ለመዳን የሚያበቃ ጥበብ” ለማግኘት የሚያስችሏቸውን ‘ቅዱሳን መጻሕፍትን’ በደንብ እንዲገነዘቡ እንረዳቸዋለን። (2 ጢሞ. 3:15) ይህ እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! ከዚህ ቀጥሎ የቀረቡት ሦስት ነጥቦች የማስተማር ችሎታችንን ማሻሻል የምችልበትን መንገድ ይጠቁሙናል።
2. በቀላሉ በሚገባ መንገድ ማስተማር የምንችለው እንዴት ነው?
2 በቀላሉ ሊገባ በሚችል መንገድ ማስተማር፦ ስለ አንድ ርዕሰ ጉዳይ ጠለቅ ያለ እውቀት ካለን ብዙውን ስለ ጉዳዩ በደንብ የማያውቁ ሰዎች ሐሳቡ መረዳት እንደሚከብዳቸው ልንዘነጋ እንችላለን። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን ስታስጠና አላስፈላጊ ዝርዝር ጉዳዮችን ከመናገር ተቆጠብ። ከዚህ ይልቅ በትምህርቱ ዋና ዋና ነጥቦች ላይ ትኩረት አድርግ። ጥሩ አስተማሪ ለመሆን የግድ ብዙ መናገር አያስፈልግህም። (ምሳሌ 10:19) ብዙውን ጊዜ ቁልፍ የሆኑ ጥቅሶችን ማንበብ ብቻ የተሻለ ሊሆን ይችላል። ጥቅሱን ካነበብክ በኋላ ከጥቅሱ ውስጥ ትምህርቱን በሚደግፈው ሐሳብ ላይ ትኩረት አድርግ። ኢየሱስ ከማቴዎስ ምዕራፍ 5 እስከ 7 ላይ ተመዝግቦ በምናገኘው የተራራ ስብከት ላይ ያሉትን ጥልቅ እውነቶች ያስተማረው በቀላሉ በሚገባ መንገድ የነበረ ሲሆን ብዙ ቃላትም አልተጠቀመም።
3. ምሳሌዎች ምን ጥቅም አላቸው? የተሻለ ውጤት የምናገኘውስ ምን ዓይነት ምሳሌዎችን ብንጠቀም ነው?
3 ምሳሌዎችን መጠቀም፦ ምሳሌዎች አእምሮን ያሠራሉ፣ ስሜትን ይኮረኩራሉ እንዲሁም ትምህርቱን ለማስታወስ ይረዳሉ። ጥሩ ምሳሌ ለመጠቀም የግድ የተለየ ችሎታ ሊኖርህ እንደሚገባ ማሰብ አይኖርብህም። ኢየሱስ ብዙውን ጊዜ አጭርና ያልተወሳሰቡ ምሳሌዎችን ይጠቀም ነበር። (ማቴ. 7:3-5፤ 18:2-4) በወረቀት ላይ ጫር ጫር ተደርጎ የተሳለ ሥዕል መጠቀምም በጣም ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ለጉዳዩ ትንሽ ጊዜ ሰጥተህ አስቀድመህ ማሰብህ ውጤታማ የሆነ ምሳሌ ለማግኘት ያስችልሃል።
4. ጥያቄዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?
4 ጥያቄዎችን መጠቀም፦ ጥያቄዎችን መጠቀምህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪህ ጉዳዩን ቆም ብሎ እንዲያስብበት ያደርጉታል። በመሆኑም አንድ ጥያቄ ካቀረብክ በኋላ ተማሪህ መልስ እስኪሰጥ ታገሰው። አንተው ራስህ ወዲያውኑ መልሱን የምትናገር ከሆነ ተማሪህ ትምህርቱን ተረድቶት እንደሆነና እንዳልሆነ ማወቅ አትችልም። ተማሪው የተሳሳተ መልስ ቢሰጥ እንኳ ወዲያውኑ ለማረም ከመሞከር ይልቅ ተጨማሪ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ራሱ ትክክለኛ መደምደሚያ ላይ እንዲደርስ መርዳቱ የተሻለ ነው። (ማቴ. 17:24-27) እርግጥ ነው፣ ማናችንም ብንሆን ፍጹም አስተማሪዎች አይደለንም። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ለምናስተምረው ትምህርት ምንጊዜም ትኩረት እንድንሰጥ ያበረታታናል። እንዲህ ማድረጋችን ለእኛም ሆነ ለሚሰሙን ሰዎች ዘላለማዊ ጥቅም ያስገኛል።—1 ጢሞ. 4:16