በቀላሉ ሊገባ በሚችል መንገድ አስተምር
1. ግልጽና ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማስተማር የሚያስችለው አንዱ ወሳኝ ነገር ምንድን ነው?
1 በቀላሉ ሊገባ በሚችል መንገድ ማስተማር ውጤታማ አስተማሪ ለመሆን ከሚረዱ ወሳኝ ነገሮች አንዱ ነው። ታላቁ አስተማሪ የሆነው ኢየሱስ ያስተማረበትን መንገድ መመርመራችን ‘የማስተማር ጥበባችንን’ ለማሻሻል ይረዳናል። (2 ጢሞ. 4:2፤ ዮሐ. 13:13)
2. በቀላሉ ሊገባ በሚችል መንገድ ማስተማር ምን ነገር ይጨምራል? እንዲህ ያለው የማስተማሪያ ዘዴ ምን ውጤት ያስገኛል?
2 በቀላሉ ሊገባ በሚችል መንገድ ተናገር፦ የተራራው ስብከት ሰዎች ከተናገሯቸው ከየትኞቹም ንግግሮች የበለጡ ጥልቅ እውነቶችን የያዘ ሲሆን ሁሉም የተገለጹት በቀላሉ ሊገባ በሚችል መንገድ ነው። (ማቴ. ምዕ. 5-7) ኢየሱስን ሲያዳምጡ የነበሩ ሰዎች ‘በትምህርት አሰጣጡ እጅግ ተደንቀው’ ነበር። ኢየሱስን ይዘው እንዲመጡ የተላኩ ሰዎችም “ማንም እንደዚህ ሰው ተናግሮ አያውቅም” ብለው ነበር። (ማቴ. 7:28, 29፤ ዮሐ. 7:46) ሌሎችን በሚያሳምን መንገድ እውነትን ለማስረዳት ከባድ የሆኑ ቃላትን፣ የተወሳሰቡ ሐረጎችን ወይም ዝርዝር ነጥቦችን የያዙ ምሳሌዎችን መጠቀም አያስፈልገንም። የተለመዱ አገላለጾች ተጠቅመን እውነትን ለሌሎች በግልጽ ማስረዳት እንችላለን።
3. አንዳንዶች በአንድ ጊዜ በርካታ እውቀቶችን የሚያዥጎደጉዱት ለምን ሊሆን ይችላል? እንዲህ ከማድረግ መቆጠብ የሚቻለውስ እንዴት ነው?
3 መጠኑን ወስኑ፦ ኢየሱስ በአንድ ጊዜ ምን ያህል እውቀት መስጠት እንዳለበት ለመወሰን የአድማጮቹን ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገባ ነበር። (ዮሐ. 16:12) በተለይ ለዘመዶቻችን፣ ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች ወይም ለልጆች በምንመሠክርበት ጊዜ አስተዋዮችና አቀራረባችንን እንደ ሁኔታው የምንለዋውጥ መሆን ይኖርብናል። በጥሞና እያዳመጡን እንደሆነ በሚሰማን ጊዜም እንኳ በአንድ ጊዜ በርካታ እውቀቶችን እንዳናዥጎደጉድባቸው መጠንቀቅ አለብን። ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ስለ እውነተኛው አምላክ ስለ ይሖዋ እውቀት መቅሰማቸውን ለመቀጠል ፈቃደኛ መሆናቸው አይቀርም።—ዮሐ. 17:3፤ 1 ቆሮ. 3:6
4. ዝርዝር ማብራሪያዎችን ከመናገር ይልቅ በዋና ዋና ነጥቦች ላይ ማተኮራችን ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
4 በዋና ዋና ነጥቦች ላይ ትኩረት አድርጉ፦ ኢየሱስ ዝርዝር ማብራሪያዎችን በመናገር የሚሰጠውን ትምህርት አላወሳሰበም። “በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ . . . ይወጣሉ” ብሎ በተናገረ ጊዜ ከሞት የሚነሱት ሰዎች የሚኖሩባቸውን ሁለት ቦታዎች ማብራራት እንዳለበት አልተሰማውም። (ዮሐ. 5:28, 29) እኛም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስንመራ በዋና ዋና ነጥቦች ላይ ብቻ ማተኮር ያለብን ከመሆኑም በላይ መጽሐፉ ላይ የሌሉ አላስፈላጊ ነጥቦችን አንስተን እንድንወያይ የሚገፋፋንን ፍላጎት መግታት ይኖርብናል።
5. በቀላሉ ሊገባ በሚችል መንገድ ማስተማራችን ምን በረከት ያስገኝልናል?
5 ይሖዋ ማወቅ የሚገባንን ነገር ሁሉ ቀላል በሆነ መንገድ ስለሚያስተምረን ምንኛ አመስጋኞች ነን! (ማቴ. 11:25) እኛም በቀላሉ ሊገባ በሚችል መንገድ ለማስተማር ጥረት በማድረግ ውጤታማ አገልግሎት ማከናወን የሚያስገኘውን ደስታ እናጣጥም።