በስብከቱ ሥራ የምንካፈልባቸው አሥራ ሁለት ምክንያቶች
ምሥራቹን የምንሰብከውና ሰዎችን የምናስተምረው ለምንድን ነው? እንዲህ የምናደርግበት ዋናው ምክንያት ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ወደ ሕይወት በሚወስደው መንገድ ላይ እንዲጓዙ ለመርዳት ነው? (ማቴ. 7:14) ይህ ከታች ከተዘረዘሩት ምክንያቶች ውስጥ የመጀመሪያው ቢሆንም ዋነኛው ምክንያት ግን አይደለም። በአገልግሎት የምንካፈልባቸው 12 ምክንያቶች ከዚህ በታች ተዘርዝረዋል፤ ከእነዚህ መካከል በጣም አስፈላጊው የትኛው ይመስልሃል?
1. የሰዎች ሕይወት እንዲድን በር ይከፍታል።—ዮሐ. 17:3
2. ክፉ ሰዎችን ለማስጠንቀቅ ያስችላል።—ሕዝ. 3:18, 19
3. የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንዲፈጸም ያደርጋል።—ማቴ. 24:14
4. የአምላክ ጽድቅ መግለጫ ሆኖ ያገለግላል። ማንም ሰው ቢሆን ‘ይሖዋ ክፉዎችን ከማጥፋቱ በፊት ንስሐ እንዲገቡ ዕድል አልሰጠም’ ብሎ ሊናገር አይችልም።—ሥራ 17:30, 31፤ 1 ጢሞ. 2:3, 4
5. የኢየሱስ ደም የተከፈለላቸውን ሰዎች በመንፈሳዊ እንድንረዳ የተጣለብንን ግዴታ ለመወጣት ያስችለናል።—ሮም 1:14, 15
6. ከደም ዕዳ ነፃ እንድንሆን ያደርገናል።—ሥራ 20:26, 27
7. እኛ ራሳችን ለመዳን የግድ መስበክ ይኖርብናል።—ሕዝ. 3:19፤ ሮም 10:9, 10
8. ባልንጀራችንን እንደምንወድ ማሳየት የምንችልበት መንገድ ነው።—ማቴ. 22:39
9. ለይሖዋና ለልጁ ታዛዦች እንደሆንን ማሳየት የምንችልበት አጋጣሚ ነው።—ማቴ. 28:19, 20
10. የአምልኳችን ክፍል ነው።—ዕብ. 13:15
11. አምላክን እንደምንወደው ያሳያል።—1 ዮሐ. 5:3
12. የይሖዋ ስም እንዲቀደስ አስተዋጽኦ ያበረክታል።—ኢሳ. 43:10-12፤ ማቴ. 6:9
በአገልግሎት የምንካፈልባቸው ምክንያቶች እነዚህ ብቻ እንዳልሆኑ ግልጽ ነው። ለምሳሌ ያህል የስብከቱ ሥራ እምነታችንን የሚያጠናክርልን ከመሆኑም ሌላ ከአምላክ ጋር አብሮ የመሥራት መብት ያስገኝልናል። (1 ቆሮ. 3:9) ይሁንና በአገልግሎት የምንካፈልበት ዋነኛው ምክንያት በቁጥር 12 ላይ የተጠቀሰው ነው። ሰዎች ለስብከታችን የሚሰጡት ምላሽ ምንም ይሁን ምን፣ የምናከናውነው አገልግሎት የአምላክን ስም የሚያስቀድስ ከመሆኑም ሌላ ይሖዋ ለሚሰድበው መልስ እንዲሰጥ ያስችለዋል። (ምሳሌ 27:11 የ1954 ትርጉም) በእርግጥም፣ ‘ምሥራቹን ያለማሰለስ ማስተማራችንንና ማወጃችንን እንድንቀጥል’ የሚያነሳሱ አሳማኝ ምክንያቶች አሉን።—ሥራ 5:42